የእለት ዜና

በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ተለዋጭ ድልድይ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ድልድዩ ሥራው ሲጠናቀቅ ከ100 ዓመታት በላይ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል

በቻይና ኮንስትራክሽን ኮምዩኒኬሽን ካምፓኒ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ተለዋጭ ድልድይ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ርዕስ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ርዕሰ መሥተዳድሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ዛሬ በቦታው ተገኝተው የድልድዩን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

ዶክተር ይልቃል የድልድዩ አጠቃላይ ሥራ በጥራት እየተከናወነ መሆኑን መመልከት ችለናል ብለዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታው ለሥራው መጓተት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ርዕስ መሥተዳድሩ በቀጣይ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርና በክልሉ መንግሥት መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች በመወያየት መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ድልድዩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት ርዕስ መሥተዳድሩ።

በቀጣይም የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግና እንቅስቃሴውን በማያስተጓጉል መልኩ በድልድዩ ግንባታ መጠነኛ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎበት የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንም ይደረጋል ነው ያሉት።

ርዕሰ መሥተዳድሩ በአዲስ የተሾሙ የሥራ ኀላፊዎችም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ይሠራል፤ በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ድልድይም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ምክትል ተጠሪ መሃንዲስ ፍቅረሥላሴ ወርቁ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ 22 ወራት ማስቆጠሩን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሥራው 41 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል።

ሕዝቡ በጉጉት የሚጠብቀውን የድልድዩን ግንባታ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ቀንና ሌሊት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።

በቻይናው ኮንስትራክሽን ኮምዩኒኬሽን ካምፓኒ እየተሠራ የሚገኘው ድልድዩ ሥራው ሲጠናቀቅ ከ100 ዓመታት በላይ አገልግሎት ይሰጣል፤ ድልድዩን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ደግሞ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ማወቅ ተችሏል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com