የእለት ዜና

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በአንድ ቀን ከ60 በላይ ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪራሞ ወረዳ ሀሮ አዲስ አለም ከተማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሸኔ ታጣቂዎች፣ በአንድ ቀን ከ60 በላይ ንጹኃን ሰዎች መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
“ጥበቃ እንዳያደርግልን ሆን ተብሎ ልዩ ኃይል ከአካባቢው እንዲወጣ እየተደረገ ከሞት መትረፍ የማይታሰብ ነው” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ንጹኃን የሚገደሉት ልዩ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እንደወጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች እንደሰማችው፣ ባሳለፍነው መስከረም 30/2014 ከ60 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በኦነግ ሸኔ የተገደሉ ሲሆን፣ ግድያው የተፈጸመው በኪራሙ ወረዳ ሀሮ አዲስ አለም ከተማ ውስጥ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ነው ተብሏል።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም፣ “ልዩ ኃይሎቹ አካባቢውን ለቀው የወጡት ያለ ምንም ተኩስ ስለሆነ ነዋሪዎቹን ለሞት አሳልፎ ለመስጠት የተስማሙ ይመስላል” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
“ፈጣሪ ረድቶን ተኩሱ ከመጀመሩ በፊት ስለሸሸን ከጫካ ተደብቀን ነው ያለነው” የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ተኩሱ ከመጀመሩ በፊት ማለትም መስከረም 29/2014 ቅዳሜ ምሽት ነው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የተደረገው ብለዋል።
“ልዩ ኃይሎቹ እንዲወጡ የተደረጉት ከሞት የተረፉትን ሰዎች ለመጨረስ ሆን ተብሎ ስለታቀደ ይመስላል፤ ጥይት እንዳያልቅባቸውም በጅምላ ይገድላሉ” የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በንጹኃን ዜጎች ላይ ታጣቂዎች ጥቃት የፈጸሙት በገበያ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት እንደሌለ እና ከአካባቢው ለመውጣት ያልቻሉ ሕፃናትና አዛውንቶች በርሃብ ውስጥ መሆናቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ከጥቃት ሸሽተው የወጡትም ነዋሪዎች ጫካ ውስጥ በመሆናቸው ረሃብ እንደተጋረጠባቸውም ነው የገለጹት።

ከምንጮቻችን መካከል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ወጣት፣ “ምግብ ካገኘሁ ሦስት ቀን ሆነኝ፤ ሸሽቼ ጫካ ወስጥ ነው ያለሁት። ገበሬዎች በጥይት ተገድለዋል፤ ሴቶችና ሕፃናትም ሆዳቸው በስለት ተዘርግፎ በየቦታው ወድቀው አይቻለሁ” በማለት ነው የአይን ምስክርነቱን የሰጠው።

ታጣቂዎቹ የሚፈልጉት የአማራ ተወላጅ ኦሮሚያ ክልል እንዳይኖር ማድረግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ “እየተዋጋን እንዳንሞት እንኳን መሣሪያ የለንም። መከላከያ ራሱ እንኳን ሊያግዘን በአካባቢውም የለም። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ብዙ ንጹኃን ሞተው አልቀዋል፤ የቀረነው ጥቂቶቹም ተስፋ ባለመቁረጥ መንግሥትን እየተጠባበቅን ነው” ሲል እማኝነቱን ተናግሯል።

ከጥቃት የተረፉ እና በጫካ ውስጥ ተሸሽገው የሚገኙ ሰዎች፣ ወደ አጎራባች ቦታዎች ለመሄድ ቢፈልጉም ዙሪያ ገባውን በከበባ መያዛቸውን ጠቁመዋል። ከአዲስ ማለዳ ምንጮች መካከል አንዱ፣ “ምሽግ ላይ ነው ያለነው፤ በየአቅጣጫው ተከበናል፤ የሚሞተውም እየሞተ ያው አንዳንድ የተረፍነውም በተስፋ አለን” ሲል ነው የተመለከተውን የገለጸው።

ሸሽተው ለማምለጥ ስላልቻሉ “ሴቶችና ሕፃናትም እየታረዱ በየቦታው ወድቀዋል” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የሸኔ ታጣቂዎች የአማራ ተወላጆችን ከሚኖሩበትን አካባቢ ለቀው እንዳይወጡ አስገድደው እንዳፈኗቸው ገልጸዋል።
ምንጮቻችን አክለውም፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ጥቃቱ እንዳላቆመ የገለጹ ሲሆን፣ መከላከያ እና ልዩ ኃይል ስለሌለ የሟቾችን አስከሬን ለመቅበር ካለመቻሉም ባሻገር፣ የሟቾችን ቁጥርም በውል ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ለኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።
አዲስ ማለዳ በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ንጹኃን እንደተገደሉ፣ ከአካባቢያቸው እንደተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በሠላም መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!