የእለት ዜና

ቤተሰቦቻቸው በጦርነት አካባቢ የሚገኙ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር ላይ ነን አሉ

ከግቢ ውጡ የተባሉ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው ያሉበት አካባቢ በጦርነት ቀጠና ውስጥ በመሆኑ ማረፊያ ስለሌላቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው አገራችን ያለችበትን ጦርነት ግምት ውስጥ በማስገባት የ2013 ትምህርት ዘመን ተመራቂዎችንና የኹለተኛ ዓመት ተማሪዎችን የተለመደውን የአልጋና የምግብ አገልግሎት እያገኙ እንዲቆዩ ፈቅዶላቸው ቢቆይም፣ ባሳለፍነው መስከረም 26/2014 ባወጣው ማስታወቂያ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ አዟል።

ዩኒቨርስቲው ባወጣው ማስታወቂያ ተማሪዎቹ ከመስከረም 30/2014 ጀምሮ ከግቢው ውጡ መባላቸውን ነው አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው። ማስታወቂያው “በ2013 ትምህርት ዘመን የተመረቃችሁ እና ከኹለተኛ ዓመት በላይ የሆናችሁ ተማሪዎች በሰሜኑ አገራችን ክፍል በተፈጠረው ፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻችሁ ያልተመለሳችሁ የምገባና የመኝታ አገልግሎት እያገኛችሁ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ከመስከረም 30/2014 በኋላ በዩኒቨርስቲው ምንም አይነት አገልግሎት ማግኘት የማትችሉና በግቢውም መቆየት የማትችሉ መሆኑን አውቃችሁ ከወዲሁ ዝግጅት እንድታደርጉ እናሳውቃለን” የሚል ነው።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ዩኒቨርስቲው በማስታወቂያው በግቢው ለሚገኙ ሌሎች አካላት ያስተላለፈው መልዕከት የተጠቀሰ ሲሆን፣ መልዕክቱም “የምግብና የመኝታ፣ እንዲሁም የግቢውን ፖሊስና ደኅንነት ጽ/ቤት ከመስከረም 30/2014 በኋላ ከላይ ለተጠቀሱ ተማሪዎች የሚሰጥ አገልግሎት የማይኖር ስለሆነ ከወዲሁ ለተማሪዎች እንድታሳውቁ እንገልጻለን” ማለቱ ተመላክቷል።

ከግቢው ውጡ የተባሉት በ2013 የተመረቁና ከኹለተኛ ዓመት በላይ የሆኑ ተማሪዎች፣ ዩኒቨርስቲው በማስታወቂያው ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት ከፊሉ በአካባቢያቸው ያለውን ችግር በማሳሰብ ከግቢው እንዲቆዩ በማመቻቸት ላይ እንደሆኑና ከፊሉ መውጣታቸውን ነው ምንጮቻችን ያመላከቱት።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በትዕዛዙ መሠረት ከግቢው የወጡ ተማሪዎች እንዳሉና አካባቢያቸው በጦርነት ቀጠና ውስጥ በመሆኑ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ባለመቻላቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል፣ ዩኒቨርስቲው እንዲወጡ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም አካባቢያቸው ያለበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የትንሽ ጊዜ ቆይታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ ግማሾቹ ተማሪዎች፣ ከግቢው ባወይወጡም የተለመደውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ነው ያመላከቱት።

ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ ባለማወቃቸው ማረፊያ ለማግኘት እንደሚቸገሩና ከዚህም ለመዳን በግቢው እንዲቆዩ ለዩኒቨርስተው የጠየቁት ተማሪዎች፣ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ቢያገኙም በተግባር እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) “ተመራቂ ተማሪዎችን እንጅ ከኹለተኛ ዓመት በላይ የሆናችሁትን ውጡ ያልነው በስህተት ነው” ቢሏቸውም፣ በግቢው ውስጥ ትክክለኛውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን አመላክተዋል።

ምንጮቻችን እንደተናገሩት ከሆነ፣ የትግራይና የአማራ ክልል ተማሪዎች አካባቢያቸው በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንዳለ በማሰብ በግቢው እንዲቆዩ ለማድረግ በታሰበው መሰረት የመጡበትን አካባቢ ለማወቅ በስምንተኛ ክፍል መረጃቸው ተለይተው እንዲቆዩ ቢደረግም፣ አልጋ ለማግኘት እየተቸገሩ መሆናቸውን ነው።

በሌላ በኩል፣ ተመራቂ ተማሪዎች በትዕዛዙ መሠረት እንደወጡና ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ስላልቻሉ በችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ አገር ሠላም እስከሚሆን በግቢው መቆየት ብንፈልግም አልቻልንም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
ባሳለፍነው ጥቅምት አንድ 2014 የአንደኛውን ሴሚስተር ፈተና ጨርሰናል የሚሉት ጀማሪ ተማሪዎቹ በበኩላቸው፤ ከግቢው ውጡ እንደተባሉና ገና ባይወጡም ሥጋት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ተማሪዎቹ አያየዘውም፣ እስካሁን ዕረፍት በሚሆንበት ወቅት ወደ ቤተሰብ መሄድ የሚፈልግ ተማሪ መሄድ እንደሚችልና በግቢው መቆየት የሚፈልግ ደግሞ የተለመደውን የአልጋና የመኝታ አገልግሎት እያገኘ መቆየት ይችል ነበር። እንደተናገሩት ከሆነ ግን አሁን ገና ተግባራዊ መሆን አለመሆኑን ባያቁም ከግቢው ውጡ መባላቸውን ነው መረዳት የተቻለው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ማስታወቂያው ለተመራቂ ተማሪዎች እንጂ ለኹለተኛና ከዛ በላይ ለሆኑ ተማሪዎች መባሉ በስህተት መሆኑን ገልጸዋል።
የጀማሪ ተማሪዎችን ቅሬታ በተመለከተም፣ ውጡ እንዳላሉና በግቢው መቆየት እንደሚችሉ በማመላከት፣ ቅሬታቸውንም ለዩኒቨርስቲው ማቅረብ እንደሚችሉና መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!