የእለት ዜና

ባህርዳር በሚገኘው ዘንዘልማ የተፈናቃዮች መጠለያ የፊት ቁስለት በሽታ መከሰቱ ተገለጸ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ጥቃት ከአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን ተፈናቅለው በባህርዳር ዘንዘልማ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የፊት ቁስለት በሽታ እንዳጋጠማቸው ገለጹ።
ህወሓት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ከጥቃት ሸሽተው ባህርዳር በሚገኘው ዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ምንነቱ ባልታወቀ የትንኝ ንክሻ ምክንያት የፊት መቁሰል በሽታ ተከስቶ ብዙዎች ፊታቸው መቁሰሉን ተፈናቃዮቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በሽታው ከተከሰተ ከኹለት ሳምንት በላይ እንደሆነው የገለጹት ተፈናቃዮቹ፣ እስካሁን በሽታው የተከሰተባቸው ሰዎች ፊታቸው በመቁሰሉ እየተቸገሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምንነቱ ባልታወቀ የትንኝ ንክሻ የሚከሰት ነው የተባለው ይህ በሽታ፣ በተፈናቃዮቹ ላይ ተከስቶ የፊት ቁስለት ማስከተሉን ተከትሎ መጠለያውን ለቀው ለመውጣት የተገደዱ ሰዎች መኖራቸው ተገልጿል። በሽታው በመከሰቱ መጠለያውን ለቀው የወጡት ተፈናቃዮች ለጊዜው በራሳቸው ወጪ ከመጠለያ ውጪ የመኖር አቅም ያላቸው ሲሆን፣ በራሳቸው አቅም ከመጠለያ ውጪ መኖር የማይችሉ ተፈናቃዮች በበሽታው እየተጠቁ ቢሆንም፣ በመጠለያው ውስጥ ለመኖር ተገደዋል ተብሏል።

በትንኝ ንክሻ የሚፈጠር ነው የተባለው በተፈናቃዮች ላይ የተከሰተው በሽታ፣ በንጽህና ጉድለት እና ሳር ባለበት አካባቢ በሚኖሩ ትንኞች የተከሰተ ነው ሲሉ ተፈናቃዮቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በሽታው በመጠለያ ጣቢያ መከሰቱን ተከትሎ፣ ጣቢያው ጸረ ተባይ መድኃኒት ከቀናት በፊት መረጨቱን በመጠለያው የሚገኙ ተፈናቃዮች ጠቁመዋል።

መጠለያ ጣቢያው ጸረ ተባይ መድኃኒት መረጨቱን ተከትሎ፣ በተፈናቃዮች ላይ የሚከሰተው በሽታ አዲስ ሰዎችን የማጥቃት ሁኔታው መቀነሱ ተገልጿል። ይሁን እንጅ በበሽታው የሚጠቁ አዲስ ሰዎች ቁጠር ቢቀንስም፣ አሁንም ድረስ በበሽታው የሚታመሙ ሰዎች መኖራቸው ተገልጿል።

በሽታው ከፊት መቁሰል በተጨማሪ የማቃጠል እና የማሳከክ ባህሪ እንዳለው የተናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ እንዳንድ ሰዎች ላይ የተከሰተው የፊት መቁሰል የከፋ በመሆኑ ወደ ሕክምና ለመሄድ መገደዳቸውን ተፈናቃዮቹ ጠቁመዋል። በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙ ተፈናቀዮች መካከል ታናሽ ወንድሙ በበሽታው የተጠቃበት መንግስቴ ደሳለኝ፣ ወንድሙ ላይ የተከሰተው የፊት መቁሰል ከፍተኛ የመቁሰልና የሕመም ስሜት በመፍጠሩ ወደ ሕክምና ለመውሰድ መገደዱን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በሽታው ከተከሰተ በኋላ ውኃ ሲነካው እንደሚባባስ የተገለጸ ሲሆን፣ በሽታው የተከሰተባቸው ሰዎች ፊታቸውን ውኃ እንደማያስነኩ ገልጸዋል። በሽታው ከሚያስከትላቸው የሕመም ስሜቶች መካከል የማሳከክ ስሜት አንዱ ሲሆን፣ በእጅ ሲነካ ቁስሉ የመባባስ ሁኔታ እንዳለውም ተመላክቷል።

በሌላ በኩል፣ በዘንዘልማ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በመንግሥትም ይሁን በረጅ አካላት የሚቀርቡ ድጋፎችን በተገቢው ሁኔታ ለተፈናቃዮች የማዳረስ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። በመጠለያ ጣቢያው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚቀርበው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ሁሉንም ማዳረስ የሚችል ቢሆንም፣ የሚገኘውን ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ የማድረግ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ተፈናቃዮች ገልጸዋል።

በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ህወሓት ከተቆጣራቸው የዋግኸምራ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከጥቃት ሸሽተው የተፈናቀሉ ዜጎች ሲሆኑ፣ በተጠለሉበት መጠለያ የባህርዳር ነዋሪዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው ከመንግሥትና ከረጅ አካላት ድጋፍ እስከሚያገኙ ድረስ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com