አዲሱ በጀት፡ ከነባራዊው እውነታ አንፃር

0
794

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው ፈጣን ዕድገት መንግስት በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ ድርሻ የተገኘ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ነገር ግን ይህ ለረጅም ዓመታት ሲታይ የነበረው በመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ላይ የተመሰረተ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ መቀነስ በማሳየት አዲስ መስመር ውስጥ መግባቱን ባለሞያዎች ይናገራሉ።መንግሥት በየዓመቱ ወደ ኢኮኖሚው የሚያስገባው ገንዘብ ለተከታታይ ኹለት ዓመታት ባሳየው ቅነሳ በተወሰነ መጠን ዕድገቱን እንደገታው የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ይናገራሉ።

ምንም እንኳን የ2011 እና የ2012 የፌደራል መንግሥት በጀት በብር ጭማሪ አሳይቷል ተብሎ ቢነገርም በዶላር ሲሰላ ግን ትንሽ የሚባል ቢሆንም መቀነስ አሳይቷል። የ2011 በጀት ከ2010 ጋር ሲነፃፀር የ12 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት ወደ 346.9 ብር ከፍ ብሎ ነበር። ነገር ግን በጀቱ በወቅቱ ብር ከዶላር አንጻር ከነበረው ምንዛሬ ጋር ሲታይ የ15 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።የያዝነው የበጀት ዓመትም ካለፈው ጋር ሲነጻፀር(ከተጨማሪ በጀቱ ውጪ) የ40 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ቢያሳይም ባለፈው ዓመት ከነበረው የ13.9 ቢሊዮን ዶላር በጀት ጋር ሲነጻጸርየ1.8 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ 13.4 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ ጸድቋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጌታቸው ተክለማርያም እንደሚሉት መንግሥት በመጪው ዓመት የብር ዋጋ ከዋና ዋና የውጪ ምንዛሬ ገንዘቦች አንጻር እስክ ስድስት በመቶ መቀነሱ እየናረ ከመጣው ዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ የበጀቱን የመግዛት አቅም ያሳንሰዋል።

በተጨማሪም መንግሥት በበጀት ዓመቱ ያጋጥመኛል ያለው የ97 ቢሊዮን ብር ጉድለት ቀላል የማይባል ነው የሚሉት ጌታቸው፥ ከዚህ ከፍ ያለ ጉድለት ሊያጋጥም እንደሚችል ያብራራሉ። ያለፉት 10ዓመታትን የግብር አሳባሰብ መጠን በመመልከት በአማካኝ ከዕቅዱ 65 በመቶ አካባቢ በመሆኑ እና በአንድ ዓመት ውስጥ መቶ በመቶ ስለማይደርስ ከግብር ይገኛል የተባለው ገቢ ዝቅ ሊል እንደሚችል እና የበጀት ጉድለቱ ከተባለው ሊሰፋ መቻሉ እሙን ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

“ይህንን ያህል የበጀት ጉድለት የምታስተናግድ አገር፥ እንዴት አድርጋ ነው የዋጋ ግሽበቱን በነጠላ ቁጥር ልታስኬድ የምትችለው” ብለው የሚጠይቁት የኢኮኖሚ ባለሞያው መልሱ በመንግሥት ዕቅድ ላይ በግልፅ አልተቀመጠም ብለው ያምናሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት የተጨማሪ እሴት ታክስን መሰረት በማስፋት፣ ከቀረጥ የሚሰበሰብ ገቢን በመጨመር፣ እንዲሁም በሚሻሻሉ ሕጎች አማከኝነት ገቢ ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

“የእኛ አገር የዋጋ ግሽበት ከውጪ የሚገባ አይደለም” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ንግግር የሚዋሱት ጌታቸው ይህ ማለት የዋጋ ግሽበቱ ምንጭ የገንዘብ ፖሊሲው ነው ማለት መሆኑን ይናገራሉ። የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ብድር ለመውሰድ እንደሚገደድ እና ብሔራዊ ባንክም ብር በማተም በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የሚንሸራሻረውን ገንዘብ ያለአግባብ በመጨመር በረጅም እና በአጭር ጊዜ የግሽበት አደጋ ይዞ እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም ይላሉ።

በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚው ሌላኛው ራስ ምታት የሆነውን የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት መንግሥት 3ሚሊዮን ሥራ ለመፍጠር ያሰበ ሲሆን ይህም አዲስ በተቋቋመው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አማካኝነት የሚመራ ይሆናል። ኮሚሽኑ ለመደበኛ ወጪዎቹ የተመደበለት 36 ሚሊዮን ብር ነው።

በያዝነው ዓመት በመስኖ ልማት ዘርፍ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች በዘርፉ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሰለጠኑ ወጣቶችን ወደተለያዩ የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ይጓዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።

ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚው የቤት ሥራ የሆኑትን የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር እንዲሁም ሥራ አጥነትን የመፍታት ኀላፊነት የነበረበት ብሔራዊ ባንክ አሁንም ለተያዘው የበጀት ዓመት የተለየ ሥራ ይሠራል ብለው እንደማያምኑ ጌታቸው ይናገራሉ። ባንኩ የራሱ አካሔድ የሌለው እና የሕግ አስፈጻሚው አጀንዳ ፈጻሚ ስለሆነ አሁንም በነፃነት ትክክለኝ የማክሮ ኢኮኖሚ ውሳኔዎችን ከመስጠት ይልቅ የመንግሥትን ፖሊስ አስፈጻሚ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተከታታይ ሲመዘገብ የነበረው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ መጨመር ቀርቶ ባለበት ባልቆመበት ሁኔታ በሚቀጥለው ዓመትም ይሳካል የተባለው የ9በመቶ ዕድገት እንዴት ሊፈፀም እንደታሰበ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴታው እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በተለያየ ጊዜ የሰጡት መግለጫ ለማብራራት ይሞክራል።

“በቢሊዮን ዶላሮች የውጪ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ የማዕድን ፕሮጀክቶች ውሳኔ መስጠት ባለመቻሉ ሲንከባለሉ የመጡትን በመጪው የበጀት ዓመት ወደ ሥራ በማስገባት ከፍተኛ ገቢ ለመፍጠር ታስቧል” ያሉት እዮብ የቤተ መንግሥቱን ፕሮጀክት ጨምሮ በቱሪዝሙ ዘርፉ እጅግ ብዙ ያልታዩ ነገር ግን ወደ ገቢ ለመቀየር የሚሰሩ ስራዎች አዳዲስ የመዋእለ ነዋይ ምንጮች እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

እዮብ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ ያላቸው ወጣቶች ላይ ሀብት በማፍሰስ የሚሠሩ ሥራዎች ሌላው አማራጭ መሆኑን ጠቁመው፥ይህንን ወደ ሥራ የሚያስገባ የሕግ ማዕቀፍ በብሔራዊ ባንክ አማካኝነት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።በተጨማሪም የግሉን ዘርፍ ምርታማነት የሚገድቡ ቢሮክራሲዎችን ለማስቀረት ይሠራል ማለታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን በሰፊው ዘግበውታል።

የመስኖ ዘርፉን በማነቃቃት ግብርናው ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን ሲያብራሩም የግሉ ዘርፍ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች በተጨማሪም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የያዝነው የበጀት ዓመት ካለፉት ዓመታት የመጡ ጫናዎች አሉበት ከእነዚህም መካከል እንደ ጌታቸው ገለጻ፥የተፈናቀሉ ከ2.8 ሚሊዮን አካባቢ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም አንዱ ነው። ምንም እንኳን የልማት አጋሮች አብዛኛውን ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም መንግሥት ላይም የራሱ ጫና እንደሚኖረው ይጠበቃል ብለዋል።
በመጪው ዓመት ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ አማካኝነት የሚጨምሩ የጸጥታ እና ተለያዩ ወጪዎችም ቀላል የሚባሉ እንደማይሆኑ በመግለፅ ሌላኛው ጫና እንደሚሆን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ለመከላከያ የተመደበው በጀት ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 6.25 ሲሆን እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ያለፈው ዓመት የመከላከያ በጀት 3.8 በመቶ ነበር። የያዝነው አመት ጭማሪ ከ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ትልቁ የሚባል ሲሆን ከፍተኛ የሚባለው የመከላከያ በጀት በ1992ቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተመደበው እንደነበረ የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል። በወቅቱ 36.1 በመቶ የአገሪቱ የመንግሥት በጀት የተመደበለት መከላከያው፥ ወታደራዊው አገዛዝ ደርግ በመውደቂያው ዓመት ከያዘው የ30.7 በመቶ የበለጠም ነበር። የአንድ አገር የመከላከያ በጀት ያጋጥመኛል ብላ ከምታስበው ጥቃት በመነሳት የሚመደብ ሲሆን አሜሪካ እና ቻይና ዓለም በአመት ለመከላከያ ከምትመድበው በጀት ላይ ግማሹን እንደሚወስዱ የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

በኢትዮጵያም በያዝነው ዓመት በከፍተኛ መጠን ያደገው የመከላከያ በጀት ለግብርና ከተመደበው 14.5 ቢሊዮን ብር የተወሰነ ብልጫ በማሳይት 15 ቢሊዮን ብር ሆኗል። መንግሥት የመከላከያውን የደንብ ልብስ መልክ (Pattern) ለመቀየር ከማሰቡ ባሻገር የባሕር ኀይል ማደራጀት እንዲሁም የተለያዩ የወታደራዊ ማሻሻያዎችን ለማካሔድ ማሰቡ ይታወቃል።የፍትሕ እና የደኅንነት በጀቱም ስምንት ቢሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ በጀቱ 3.36 በመቶ ይይዛል።
ሌላኛው የ2012 የበጀት ዓመት ያደረ የቤት ሥራ የንግድ ዑደት (Business cycle) መቀነሱ እንደሆነ የሚገልፁት ጌታቸው፥ይህንንም ለማነቃቃት የመንግሥት መዋዕለንዋይ መጨመር ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም በጀቱ ከግምት ውስጥ ያላስገባው ይመስላል ሲሉ ተናግረዋል።

“በየዘርፉ ስንመለከተው በጣም የተጣበበው ይህ በጀት ብዙ እርስ በእርሱ የሚጣረሱ ነገሮች ያሉት ነው” የሚሉት ጌታቸው “በአንድ በኩል ጥብቅ ፊስካል ፖሊሲ እከተላለሁ የሚለው መንግሥት ኹለት ከእሱ ጋር የሚጣረሱ ነገሮችን ሲያከናውን ይታያል።”

የመጀመሪያው የበጀቱ ጉድለት ካለፈው ዓመት በጀት እንዲሁም ከወጪ ንግድ ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ የሚባል መሆኑን ያስረዳሉ። ሌላው ግን ከበጀት ውጪ የሚከናወኑ ነገር ግን በማክሮ ኢኮኖሚውላይ የራሳቸው የሆነ ጫና ያላቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያነሳሉ። የአዲስ አበባ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክትን እንደ አንድ ማሳያ የሚያነሱት ጌታቸው ልክ እንደ ህዳሴ ግድቡ በበጀት ውስጥ የማይገኝ ነገር ግን እንደማንኛውም የመንግሥት ወጪ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ያራሱን ጫና የሚያሳድር ነው ሲሉ ያነሳሉ።

በተጨማሪም በመንግሥት እና በግል አጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የሚያነሱት ጌታቸው መንግሥት በፕሮጀክቶች ውስጥ በሚኖረው ድርሻ አማካኝነት የሚሸከማቸው አደጋዎች (Risks) መኖራቸውን ይገልጻሉ። የግል ባለሀብቱ መቆጣጠር የማይችላቸውን አደጋዎች የሚሽከመው መንግሥት 20 በመቶ አካባቢ አደጋዎች (Risks) መንግሥት እንደሚሸከም ገልጸው፥ ይህ ዓይነቱ ወጪ ግን በበጀቱ ውስጥ የማይካተት ወጪ ነው ይላሉ። የበጀት አፈፃፀሙም በተለይም ከዝቅተኛው መዋቅር ይገጥመዋል ተበሎ ከሚጠበው ችግር አንጻር ሌላኛው ችግር ነው ብላዋለ።ጌታቸው አክለውም የተጨማሪ በጀት መጠን ከ15 ዓመት በፊት ከነበረው አመታዊ በጀት ጋር ተመሳሳይ እስከመሆን የደረሰ መሆኑን አመልክተው፥ለዚህም መጀመሪያ በበጀቱ ማዘጋጀት ወቅት ቀድሞ ተዘጋጅቶ እና ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ወጪ በአግባቡ የመተንበይ ችግር መሆኑን ይናገራሉ።ይህም የመንግሥትን ዕቅድ አዘገጃጀት ብቃት ውስንነት ያሳያል ብለው ያምናሉ።

የፌደራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያሳየው በትምህርቱ ዘርፍ በተለይም በከፍተኛ የትምርት ተቋማት ላይ የሚታየው የበጀት መባከን አሁንም ቀላል የማይበል ፈተና ነው። በያዝነው የበጀት ዓመት 63 በመቶ የሚሆነው የካፒታል በጀት የትምህርት፣ የጤና እና የመሰረተ ልማት የተያዘ ሆኑ ሳለ እነዚህ ዘርፎች ግን እንደ ኦዲተር ጄነራል ዓመታዊ ሪፖርቶች ከፍተኛ የሆነ የበጀት አፈጻጸም ሕግን ያልተከተሉ ናቸው ሲሉ ጌታቸው ያስረዳሉ። በመጪው ዓመት ሕግን ተከትሎ በጀትን የመፈጸም ችግሮች በያዝነው ዓመት እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ እንደማይሆኑ መገመት ይቻላል”ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የፌደራል ዋና ኦዲተር ጄነራል ገመቹ ዱቢሶ እንደሚሉት በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲታይ የነበረው የበጀት አጠቃቀም ችግር በተያዘው በጀት ዓመት ይቃለላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ተመን ሊወጣላቸው የሚገቡ ነገር ግን ያልነበራቸው ወጪዎች የሚኒስትሮች ምክርቤት አዲስ ደንብ አዘጋጅቶ ማሰራጨቱን ጠቅሰው ለውጥ ይታይባቸዋል ብለው እንደሚጠብቁ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ለአብዛኛው ወጪ መመሪያው ተመን ያወጣ ቢሆንም ምንአልባት ተመን ያልወጣላቸው ክፍያዎች ቢያጋጥማቸውም እስከዛሬ እንደሚያደርጉት ያለተመን ከመክፈል ለሚኒስቴሩ በማቅረብ እና በማጸደቅ የራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የተወሰኑት ኹለት ትልልቅ ውሳኔዎች ከሕግ ማስከበር ጋር በተያያዘ ለውጥ እንደሚያመጡ ገልፀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ መሰረት ተቋማት ሕግና ስርዓት ጠብቀው እንዲሠሩ እና ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ ሕግ አስፈፃሚው ይህንን እንዲያሰፈጽሙ መደንገጉን ይናገራሉ።ላለፈው ጥፋት ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እርምጃ እንዲወስድ ምክር ቤቱ አዟል ያሉት ገመቹ ዐቃቤ ሕጉ የደረሰበትን በየሶስትወሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የማቅረብ ግዴታም ተጥሎበታል ብለዋል።

ገመቹ “በምናወጣው ገንዘብ እና በምንሰበስበው መካከል ያለው ክፍተት ከታቀደው በላይ ይሰፋል ተብሎ ባይታሰብም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ይህንን ውስን በጀት በቁጠባ ካልተጠቀሙ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ይህንን የሕዝብ ገንዘብ መቆጠብ ግዴታ ነው” ብለዋል።በተለይም መደበኛ ወጪን በተጠበቀው ልክ ብቻ ሳይሆን ከተጠበቀው በላይ በመቆጠብ እና የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂውን መተግበር አለባቸውም ሲሉ አሳስበዋል።

መስሪያቤታቸው የወጪ ቁጠባ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተቆጣጠረ ነው ያሉት ገመቹ፥ የፕሮጀክት አስተዳደር እና አመራር ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here