የእለት ዜና

በ22 ከተሞች የ‹4ጂ ኤል.ቲ.ኢ› ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ

በኹለተኛ ዙር ማሥፋፊያ ሥራው በ22 ከተሞች ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሩን ኢትዮ-ቴሌኮም ይፋ አድርጓል።
በመጀመሪያው ዙር የማስፋፊያ ሥራው ከፍተኛ የዳታ አጠቃቀም በሚታይባቸው 92 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት አስጀምሮ የነበረው ኢትዮ-ቴሌኮም፣ በኹለተኛው ዙር የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አግልግሎት ማስፋፊያ ሥራም የዳታ ትራፊክና ፍላጎት መሠረት በማድረግ በ22 ከተሞች አገልግሎት ማስጀመሩን ገልጿል።
ከጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በደደር፣ ዱብቲ፣ ደባርቅ፣ እስቴ፣ ሸሃዲ፣ ወረታ፣ ጃዊ፣ አዴት፣ ቢቸና፣ ደጀን፣ ሞጣ፣ አሰላ፣ ጎባ፣ ሮቤ፣ ሶደሬ፣ ባቱ፣ ሐላባ፣ ዱራሜ፣ ኮንሶ፣ ሳውላ፣ ሺንሺቾ፣ እና ወራቤ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጌያለሁ ሲል በላከው መግለጫ አሳውቋል።
አጠቃላይ 112 ከተሞችን የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጸው ኢትዮ-ቴሌኮም፣ ከዚህ ቀደም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑት የደሴ፣ ደብረ ታቦር፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሎጊያ፣ ሆሳዕና፣ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ እና ቡታጅራ ከተሞችም ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ ተከናውኖ ተግባራዊ መደረጉንም አመላክቷል።
በተመሳሳይ ዜና፣ የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ተወካዮች በአዲስ አበባ ውይይት አካሂደዋል። የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚዘጋጀውን የዓለም አቀፉን የቴሌኮም ልማት ኮንፈረንስ ዝግጅት በሚመለከት በአዲስ አበባ መክረዋል።
8ኛው ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ልማት ኮንፈረንስ ከግንቦት 27/2014 ጀምሮ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መካሄዱን በማስመልከት ውይይቱ መካሄዱ ተነግሯል።
ከ2ሺሕ በላይ እንግዶች የሚስተናገዱበት ኮንፈረንስ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዝግጅት እያደረገች ነው የተባለ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ዙሪያ የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ተወካዮች ከቴሌኮም ልማት ኮንፈረንሱ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com