የእለት ዜና

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰሊጥ ወቅቱን ባለጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ እየተሰበሰበ ነው ተባለ

በምዕራብ ጎንደር ዞን በ130 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የለማ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰሊጥ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ መሰብሰብ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በ2013/14 ምርት ዘመን በባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ከዘመቻ ጎን ለጎን የለማ የሰሊጥ ምርት እየተሰበሰበ ነው ያለው ግብርና መምሪያው፣ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ በ55 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የለማ ሰሊጥ ምርት መሰብሰቡን አሳውቋል።
በዞኑ በስፋት የሚመረተውና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት በፍጥነት እየተሰበሰበ መሆኑን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ተናግረዋል። እስከዚህ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ምርቱን ከማሳ ላይ ለማንሳት እየተሠራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከለማው መሬትም 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
በሰሊጥ ሰብል ከለማው መሬት ውስጥ 50 ሺሕ ሔክታር በእርሻ ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሀብቶች የለማ፣ ቀሪው ደግሞ በአርሶ አደሮች የለማ ነው ያለው ተቋሙ፣ ሰሞኑን እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሰሊጥ ሰብል ላይ ብክነት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ጊዜውን ተጠቅመው እንዲሰበስቡ እየተደረገ እንደሆነ አሳውቋል። በዞኑ ባለፈው ዓመት በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ መምሪያው ይፋ አድርጓል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com