የእለት ዜና

ለዕርዳታ የሚውል 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን መጠባበቂያ እህል ግዢ መፈጸሙ ተነገረ

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚውል 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ እህል ግዢ መፈጸሙን ተናግሯል።
በአገሪቱ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ምግብ የሚውል መጠባበቂያ እህል በ8 ማዕከላዊ መጋዝኖች ውስጥ ይገኛል ያለው ኮሚሽኑ፣ ከዚህ በተጨማሪ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን መጠባበቂያ የምግብ እህል ግዢ መፈጸሙን አሳውቋል፡፡
ከተገዛው ውስጥ 72 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ወደ አገር ውስጥ መግባቱ የተነገረ ሲሆን፣ 40 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ደግሞ ወደብ ላይ መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
የቀረው የምግብ እህልም እስከ ፊታችን ታኅሳስ ወር ድረስ ተጓጉዞ አገር ውስጥ በሚገኙ ማከማቻ መጋዝኖች ይሰራጫል የተባለ ሲሆን፣ በቅርቡም ተጨማሪ 300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን መጠባበቂያ የምግብ እህል ለመግዛት አስፈላጊው የግዢ ሒደት መጀመሩ ታውቋል።
የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀቡን ምክንያት በማድረግ፣ ለእነዚህ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት እና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ ተነግሯል።
ወቅታዊውን የተፈናቃዮች ቁጥር ከግምት በማስገባት በአማራ ክልል ባህርዳር እና አፋር ክልል ሰመራ ከተሞች አስቸኳይ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች ተቋቁመዋል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com