የእለት ዜና

የኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ውልደት

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በአንድ ጊዜ ማካሄድ ባትችልም፣ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ ሰኔ14/2013፣ እንዲሁም ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ባሳለፍነው መስከረም 20/2014 አካሂዳለች። የኹለተኛው ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ከተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያ 11ኛውን ክልል ውልደት ያረጋጋጠ መሆኑ ነው።

ምርጫውን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በሚያካሂድበት ወቅት በክልል የመደራጀት ጥያቄ የቀረበበትን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ አብሮ ለማካሄድ በያዘው ዕቀድ መሠረት ባሳለፍነው መስከረም 20/2014 ሕዝበ ውሳኔውን በምርጫ አስወስኗል።

ቦርዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔንን አስመልክቶ መስከረም 29/2014 ባወጣው መግለጫ፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መስከረም 29/2013 በደብዳቤ ቁጥር ፌደም/አፈ/11/61 ባሳወቀው መሠረት፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ማለትም ኮንታ ልዮ ወረዳ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ ካፋ ዞን እና ሻካ ዞን በጋራ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በማቅረባቸው እና ቦርዱም ይህንን እንዲያስፈጽም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበለት በመሆኑ፣ ቦርዱም ሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሚለካበትን መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ በመጠየቅ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በሕዝቡ የተሰጠው ድምጽ አንድ ላይ ተደምሮ የሕዝበ ውሳኔ ውጤት የሚቀርብ መሆኑን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሕዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ መስከረም 20/2014 ማከናወኑን ገልጿል።

የሕዝበ ወሳኔው አፈጻጸም ተዓማኒ እና ሠላማዊ እንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጸ ሲሆን፣ ከነዚህ ሥራዎች መካከልም የሕዝበ ውሳኔውን በጀት ማዘጋጀት፣ ውሳኔው የሚከናወንበትን ጊዜ መወሰን፣ የተለያዩ ውይይቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ማከናወን፣ የአፈጻጸም ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የመራጮች መረጃዎችን ማድረስ እንደሚገኙበት አስታውሷል።

በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት የቦርዱ ባለሙያዎች መረጃዎችን አደራጅተው እና ውሳኔው የሚከናወንባቸው ምርጫ ጣቢያዎች እና ምርጫ ክልሎችን መለየቱን የጠቆመው ቦርዱ፣ በ22 ምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 1613 ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እና የመራጮች ድምጽ አሰጣጥ አከናውኛለሁ ብሏል። ከበጀት ቁጠባ፣ ከአፈጻጸም ቅልጥፍና እና ከጊዜ አንጻር ሕዝበ ውሳኔው ከስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር እንዲከናወን ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሰው ቦርዱ፣ የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚከናወንበት ቀን መቀየሩን ተከትሎ የሕዝበ ውሳኔው የሚከናወንበት ቀን መቀየሩን አስታውሷል።

ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን ሰኔ 14/2013 በተደረገው የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሒደት ጋር በጋራ ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በሕዝበ ውሳኔው ውስጥ ከሚካተቱ ዞኖች መካከል የመራጮች ምዝገባ [በትክክል] ያልተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎች በመኖራቸው የድምጽ አሰጣጥ ሒደቱ ለመስከረም 20/2014 እንዲዛወር መደረጉን ተከትሎ፣ ሕዝበ ውሳኔው ከኹለተኛው ዙር ምርጫ ጋር ተካሂዷል።

ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለማከናወን እስካሁን ከተጠቀመው በጀት ውስጥ 7 ሚሊዮን ብር ከሕዝበ ውሳኔ ጋር ለተገናኙ ሥራዎች ማዋሉን ገልጿል። የሕዝብ ወሳኔውን አፈጻጸም በሠላም ለማከናወን ይቻል ዘንድ ቦርዱ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር፣ ሕዝበ ውሳኔው ከሚከናወንባቸው ዞኖች አስተዳደሮች ጋር በትብብር መሥራቱን ያስታወሰ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ከሕዝበ ውሳኔው አስተባባሪ ፕሮጄክት ቢሮ ጋር የውሳኔውን የምልክት መረጣ ሥራ ማከናወኑን ጠቁሟል።

ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን የሚያስፈፅሙ 4427 አስፈጻሚዎችን መመደቡን ያስታወሰ ሲሆን፣ ለሕዝበ ውሳኔው የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 18 እስከ ግንቦት 6/2013 የተከናወነ ሲሆን ፣ በልዮ ሁኔታ ደግሞ ከነሐሴ 26 እስከ ጷግሜ 6/2013 ድረስ በአንድ ዞን ላይ ኹለተኛ ዙር መራጮች ምዝገባ በማከናወን አንድ ሚሊዮን 344 ሺሕ 622 ያህል ዜጎች በሕዝበ በውሳኔው በመራጭነት ለመሳተፍ ተመዝገበው እንደነበር ጠቁሟል። በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ በአጠቃላይ ከተመዘገበው አንድ ሚሊዮን 344 ሺሕ 622 መራጭ መካከል አንድ ሚሊዮን 262 ሺሕ 679 መራጮች ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ከተመዘገቡት መራጮች በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ የሰጡት 94 በመቶ መሆናቸውን ቦርዱ ገልጿል።

የሕዝበ ውሳኔውን ቁሳቁስ ዝግጅት እና ሥርጭት ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር በመከናወኑ የቁሳቁሶች ግዥ አብሮ የተከናወነ ሲሆን፣ ለሕዝበ ውሳኔው አንድ ሚሊዮን 774 ሺሕ 500 የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ከአገር ውጪ መታተማቸው ተገልጿል። ይሁን እንጂ የታተመው የድምጽ መስጫ ወረቀት ብዛት በሕዝበ ውሳውኔው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ መራጮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር 429 ሺሕ 878 ብልጫ አለው።

ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ቢሮ በቦንጋ ከተማ ከፍቶ ቢሮው ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የማስተባበር ሥራን በማከናውን፣ እንዲሁም የውጤት ድመራን የማጠናቀቅ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል።
ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር የቅድመ ምርጫ ሒደቱ የተከናወነለት ሕዝበ ውሳኔው፣ መስከረም 20/2014 ሲካሄድ ሠላማዊ እና የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

የቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን ዴስክ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄዎችን እየሰጠ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ በቦንጋ ጊዜያዊ ቢሮ የሚያስተባብሩ የቦርዱ ሠራተኞችም ወደተለያዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በመንቀሳቀስ የድምጽ አሰጣጥ ሒደቱን ቀልጣፋ እንዲሆን ከማገዛቸው በተጨማሪ፣ አንድ ሺሕ 424 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች የድምጽ አሰጣጡን ታዝበዋል ተብሏል።

ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቀበለውን ትዕዛዝ ከዓመት በላይ ሲያከናውን የነበረው ምርጫ ቦርድ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ የቀረቡት ኹለት አማራጮች ማለትም በኮንታ ልዮ ወረዳ፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ በካፋ ዞን እና በሻካ ዞን በጋራ ክልል መመስረታቸውን ለመደገፍ ወይንም እነዚሁ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳደሮች የደቡብ ክልል አስተዳደር አካል ሆነው መቆየታቸውን ለመወሰን በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ፣ በክልል የመጀራጀት ጥያቄው እውን ሆኗል።

በቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/ 2011 እንዲሁም በምርጫ ፓለቲካ ፓርቲዎች እና ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 አንቀጽ ስድስት መሠረት በተከናወነው ሕዝበ ውሳኔ፣ በኮንታ ልዮ ወረዳ፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ በካፋ ዞን እና በሻካ ዞን በጋራ ክልል መመስረታቸውን የሚደግፈው አማራጭ በአብላጫ ድምጽ መደገፉ ማረጋገጡን ተከትሎ፣ ቦርዱ በምርጫው ያገኘውን ውጤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ጠቁሟል።

በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ መራጮች ውስጥ አንድ ሚሊዮን 221 ሺሕ 92 መራጮች “የኮንታ ልዮ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ ዳየውሮ ዞን፣ የካፋ ዞን እና የሻካ ዞን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ” በማለት ድምጽ የሰጡ ሲሆን፣ በአንጻሩ 24 ሺሕ 24 መራጮች “የኮንታ ልዮ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የዳውሮ ዞን፣ የካፋ ዞን እና የሻካ ዞን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸሰውን አድግፋለሁ” በማለት ድምጽ ሰጥተዋል።

ምርጫ ቦርድ ባካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል የኢትዮጵያ 11ኛው ክልል ሆኖ እንደሚመሰረት ተገልጿል። ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ክልል መመስረት የሚያስችል ደምጽ ማግኘቱን ተከትሎ፣ ጥቅምት 29/2014 የመንግሥት ምሥረታውን ለማካሄድ መዘጋጀቱን የሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ሰኔ 14/2014 በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት መመስረቱ የሚታወስ ነው። በዚህም ክልሎች ካቢኔያቸውን አዋቅረዋል። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተወካዮች አለመካተታቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አዲስ ክልል ስለሚመሰርት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

በደቡብ ክልል ውስጥ ታቅፈው የሚተዳደሩ ብሔር ብሔረሰቦች ባለፉት ዓመታት በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም በክልል የመደራጀት ጥያቄ ያላቸው ብሔረሰቦች አሉ። ከክልሉ ተነጥሎ ክልል የመሆን ጥያቄ የነበረው የአሁኑ ሲዳማ ክልል ኅዳር 10/2012 በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በክልል የመደራጀት ጥያቄውን እውን ማድረጉ የሚታወስ ነው። በኢትዮጵያ አዲስ ክልል ለመመስረት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ በደቡብ ክልል ዉስጥ ይገኝ የነበረው የአሁኑ ሲዳማ ክልል 10ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ የተመሰረተው ሰኔ 11/2012 ነበር።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!