የእለት ዜና

ማን ይናገር… ከቫይረሱ ያገገመ!

‹‹ኮቪድን በተመለከተ ራሴን ጥንቁቅ ነኝ ብዬ አምናለሁ። ሌሎች ይጠነቀቁልኛል ብዬ ሳልተው፤ ሌሎች ራሳቸውን ይጠብቁ ብዬ ሳላጋልጥ ላለፉት ኹለት ዓመታት ለተጠጉ ጊዜያት በጥንቃቄ ዘልቄያለሁ። ማስከ አድርጌ ለመመገብ ሁሉ ያግደረድረኛል። ያ ሁሉ ሆኖ መቶ በመቶ ራሴን አላጋለጥኩም ብዬ አልምልም። እንዴት እስካሁን አልተያዝክም ብሎ ለሚጠይቁኝ ወዳጆቼ ‹ዐይቶ ንቆኛል ወይ ይዞ ለቆኛል› ነበር መልሴ። የ2013 ጳጉሜን ግን በማላመልጠው አቅጣጫ አገኘኝ። ይኸው ለ15 ቀናት ከሞቀ ግብግብ በኋላ ቁንጥጫችንን ቀምሰን ወጥተናል። ይህ በሽታ ፈጽሞ ተገማች በሽታ አይደለም። ሙሉ ቤተሰብን ሲያማቅቅ ዐይተህ ስትደነግጥ በሌላ አቅጣጫ መርጦ ከቤትህ አንተን ያሽሃል። ደካማው እንዴት ይቋቋመዋል ብለህ ስትጨነቅ ደንዳኔውን አፈር ያስበላዋል።

ይህ ሁሉ ሆኖ እግዚአብሔር ካልጠበቀ በረኞች ከንቱ ይደክማሉ ቢሆንም ከእግዜር ጋር ለደቂቃም ቢሆን ሳንዘናጋ ራሳችንን እንጠብቅ። የእኛ ጥንቃቄ ከኛ ባሻገር ላሉ ሁሉ ነውና ኃላፊነታችንን እንወጣ። የት ጋ ሕይወት እንደሚቆም አይታወቅምና ቢያንስ ለመልካም ነገር እንፋጠን።›› ገጣሚና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት

‹ደጅ ያደረ ልብ› እና ‹ጥቁር ነጥብ› የተሰኙ የግጥብ ስብስብ እንዲሁም ‹የደመና መንገድ› የአጭር ልብወለዶች ስብስብ መጽሐፍትን ለአንባብያን ያደረሰው ገጣሚና ደራሲ ይታገሱ፣ ይህን መልዕክት ያጋራው መስከረም 12/2014 ከኮቪድ 19 ማገገሙን ተከትሎ ነው። ይህንንም ስለጤናው ሁኔታ የጠየቁትን ለማመስገንና ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጭምር ለማሳሰብ ሲል ያጋራው ሐሳብ ነው።

እርግጥ ነው! በኮቪድ 19 ቫይረስ ተይዘው፣ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሳይቀር ገብተው ነገር ግን አገግመው የወጡ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ይታገሱ እንዳለው ቫይረሱ ፈጽሞ ተገማች ባለመሆኑ አዛውንትና ተደራራቢ በሽታ ያለባቸውን ብቻ ሳይሆን ወጣቶችንና ይቋቋሙታል ተብሎ የታሰቡትን ሳይቀር ይዞ ሲሄድ ተስተውሏል።

ማን ይናገር?
በኮቪድ ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ መጥቷል። ነገሩ እየተለመደ መስሎ ቁጥሩ ሲጠራ መደንገጥ እየቀረ፣ ጥንቃቄም እየቀነሰ መሄዱ እንጂ በአንድ ቀን ሕይወታቸው እንዳለፈ የሚጠቀሱ ሰዎች የአንድ ሰፈር ሰዎች ቢሆኑ፣ በሰፈሩ ሙሉ ድንኳን ተጥሎ ሐዘን ሲረብብ መመልከቱ ብዙዎችን ሊያነቃ የሚችል መሆኑ ጥርጥር አይኖረውም ነበር። ሩቅ የሚመስል ወይም አይነካንም ያሉት ጉዳይ እንዴትና በየት በኩል ቀርቦ ሊፈትን እንደሚችል መገመት አይቻልም።
ይህን ነጥብ መግቢያችን ያደረግነው ያለምክንያት አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ በገጹ ባስነበበው አንድ ዘገባ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎችን ባካተተ መልኩ እንዴት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መግታት፣ እንዴትስ ማኅበረሰቡ እንዲጠነቀቅ፣ በቫይረሱ ከተያዘም በኋላ ሕመሙን በጽናት እንዲታገል ማድረግ ይቻላል የሚል ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ አጋርቷል።

በዚህም የናይጄሪያዊውን አዴ ኦጉንሳንያን ታሪክ ያነሳል። አዴ ነዋሪነቱ በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ ሲሆን በኮቪድ 19 ቫይረስ ተይዞ ነበር። አስም የተባለው በሽታ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ አስቀድሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር ዘገባው ያትታል። ጓደኞቹ ሳይቀር በሚያደርገው ጥንቃቄ ይስቁበታል። ያም ቢሆን ግን አልፎ አልፎ የሚገኝበት ቦታ ነፋሻማ ሲሆን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሉን አውልቆ ከመንቀሳቀሱ በቀር፣ ጥንቃቄ አላጓደለም ነበር።

ከወራት በፊት ግን ድካምና ከወባ በሽታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምልክትን አስተዋለ። ይህንንም ተከትሎ ሕመም ሲጠናበት ለምርመራ ወደ ሆስፒታል አቀና። ይሄኔ በኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዘ መሆኑ ተረጋገጠ። እናም ነጻ እስኪሆንና እስኪያገግም ድረስ ከቤቱ ሳይወጣ ከረመ። ያ ሰሞን ቀላል አልነበረም። ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ ተነጥሎ ሕመሙን ብቻ እያዳመጠ፣ በቫይረሱ ሳይያዝ በፊት ስለቫይረሱ ይሰማቸው የነበሩ ጉዳዮችን እያሰላሰለ ነው የከረመው። ካገገመ በኋላ ታድያ ሕይወቱን እንደ ወትሮው አልቀጠለም፣ ሰዎችን ለመርዳት መንቀሳቀስ ጀመረ።

እንዴት?
በናይጄሪያ የጤና ሚኒስቴር በዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ፣ አዴን ጨምሮ 48 በኮቮድ 19 ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችን ጠርቶ አመስግኗል። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው፣ ሕመሙን አሳልፈው ካገገሙ በኋላ ሰብሰብ ብለው ምስክርነት የሰጡና ኮቪድን 19 ቫይረስ በነገሠበት በዚህ ወቅት እንዴት ሕይወትን መግፋትና መወጣት ይቻላል የሚለውን ከልምዳቸው ያካፈሉ ናቸው።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰሜኑ አካባቢ ጦርነት እንዲሁም የኑሮ ውድነት ተደራርበው የሰዉን ቀልብና ትኩረት በመላ ገዝተው እንጂ፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለብቻው ከባድ ጫና እያሳደረ ያለ መሆኑ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። እንዲሁም ማኅበረሰቡ በብዛት ለልቦና እና አእምሮ ጤና የዛን ያህል ተገቢ ትኩረት የማይሰጥ በመሆኑ እንጂ፣ ወረርሽኙ በአእምሮ እና ሥነልቦና ላይ የሚያደርሰው ጫና ከባድ የሚባል ነው።

የሚወዷቸውን በወረርሽኙ ምክንያት የተነጠቁና ተስፋ የቆረጡ፣ በቫይረሱ ተይዘው በኋላ ያገገሙ ወይም አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዘ የቅርብ ቤተሰብ ያላቸው፣ ቫይረሱን ለቤተሰቤ ያስያዝኩት እኔ ነኝ የሚል ጥፋተኝነት የሚሰማቸውና በጸጸት ውስጥ ያሉ እንዲሁም አሁን በየሆስፒታሉና በተዘጋ በር ተጨንቀው የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እያለፉ ያሉትና የሚያልፉት መንገድ አካልን ብቻ ሳይሆን መንፈስን የሚፈትን መሆኑም አያጠያይቅም።

ነገር ግን ጉዳዩን ነገሬ ያለው ያለ አይመስልም፤ ነገሬ የተባለም ከሆነ በቂ ትኩረት ያላገኘ መሆኑ አያጠያይቅም። የዓለም ጤና ድርጅትም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ያለፉበትን መንገድ እንዲያካፍሉና እርስ በእርስም እንዲነጋገሩ መደገፉ ስለዚህ ነው። ይልቁንም ራስን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ጥንቃቄ ከማድረግ በተጓዳኝ፣ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መዳን እንደሚቻል እንዲያምኑና በመንፈስ እንዲበረቱ ብርታት እንዲሆናቸው ለማገዝ ነው።

‹‹ይህ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት አሁንም ቫይረሱ የለም ብለው ለሚሞግቱና ለሚዘናጉትም ትምህርት ይሆናል›› ያሉት ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ጉዳዮች መረጃ ልውውጥ ባለሞያ ዶክተር ቶሉሎፕ ፎላሪን ናቸው። እርሳቸው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ከኮቪድ 19 ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች የኖሩትን እውነት ሲናገሩ፣ የተናገሩት ሐሳብ በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉና እንዲያስተውሉ በጎ ተጽእኖ ይፈጥርባቸዋል።›› ብለዋል።

በዚህ ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ በሆነችውና ከፍተኛ የኮቪድ ተጠቂ ባለባት ናይጄሪያ፣ ከኮቪድ 19 ቫይረስ ያገገሙ ሰዎችን በማስተባበር ወደ ማኅበረሰቡ መድረስን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ያገገሙ ሰዎችም አሁን ላይ በቫይረሱ ተይዘው በሕመሙ ላይ ጭንቀትና ስጋት ተደርቦ ለከበዳቸው ሰዎች የሚታገሉበትን ተስፋና ጽናት እንዲሰንቁ ‹አይዟችሁ! ይታለፋል!› እያሉ እያበረታቱ ይገኛሉ።

ከወራት በፊት በኢንግሊዝ የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ይፋ ባደረጉት ጥናት፣ በኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች የመርሳት በሽታን ጨምሮ ለድባቴ በከፍተኛ መጠን ተጋላጭ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። በተለይም በጽኑ ሕሙማን ክፍል የቆዩና በከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሰዎች ለአእምሮ ጤና መታወክ ተጋላጭነታቸው የበለጠ ቅርብ ነው። አስቀድሞ የሥነልቦና ችግር የነበረባቸው ሰዎች ሕመሙ እንደ አዲስ አገርሽቶ ጤናቸው እንደሚታወክ ነው ተመራማሪዎቹ የገለጹት።

ከላይ እንዳነሳነው ለአእምሮ ጤና እምብዛም ትኩረት በማይሰጥባት ኢትዮጵያ ብዙዎች ከጭንቀት ጋር ለብቻቸው ይብሰለሰላሉ። አልያም ስሜትንና የመንፈስ ሕመምን ዋጥ አድርጎ መያዝን እንደ ጥንካሬ በመቁጠር ለከፋ የሥነልቦና እና የአእምሮ ጤና መታወክ ተጋላጭ ይሆናሉ።
በናይጄሪያ የታየው ከኮቪድ 19 ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች የሚያካፍሉት ልምድ በኢትዮጵያም በተግባር ሊታይ የሚገባ ነው። በእርግጥ በተለያዩ አጫጭር መልዕክቶች ውስጥ እነዚህን ሐሳቦች ለማንሳት ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል። ነገር ግን ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብቻ እንጂ ከተያዙ በኋላ ሊኖራቸው የሚገባውን የመንፈስ ጥንካሬ በሚመለከት ብዙ ሲባል አይስተዋልም።

ይህም ጭራሽ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ በድብቅ እንዲይዙት፣ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ምልክቶቹ ጠፉ በሚል ብቻ ከሰዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ያደርጋቸዋል። ተያይዞም የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ መጠን ይጨምረዋል። አገርኛው ብሂል ‹ማን ይናገር የነበረ…ማን ያርዳ የቀበረ!› እንዲል፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች በተለይም ከከባድ ሁኔታ ውስጥ የተሻገሩ ሰዎች፣ አሁን በትግል ላይ ላሉት ጽናትና ተስፋ ይሆናሉና ነገሩ ልብ ሊባል ያሻል። እንዲሁም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ምክክርም በሥነልቦና ጥንካሬ የሚያስፈልጋቸውን የሚያግዝ ስለሚሆን ለጉዳዩ ትኩረት ይሰጠው።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!