የእለት ዜና

“ደሞዝ እያገኙም ከተቸገሩት ጋር ተጋፍተው እርዳታ የሚቀበሉ አሉ”

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በኢሳት ዜናዎችን በመዘገብና በማቅረብ እንዲሁም ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ ለተመልካች በማድረስ የሚታወቅ ባለሙያ ነው። ኢሳት ወደአገር ውስጥ ከገባ ጊዜ አንስቶ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኛው ጋዜጠኛ የማይደፍራቸውን ዘገባዎች ፈልፍሎ በማውጣት ስሙ በብዙዎች ዘንድ በአድናቆት ይነሳል። ኦነግ ወደአገር ገባ ከተባለ ጊዜ አንስቶ በወለጋና በሌሎች የኦሮሚያ ግዛቶች በሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ በተለይም በአማርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ላይ ይፈጸም የነበረ ግፍን በማጋለጥም ይታወቃል። በአጣዬ የተከሰተውን በተመለከተ ለሕዝብ መረጃዎችን በማቅረብ ስሙ የገነነው ይህ ወጣት ጋዜጠኛ፣ ከሠሞኑም ውጊያ በሚካሄድባቸው የሰሜን ወሎ ግዛቶች ረጅም የእግር መንገድ በመጓዝ እውነታውን ለሕዝብ አቅርቧል። በጉዞው ወቅት ስላስተዋለው፣ እንዲሁም ሕዝቡ ስላለበት ሁኔታ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ያለህ ምልከታ ምንድን ነው?
የሰሜኑ ጦርነትን በተመለከተ እከሌ ጥፋተኛ ነው ብዬ መናገሩ ውስጥ አልገባም። ኹሉም ሁኔታውን የሚያውቀው ነው። ከማዕከላዊ ሥልጣን የተባረረው ህወሓት የፈጠረውን ሁኔታ እናውቃለን። በተለይ በሰሜን ትግራይ በነበረው መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ኹላችንም የምናውቀው ነው። ከዛም ቀደም ብሎ የአገሪቱን ማንኛውንም እንቅስቃሴ እከታተል ስለነበር፣ ድርጊታቸው አሉታዊና አፍራሽ እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ። በሥልጣን ላይ እያሉ ጭምር የምናውቃቸው ናቸው፤ “ለምን ይህን አላችሁ?” ይሉም ስለነበር አሁን የሆነው የሚጠበቅ ነው።

የህወሓት ድርጊት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ አሁን የደረሰው ጥፋት ግን ያልተጠበቀ ነው። ያለው የፖለቲካ ቀውስ ቢጠበቅም፣ ሕዝቡ ላይ የተከሰተው መንገላታትና ሰቆቃ ግን ከተጠበቀው በላይ ነው። በዚህ ደረጃ ቀውስ ይከሰታል ብዬ አልገመትኩም ነበር።
ተወልደህ ያደክበት አካባቢ ቀውስ ውስጥ እንደመሆኑ ችግሩ ከተከሰተ አንስቶ ሒደቱን እንዴት ታየዋለህ?
ተወልጄ ያደኩበት አካባቢ ስለሆነ ሒደቱን በየቀኑ እከታተላለሁ። እስከ ኮረምና አላማጣ ያለውን ሁኔታ ከግጭቱ በፊትም ሆነ እስካሁን እየተከታተልኩ ነው። ያለው ሁኔታ አሳፋሪ ነው። እንዲህ የሚያደርጉት ህወሓቶች አገር ያስተዳድሩ ነበር ብለህ ስታስበው ያሳፍራል። ለማነፃጸር እንኳን ይከብዳል። ከዚህ በፊት የወረረንና በባህልና በቋንቋ የማገናኘን ጣሊያን እንኳን ያላደረገውን ጭካኔ ነው እነሱ የፈፀሙት። በተለይ በቅርቡ ሔጄ ስመለከት እንደታዘብኩት ሥራቸው በጣም ያሳፍራል። የታጠቀ ሰው ቢርበው አርሶ አደር ቤት ገብቶ አስገድዶ ሊበላ ይችላል። ጠላቴ ነው ብለህ በምታስበው ቤት በልተህ ጠጥተህ ምን ታደርጋለህ? አስገድደኸው ያበላህን ቤቱ መግደል፣ ቤተሰቡን አስገድዶ መድፈርና የበሉበት ቤት መደብ ላይ ተፀዳድቶ መውጣት ምን ይባላል። እንደዚህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊነት ተመልክቼ አላውቅም። ጦር መሣሪያ ያልያዘን አርሶአደር በዚህ ደረጃ ማንገላታታቸውና ግፍ መፈፀማቸውን ስሰማ እንደኢትዮጵያዊነቴ በጣም ነው ያፈርኩት።

ከህወሓት ጀርባ ቢያንስ የትግራይ ሕዝብ ሊኖር ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ መጠንቀቅ ነበር። አሁን ግን የትግራይ ሕዝብ በልጆቹ ሊያፍር ይገባል። እንዲህ አሰቃቂ ግፍ ሲፈፅሙ የልጆቻችን ተግባር እኛን ሊወክል አይገባም ማለት ይገባቸው ነበር። በተቃራኒው ግን፣ በርቱ አድርጉ እያሉ ነው እየላኩዋቸው ያሉት። ከአማራ ክልል ዶሮና ተራ የሆነ ነገር ዘርፈው ሲሄዱ እያወቁ፣ ሥራችሁ በባህላችን አፀያፊ ነው ብለው ቢያንስ መውቀስ እንዴት ይሳናቸዋል? የትግራይ ሕዝብ ምንም ቢያደርጉ ዝም ብሎ ልጆቹን እየተመለከታቸው ነው። ከመካከላቸው አንድ ይሻላል የሚባል የለም። በሙሉ የሚሠሩት የበቀል ሥራ ነው።

የቀጥታ ኃይሉን ማጥቃት እየቻሉ ምንም የፖለቲካ እውቀት የሌለውን አርሶ አደር ነው እየገደሉ ያሉት። የአእምሮ በሽተኛን ጭምር ነው እየገደሉ የሚገኙት። ክብር ያለውን ሰው ገድለውም መጫወቻ አድርገውታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ወንድ ልጅን ደፍረዋል። በባህል የሌለን በጣም ነውር ሥራን ሌላ አገር ሲሠራ የምንሰማውን ነው የፈፀሙት። ወንድ ልጅ ተደፈረ ሲባል በጣም ነው ያፈርኩት። የሴትም መደፈር አስቀያሚ ቢሆንም፣ ይፈጽሙታል ብሎ ለመገመት አይከብድም። ሚስቱ ተቀምጣ እንዴት ወንድ ልጅ ፊቷ ይደፈራል? የትግራይ ማኅበረሰብ ሌላው ቢቀር ይህን መሰሉን ከሞራል ውጭ ያለ ድርጊት ሊያወግዘው ይገባል። አማራና ትግሬን በጉርብትና ሊያኖር የማይችል ድርጊት ነው የተፈጸመው።

ህወሓትም ሆኑ ካድሬዎቹ ያልፋሉ፤ ሕዝብ ግን ይኖራል። አሁን እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ሕዝብ ነው በሕዝብ ላይ እየፈጸመው ያለው። ሕዝብ እንደሕዝብ ሆኖ ስለታጠቀ ነው ይህን የሚፈፅመው። በሞራላቸው በባህላቸው ያልነበረን ነው የሚሠሩት። እኔ ትግራይ ክልል ለብዙ ዓመት ኑሬያለሁ፤ እንዴት በፍጹም ያልነበረባቸውን ነገር በአንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይፈፅማሉ?

በሰሜን ወሎ ተፈፀሙ ከሚባሉ ተግባራት አኳያ አንዳንዶች ጥቃት ነው ሲሉት፣ ሌሎች ደግሞ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ማስረጃ በማድረግ የአካባቢውን ነዋሪ አፅድቶ የራሳቸውን ወገን የማስፈርና የመስፋፋት ዕቅድ አላቸው ይላሉ። በቦታው ተገኝተህ እንደመመልከትህ ተግባራቸው ምንን ያመላክታል?
ሕዝብ ለማስፈር ከሚባለው አንፃር ዓላማቸው ተለዋዋጭ ስለሆነ የእነሱን ፍላጎት አላውቅም። ዛሬ እንዲህ ነው ስትል፣ ነገ ሌላ ሆኖ ስለምታገኘው ለመተንበይ ያስቸግራል። ይህ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች የመንግሥትን ደካማነት ተጠቅመው እንደፈለጉ መፈንጨታቸውን መመልከት ይቻላል። የመንግሥት አቅም ሲደክም 4 ኪሎ ቤተ-መንግሥት መግባት ይፈልጋሉ። መንግሥት ጠንከር ሲልባቸው እኛ ግዛታችን እስከ አላውሃ ነው ይላሉ። ስለዚህ የእነሱ ፍላጎታቸው የሚመሠረተው በመንግሥት ድክመት ላይ ነው። ሕዝቡ ሲጠነክርባቸው ከእናንተ የምንፈልገው ነገር የለም፣ እኛ ችግራችን ከመንግሥት ጋር ነው እያሉ ለማግባባት ይሞክራሉ። በአጠቃላይ፣ ባህሪያቸው ተለዋዋጭ ስለሆነ በዋናነት ሕዝብን የሚያታልሉበት ነው። መንግሥት ከደከመላቸው አይደለም ኢትዮጵያን ምስራቅ አፍሪካን ቀጥቅጠው ለማስተዳደር ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።

አርሶ አደሩ አሁን ማሳውን እየሰበሰበ አይደለም። ምክንያቱም፣ ጠዋት ሠላም ነው ብሎ ከቤቱ ወጥቶ በየሜዳውና እርሻው ላይ ወድቆ እየቀረ ነው። በየሜዳው አስከሬን ስለሚታይ አርሶ አደሩ የእርሻ ሥራውን እየከወነ አይደለም። ቆቦ ላይ ማሳቸው ላይ የነበሩትን ሜዳ ሜዳውን በመኪና እየገቡ ነው ለማረም በተቀመጡበት የፈጇቸው። አርሶ አደሩን አጥፍተው የራሳቸውን ሊያሠፍሩ ነው የሚለው የሚወሠነው በመንግሥት ድክመት ልክ ነው። እየተዋጉ ያሉት ዓላማ ኑሯቸው አይደለም። አርቀው የሚያስቡ ዓላማ ያላቸው ቢሆኑ የወረሩት አካባቢ ያለውን ሕዝብ “ያው መንግሥት ጥሏችሁ ሔደ” ብለው ከጎናቸው ለማሠለፍ ይሞክሩ ነበር። ሕዝቡን በጠቅላላ ሊጨርሱት ካልሆነ በስተቀር እንዲህ እያደረጉት እንዴት አምጥተው ያሰፍራሉ።

ተፈናቃዮችን በተመለከተ ዕርዳታ የማሠራጨቱ ሒደት ኮምቦልቻንና ደሴን በመሳሠሉ ከተሞች ብቻ ያተኩራል ብለው ቅሬታ የሚያሰሙ አሉ። ገጠራማ አካባቢዎች ያለውን ችግር እንዴት ታነጸጽረዋለህ? ችግሩስ የት አካባቢ ጎልቶ ይታያል?
ቀደም ሲል ዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም የህወሓት ታጣቂዎች ወደተቆጣጠሯቸው የሰሜን ወሎ ግዛቶች ዕርዳታ ለማድረስ መሞከሩን የብሔራዊ አደጋና ሥጋት አመራር ኮሚሽን ነግሮኝ ነበር። ዕርዳታው ወደ አካባቢዎቹ መጓጓዝ ጀምሮ የተወሰነም ተከፋፍሎ ነበር። በአፋር ጭፍራ በኩልና በኡርጌሳ በኩል ባሉት መግቢያዎች ወደ ሰሜን ወሎ ለመግባት ተሞክሮ መሀል ላይ ያስቆመው መንግሥት ነው። ይህን ያደረገበት ምክንያት መሣሪያ ይዘው ያልፋሉ ብለው የፖለቲካ አማካሪዎች በመከሩት መሠረት ነው መባሉን ሰምቻለሁ።

ህወሓቶችን ሁሉም እንደሚጠላ ቢታወቅም፣ በእነሱ ጥላቻ የራስ ወገንም እንዲጎዳ መደረግ የለበትም ነበር። መሣሪያ ይዘው ይገባሉ ቢባልም እህሉ የተጫነው ከኮምቦልቻ ነው። ኮምቦልቻ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን የራሱ መጋዘን ስላለው፣ ከዛ በተጫነ እህል እንዴት መሣሪያ ይዘው ሊገቡ ይችላሉ ሊባል ይችላል። መንግሥት ከፈለገ ሊፈትሽ ይችላል። ከመንግሥት መጋዘን የወጣ እህልን እስከመጨረሻው አጅቦ ማድረስ እየተቻለ እንዴት መሣሪያ ያስገቡላቸዋል ይባላል። በእንዲህ አይነት በማያሳምን ጥርጣሬ አሁን ሕዝቡ ረሃብ ላይ ነው። ሕፃናት በምግብ ዕጦት ተጎድተውና ቀንጭረው ማየት የተለመደ ነው። ሕዝቡ ላይ ረሃብ በግልጽ ተከስቷል፤ እየሞቱም ነው።

ሰሜን ወሎ የዓለም ምግብ ድርጅት እርዳታ እንዳይገባ መደረጉ አንዱ ችግሩን ያባባሰ ተግባር ነው። ገና ለገና የሳተላይት መረጃ ሊሰጡ ይችላሉ ተብሎ በፍርሃት መከልከል አልነበረበትም። በዚህ አይነት ምክንያት ዕርዳታውን መንገድ ላይ አስቁመውታል። በኹለቱም መንገድ የተጓጓዘው ነው የቆመው። አሁን ረሃቡ ተባብሶ ሕዝቡ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። በአካባቢው ያሉ የኤች አይ ቪና ስኳር በሽተኞች መድኃኒት እያገኙ አይደለም። በመድኃኒት ዕጦትና ሕክምና አለመኖር የሞቱ አሉ። አልጋ ላይ የቀሩትን በአካል በተገኘሁበት ጊዜ አግኝቼ ለማነጋገር ችያለሁ። በአጠቃላይ፣ ማኅበራዊ ቀውሱ እየተስፋፋ ሕዝቡ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው።

ወደ ትግራይ ተመሳሳይ እርዳታ እንዲገባ ተፈቅዶ፣ ሰሜን ወሎ ምን የተለየ ምክንያት ኖሮ ነው የተከለከለው?
መጀመሪያ ወደ ሰሜን ወሎ እንዲገባ መንግሥት ፍላጎት ነበረው። ይህን ለማስፈጸም የያኔ የሠላም ሚኒስትር የነበሩት ሙፈሪያት ካሚል ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተሮች ጋር ተፈራርመው ነበር።
በስምምነቱ መሠረት ዕርዳታው ሊገባ ትንሽ ሲቀረው ነው መከላከያ ያስቆመው። ከበላይ ትዕዛዝ መጥቶለት ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክተው የተወሰኑ የድርጅቱ ሠራተኞች በቀናት ውስጥ ውጡ መባላቸው ነው። የሰሜን ወሎው ወደትግራይ እንደተላከው በተመሳሳይ የሚጫነው ከኮምቦልቻው የመንግሥት መጋዘን ነው። ወደ ትግራይ በገባበት አግባብ ወደ ሰሜን ወሎ ይግባ ነበር ጥያቄው። የትግራይ አክቲቪስቶች ስለጮሁባቸው ትግራይ እየገባ ሰሜን ወሎ የሚጮኸለት የማኅበረሰብ አንቂ ስለሌለው ለረሃብ ተዳርጓል። ነዋሪው እንደሕዝብ አልተቆጠረም። መከላከያ በፖለቲካው ጣልቃ እየገባ እንደፈለገ ያስቆመዋል። ከመንግሥት መጋዘን የሚጫን ውስጥ ራሳቸው ካላስገቡ በስተቀር መሣሪያ እንዴት ያልፋል? የሚጠራጠሩ ከሆነ ወይ ራሳቸውን ይፈትሹ።

ሥጋታቸው፣ እህሉን የህወሓት ታጣቂዎች ሊወስዱባቸው ይችላሉ ብለው ከሆነ የማኅበረሰቡ መሪዎች የተቸገሩትን ለይተው ስለሚያውቋቸው እነሱን አገናኝቶ እነሱ እንዲረከቡ ማድረግ ይቻላል። ሌላውን ለማረጋጋት ባይቻል እንኳን ምግብ በበቂ ሁኔታ እንዲገባ አድርጎ ረሃቡ እንዲረጋጋ ማድረግ ይቻላል።

መንግሥት የራሱን መሣሪያ ጥሎ እየወጣ በእህል መሣሪያ ይገባል ብሎ መከልከል ምን ማለት ነው። ታንክና መድፍ መገናኛ ሬዲዮ ጥሎ እየወጣ ያለው መከላከያ ነው። ዙ-23 ና አጠቃቀሙን የማያውቁትን ዘመናዊ መሣሪያ ጥሎ እየወጣ ያለው መከላከያ፣ የሳተላይት መገናኛ ሊሰጡብኝ ይችላሉ በሚል ምክንያት ሕዝቡን ለረሃብ መዳረግ የለበትም። መንግሥት ራሱ አስታጥቋቸው የሚወጣው መሣሪያ ለህወሓቶች ከበቂያቸው በላይ ነው። ትግራይ በገባበት አግባብ ለምን ሰሜን ወሎ እርዳታው አይገባም ብትል የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ምላሽ የለውም።

እየተዋጉ ያሉትን የየአካባቢውን ነዋሪዎች በቦታቸው በተገኘኽበት ወቅት ስለሚገጥማቸው የስንቅም ሆነ የትጥቅ ዕጥረት ጠይቀሃቸው ነበር? በውጊያ ወቅት በሚደርስባቸው ጉዳት ቁስለኛን እንዴት እንደሚያሳክሙ ያስተዋልከው ምንድን ነው?
ማንም ሰው መግባት እንደሚችለው እስከዞብል ድረስ ገብቻለሁ። ዞብል የሚኬደው በኮምቦልቻ ባቲ በኩል በአፋር ክልል ዞን 4 ጭፍራ በኩል ተደርጎ ነው። ረጅም ተራራ ከሆነው ከዞብል በኋላ ወደ ወርቄ ለመግባት የ8 ሰዓት መንገድ በእግር መጓዝ ግድ ይላል። በጦርነቱ የቆሰለ ሠው ይህን የ8 ሰዓት መንገድ ነው በሰው ሸክም በወሳንሳ ሆኖ አቀበቱን ደሙን እያዘራ ወደ ሕክምና የሚሄደው። በዚህ መንገድ ደማቸው አልቆም ብሎ የሞቱ ወጣት ተዋጊ ፋኖዎች መንገዱ ዳር ላይ ተቀብረዋል።

የሰሜን ወሎ አምቡላንስ በሙሉ ለቆ ወጥቷል። አንድ ኹለት ካልቀሩ በስተቀር የኹሉም ወረዳዎች ጥለው ወጥተዋል። የሚገርመው ወደ ዞብል የሚሄደው አንድ አምቡላንስ ብቻ ነው። አማራጭ ስለሌለ አራትና አምስት ቁስለኛ በአንድ ጊዜ ይዞ ይመለሳል። ሌላው ተራውን እየጠበቀ ይኸው አምቡላንስ የአንድ ቀን መንገድ ተጉዞ ካደረሰ በኋላ ተመልሶ ለማምጣት ይሄዳል። ብዙ አምቡላንስ ከተማ ተቀምጦ ከሚውል እንዲሄድ ቢደረግ ምን አለበት? የመንግሥት አመራሮች ናቸው ደሴ አምቡላንሶቹን እየተመላለሱበት ያሉት። በየመጠጥ ቤቱ ይዘዋቸው ሲንቀሳቀሱም አይቻለሁ። እስከመቼ ዝም እንላለን? ከዚህ በላይ ልንወቃቀስበት የምንችለው ጉዳይ የለም።

ወጣቱ ተደራጅቶ ለአገር ራሱን እየሰዋ ነው። የምግባቸው ነገር ባይነሳ ይሻላል። ስንዴ ተቀቅሎ ንፍሮ በሬሽን እየተከፋፈለ ነው ለወራት የዘለቁት። እስካሁን ምሽግ ውስጥ ሳይወጡ ከሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ ያለዕረፍት እየተዋጉ ያሉ አሉ። ህወሓቶች ከገቡ ጀምሮ እስካሁን ከምሽግ ያልወጣ ወጣት ብዙ ነው። እንዲህ ምቾታቸውን ትተው ለሕዝብ ሲዋደቁ የሚቆስሉ ወጣቶች 4 እና አምስት ቀን ጠብቀው ነው ለሕክምና ወደ ከተማ ለመምጣት የሚችሉት። ይህ እንዲሆን የሚያደርጉት አመራሮች እየሆነ ያለው ውስጣቸውን ስላላሳመማቸው ነው። ቤተሰቦቻቸውን ቀድመው ይዘው ወጥተው በጊዜው ደሞዝ እየገባላቸው ስለሆነ ለሌላው ደንታ የላቸውም። ሲጀመር በቡድን የተደራጁና በዝምድና የታሰሩ ስለሆኑ የሕዝቡን ችግር አይረዱም።

ችግሩ በቂ አምቡላንስ አለመመደቡ ብቻ ሳይሆን ዞብልን በመሳሰሉ ወረዳዎች መላክ የነበረባቸው መድኃኒቶች እየተላኩ አይደለም። ፋሻ እንኳን አጥተው የተበላሸ ዝገት ያለበትን ነው ዞብል ላይ የሚጠቀሙት። በቀላሉ መዳን በሚችል ጉዳት ሰው እየሞተ መሆኑ አመራሩ ሊያውቅና ሊያመው ይገባል። ወደ አካባቢው በምስራቅ በኩል በተለያዩ መንገዶች ለመግባት ነፃ ነው። ፍላጎት ነው የጎደለው እንጂ ማንም እንደፈለገ ደርሶ መመለስ ይችላል። በወርቄ በኩል ሜዳ ነው።

አራት ቀበሌዎች ከህወሓት ነፃ ናቸው። ወርቄ፣ ጊቢ፣ ጂራ፣ ዞብል 10 እና 35 ነፃ ናቸው። የእነዚህ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ “እባክህ መንግሽት ናና አስተዳድረን” ብለው ጥሪ ቢያቀርቡም የደረሰላቸው የለም። የህወሓት ታጣቂዎችን ይዘው ሲማርኩ የሚረከባቸው የለም። ለራሳቸው ስንቅ የላቸው ምርኮኛ የሚመግቡበት ይቸግራቸዋል። ተጠርጣሪ ሌባም ሲይዙ የሚረከባቸው ፖሊስም ሆነ የመንግሽት አካል የላቸውም። “የያዝናቸውን ምን እናድርጋቸው” እያሉ ተቸግረዋል። “ቦታውን ነፃ አውጥተንልሃልና እባክህ መንግሥት ና” እያሉ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

አካባቢያቸውን ከወራሪ ለሚጠብቁ ወታደራዊም ሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ መንግሥት የማያደርግበት ምክንያት ይታወቃል?
መንግሥት ለዞብል አምስቱ ቀበሌዎች ድጋፍ አላደረገም። እነሱ ድጋፍ ሳይሆን መንግሥታዊ አስተዳደር እንዲዘረጋላቸው ነው የሚፈልጉት። ከተለያየ አካባቢ ድጋፍ እየተሰባሰበ የሚሄደው ወደ ደሴና ኮምቦልቻን ወደመሳሰሉ ከተሞች ነው። አሠራሩ የራሱ የሆነ ችግር አለው። በርግጥ ማንም ሰው ወደፈለገበት ቦታ ችግሩን ለማቃለል ጠጠር ከወረወረ በቂ ነው። አብዛኛው የመቶና ኹለት መቶ ሺሕ ብር ድጋፍ ይዞ ስለሚሄድ እርዳታውን ለማከፋፈል ያስቸግራል። ሕዝቡ ይጮሀል፤ ለጥቂት ሰዎች ብቻ ደርሶ ሌላው ምንም ሳያገኝ ይቀራል። ኹሉም በፈቀደው መንገድ መደገፍ ስለሚፈልግ ይህ ዓይነት ድርጊት ይደጋገማል።

20ና 30 ኩንታል ይዞ የሚሄድ ሰው ዕርዳታው ሊሸፍን የሚችለው ለ80 ገደማ ሰዎች ነው። ተረጂው ወደ 150 ሺህ ስለሆነ ለማዳረስ በጣም አስቸጋሪ ነው። በዚህ ምክንያት ተፈናቃዩ፣ “እኛ አልደረሰንም” እያለ በየጊዜው ቅሬታ ያቀርባል። እንዲህ የሚሆነው የግለሰቦችን ድጋፍ በተመለከተ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም።

ደሴና ኮምቦልቻ ያሉት ተፈናቃዮች ሰሜን ወሎ ቀያቸው እንደቀሩት አይደለም የተቸገሩት። ከተማ የመጡት አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። ደሞዛቸውንም እያገኙ ስለሆነ ቤት መከራየትም ሆነ ገዝተው መብላት ይችላሉ። የገጠሩ አብዛኛው አልመጣም። አልፎ አልፎ የመጡት ምንም ገቢ የሌላቸውን ለይቶ ነበር ድጋፍ መደረግ የነበረበት። ደሞዝ እያገኙ ከተቸገሩት ጋር ተጋፍተው እርዳታ የሚቀበሉ አሉ። በውስጥ እየተነጋገሩ የተፈናቀለው አርሶ አደር ሳያገኝ ዕርዳታውን የሚያገኙ ደሞዛቸው በባንክ የሚገባላቸው አሉ። እንዲህ አይነት ዕርዳታውን የሚሻሙ ከዚህ አይነት ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል። እኔ የማውቃቸው ተሰልፈው አይቻለሁ፤ በጣም ነውር ነው። መቅረት ያለበት ድርጊት ነው። ቅድሚያ የሚባል ነገር ባለመኖሩ በማከፋፈል ሒደቱ ላይ መድሎ ፈጥሯል።
ለተፈናቃዮች የሚሰጥ የመንግሥት ድጋፍ ውስን ነው፤ ምናልባት ግለሰቦች እየሰጡ ሊሆን ቢችልም፣ ኃላፊነቱን ተክተው እየሠሩ ስለመዝለቃቸው ሒደቱን በአርምሞ እያየነው ነው።

ሠሞኑን የሰሜን ወሎ ግንባር ጦርነቱ ተጀምሮ በድጋሚ በአሻጥር እንዲቆም ተደርጓል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ የሰማኸው አለ?
እኔ ከአካባቢው ከወጣሁ በኋላ ስለሆነ ሁኔታው ተፈጠረ የተባለው፣ እርግጠኛ የሆንኩበት አይደለም። ባላረጋገጥኩት ጉዳይ አሁን ባልናገር ይመረጣል።

በጦርነት ቀጠናው ውስጥ ያሉት ቤተሰቦችህ በምን ሁኔታ ውሰጥ እንዳሉ የምትሰማው ነገር አለ?
ቤተሰቦቼ በምን ሁኔታ እንዳሉ አላውቅም። በዛ አካባቢ ለማስጠየቅ ሞክሬያለሁ፣ ሠላም መሆናቸውን ነው የሚነግሩኝ። ምንም ነገር ማድረግ ስለማልችል ዝርዝር ሁኔታቸውን አላውቅም። ይህ ሁሉ ትግል እየተደረገ የኔ ቤተሰቦች ብቻ የሚለዩበት ነገር የለም። እነሱ ተለይተው የሚሞቱበትም ሆነ የሚድኑበት ነገር የለም። ሊቆስሉም ሊድኑም ይችላሉ፤ የእነሱ ብቻ ተለይቶ አያሳስበኝም። አጠቃላይ የሕዝቡ ችግር ነው የሚያሳስበኝ። ከሕዝቡ የተለየ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም። ከወጡ እግዚያብሔር ያውጣቸው፤ ከሞቱም እንደሌላው ነው የሚሆነው። ከሌላው ማኅበረሰብ የተለየ ነፍስ የላቸውም።

ከሥራህ ጋር በተገኛኘ በግልህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በፃፍከው ነገር ከኢሳት መልቀቅህ ይወራል። ስላልተግባበችሁበት ሒደት ምን ትላለህ?
እኔ ከኢሳት ጋር ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ከአስተዳደሩ ጋር ነበር በሃሳብ የተለያየሁት። ኢሳት ያሳደገኝና እዚህ ደረጃ ያደረሰኝ ቤት ነው። አሁን ካደረገብኝ ይልቅ ያደረገልኝ ስለሚበልጥ አመሰግነዋለሁ።

በስተመጨረሻ አገሪቱ እንዲህ ባለ ሁኔታ በተዘፈቀችበት ወቅት ከጋዜጠኛው፣ ከሕዝብና ከመንግሥት ምን ይጠበቃል ትላለህ?
እኔ ሁሌ ስሠራ ሕዝብን ነው የማየው። ለሕዝብ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ ማንም ሊያግደኝ አይችልም። ሥራዬን ስሠራ ይህን ስለሠራሁ ያሳስረኝ ይሆን ወይ ብዬ አላስብም። ሁሌ ከሕዝብ ወገን ነው መሆን የምፈልገው። አሁን አሁን አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የጦር ግንባር ባይቀርቡም፣ ደሴ ሲሄዱ እንኳን ከመከላከያ ጋር ፎቶ ተነስተው ነው የሚመለሱት። ወይ ታንክ ላይ አሊያም መሣሪያ ይዘው ከመነሳት ውጭ የሕዝቡን ችግር ተረድተው እውነታውን ለማቅረብ አይደፍሩም። ሕፃናት የሚበሉት አጥተው ተሰቃይተው እየታዩ እነሱ ማቅረብ የሚመርጡት መንግሥትን የሚያወድስ ነገር ነው። የወታደሩን ሞራል ለማነሳሳት የሚያደርጉት ጥሩ ቢሆንም ዋና ኃላፊነታቸውን መዘንጋት የለባቸውም። ዓላማቸውን ከሚዘነጉ አለመሄዱ ይሻላቸው ነበር።

የመንግሥት ሚዲያዎች ተሸቀዳድመው የሚዘግቧቸውን አይነት በጎ በጎ ጎኖች ብቻ የግሎቹ ከሚያስተላልፉ፣ ሕፃናት ተርበው እያዩ ባያልፉ ይመረጣል። ሕዝብ ተርቦ የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልገናል እያለው፣ ሕሊና ያለው ጋዜጠኛ በሬ ታርዶለት እንዴት ጨፍሮ ይመለሳል። እንዲህ አይነት ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ጋዜጠኞች ሥራቸውን ለይተው ማወቅ አለባቸው።

ኢትዮጵያን የሚያገለግሉ ጥሩ ጥሩ ጋዜጠኞች አገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ቢኖሩም አሁን ትኩረት ያደረግንባቸው አዲስ አበባ ያሉት ላይ ነው። ከከተማ መውጣት የማይፈልጉ እየተሻሙ የማይረባ ጉዳይንም የሚዘግቡት ላይ ነው አስተያየት መስጠት የምፈልገው። የሕዝቡን ችግር ተዟዙረው ማወቅ የማይፈልጉ በርካቶች ናቸው። 85 በመቶ ይሆናል የሚባለው የአገራችን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ያለበትን ውስብስብ ችግር ማሰማት አይፈልጉም። ባለሥልጣናቱ ያለእነሱ መረጃ ችግሩን እንደማይሰሙ እያወቀ ኃላፊነቱን የማይወጣ ጋዜጠኛ መኖር የለበትም። አብዛኞቻችን የሕዝብን ብሶት ለማየት ፍላጎቱ የለንም።

በሕዝብ ገንዘብ ተቋቁመው የሕዝብ ሚዲያ ነን የሚሉት ጭምር ይህ ችግር ይታይባቸዋል። አብዛኞቹ የሕዝቡን ችግር ነቅሰው ከማውጣት ይልቅ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ።

“ባሪያዎች ነጻ ወጥታችኋል” በተባሉበት ዘመን፣ አንዳንዶቹ “ጌቶቻችንን ጥለን ወዴትም አንሄድም” እንዳሉት ፣ የአሁን ጋዜጠኞችም፣ “ነጻ ሚዲያ” ተብለው የቀደመውን ዘመን አሠራር የሚተገብሩ አሉ። ነጻ ሁኑ ተብለው መሆን አልቻሉም። ገጠር ሔደው መንግሥትን አሞግሰው ብቻ ይመለሳሉ።

መንግሥት ጋዜጠኞች በዘገቡት መሠረት ማስተካከሉን የማይረዱም አሉ። እኔ በግሌ የሰራኋቸው ዘገባዎችን ተከትሎ ማሻሻያ ተደርጎ ተመልክቻለሁ። በሕክምናው ዘርፍ ስለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ስለመሬት ወረራ፣ እና ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሠርቼ መንግሥት ለውጥ አድርጓል። በድሮው መንገድ መጓዝ የፈለግነውና አልስተካከል ያልነው እኛ ጋዜጠኞች ነን። ከህወሓት የፕሬስ ቆፈን ውስጥ ገና አልወጣንም። መንግሥት ውስጥ ያሉ ችግሮችን መጠቆም ብቻ ሳይሆን፣ ሕብረተሰቡ ዘንድ ያሉ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያስተካክሉት መረጃው እንዲደርሳቸው ማድረግ የጋዜጠኞች ኃላፊነት ነው።

ሕዝቡን በተመለከተ ውስጡ መንግሥትንም ሆነ ጋዜጠኛውን መጠራጠር አለ። ያለምክንያት አላምንም ብሎ ከመቆየት እየገመገሙ የሚያጠራጥር ነገር ሲኖር መጠቆም እንጂ ሊርቅ አይገባውም። ሕዝብና መንግሥት እንዳይተማመኑ እንዲራራቁ የሚያደርጉ ደግሞ ሥራቸው ለጠላት ስለሚመች ሊያስቡበት ይገባል።

መንግሥትን በተመለከተ፣ በቀላሉ ማስተካከል የሚችላቸውን ነገሮች ባያቆያቸው መልካም ነው። አንዳንዴም ጭራሽ ችግሩ መኖሩንም አለማወቁን ሊያስተካክል ይገባል። መረጃ እየደረሰውም መተው የለበትም። በተለይ ኦሮሚያ ክልል ላይ እየተፈጠረ ስላለው የዜጎች ዕልቂት እየተነገረው ዝም ማለት አይገባውም። “ምንም የለም” እያለ 40 እና 50 ሰው ተገድሎ ያድራል። የመንግሥት ዋናው ችግሩ የፀጥታውን ሁኔታ ማስጠበቅ አለመቻሉ ነው። አቅሙ ውስንነት አለበት። ለምሳሌ፣ በኮንትሮባንድ በሰሜን ወሎ ለህወሓት ነዳጅ እየደረሰው ነው ብንልም ለመቆጣጠር አልቻለም። ጦርነት ላይ ብንሆንም መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ጉዳይ ችላ ማለቱን ማየት ይቻላል። ይህ በፍጥነት መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!