የእለት ዜና

ምርጫ ቦርድ መብታቸውን የነጠቃቸው ሕዝቦች!

መስከረም 24 በተካሔደው በዓለ ሲመት ላይ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ፣ በርካቶች በፍላጎትም ይሁን በተልዕኮ መገኘታቸው ይታወቃል። ዕለቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ እንግልትና ከፍተኛ ወጪ ያስከተለ ነበር የሚሉት ግዛቸው አበበ፣ በዕለቱ የብልጽግና መሪ የሆኑት ዶ/ር ዐቢይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የታጩበትና የተመረጡበት መንገድ የብዙዎችን መብት የነጠቀ ነው ይላሉ። ምርጫ ቦርድ በርካታ ኢትዮጵያውያን ያልተሳተፉበትና ይሁንታ ያልሰጡበትን ሒደት ሊኮራበት እንደማይገባ በጽሑፋቸው እንዲህ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ብልጽግና የተባለ ቡድናቸው የኢትዮጵያ ገዥ የሆኑበት በዓለ ሲመት መስከረም 24/2014 በአደባባይ ተካሂዷል። በልዩ ሁኔታ የተመረጡ የብልጽግና አክቲቪስቶች፣ ደጋፊዎችና ሌሎች የብልጽግና ቡድን እንግዶች በልዩ የጥሪ ወረቀታቸው እየተለዩ የአደባባዩ ፌሽታ ተካፋዮች እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከእነዚህ የብልጽግና አክቲቪስቶችና ደጋፊዎች መካካል አንዳንዶቹ ከውጭ አገር የመጡ ናቸው።

ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ወይም ወረዳዎች ተጠርንፈው በኪራይ አውቶብሶች ወደ ቦታው የተወሰዱ የብልጽግና ደጋፊዎችም አደባባዩ ጢም ይል ዘንድ ታዳሚዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል። መሰሎቻቸውም ከየክልሉ ተጠርተው መታደማቸውም ግልጽ ነው። በመስቀል አደባባዩ በዓለ ሲመት የስምንት አፍሪካ አገራት ተወካዮችም ተገኝተዋል። ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያና ደቡብ ሱዳን በመሪዎቻቸው ሲወከሉ አልጀሪያ በውጭ ጉዳይ ኃላፊዋ ተወክላለች። ከነዚህ መሪዎች በበዓለ ሲመቱ መገኘት ይልቅ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አለመገኘትና ሌላው ቢቀር ኤርትራ በሌላ ባለሥልጣኗ አለመወከሏ የበለጠ አነጋጋሪ ሆኖ ነበረ። በእርግጥ ኤሪቲቪ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኤርትራ ሕዝብ ስም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደስታ መግለጫ መልዕክት መላካቸውን ዘግቧል።

ቀን ላይ በመስቀል አደባባይ የጀመረው ፌሽታ ምሽቱንም ቀጥሏል። የማታው ፌሽታ የተካሄደበት የቀድሞው አውሮፕላን ማረፊያ የአሁኑ ጦር ኃይሎች ግቢ ነበረና፣ ከሁሉም አቅጣጫዎች ወደ ጦር ኃይሎች የሚያመሩ መንገዶች ያለ አማራጭ መንገድ ተዘጋግተው ስለነበረ የሥራ ሰዓታቸውን ጨርሰው ከየሥራ ቦታቸው የወጡ አዲስ አበቤዎች በተሸከርካሪዎች ተጉዘውም ሆነ በእግራቸው እየኳተኑ ወደየቤታቸው የደረሱት ከምሽቱ ሦስት ሰዓትና ከዚያ በኋላ ነው። የታክሲዎችና የባጃጆች መሳፈሪያ ዋጋ ከብር 50 እስከ 200 ደርሶ ስለነበረ፣ ለብዙ አዲስ አበቤ የመንግሥት ሠራተኞች በሰርቪሰ አውቶብሶች ውስጥ ሦስትና አራት ሰዓታትን የወሰደ የቅማል ጉዞ ማድረግ ወይም በእግር መጓዝ ግዴታቸው ሆኖ ነበረ። የበዓለ ሲመቱ ቀን አዲስ አበቤው የአንድ ቀን መብቱን የተነጠቀበት፣ የተረሳበትና የራስህ ጉዳይ ተብሎ ለድካምና ለገንዘብ ኪሳራ የተዳረገበት ቀን እንደሆነ ተሰምቶት ይሆን? መልሱ አዎ የሚል ከሆነ፣ ኧረ ከዚህ በባሰ ሁኔታ በአምስት ዓመት አንዴ ብቻ የሚገኝ መብታቸውን የተነጠቁ ሕዝቦች አሉ ብለን ፖለቲካዊ ሐሜት እንቀጥል።

ያም ሆነ ይህ በመስከረም 24ቱ በዓለ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚ/ሩ የኢትዮጵያ ገዥ ሆኑ ተብሎ በይፋ ታውጇል። ጠቅላዩ ራሳቸውም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዕውነተኛ ምርጫ የተመረጡ የአገር መሪ መሆናቸውን ተናግረው፣ ሹመታቸው ልዩ መሆኑን አውጀዋል። ነገር ግን፣ ይህ ሹመት ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረዥም ጊዜ ከወሎው መርሳ እስከ ትግራዩ ዛላንበሳ፣ ከወሎው ላሊበላ እስከ ጎንደሩ አድርቃይ፣ ከምስራቅ ትግራዩ ኢሮብ እስከ ምዕራብ ትግራዩ ሸራሮ፣ ከአልፋሽጋ እስከ ቋራ መዳረሻ ሥልጣን ያለው አይደለም። ከዚህ ሌላ ከምዕራብ ወለጋ እስከ ቤኒሻንጉል ባለው ቦታ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ያለው መንግሥት አይደለም። 110 ሚሊዮን ነው ከሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ምን ያህሉ ይሆን በነዚህ ቦታዎች የሚኖረውና ከጠቅላይ ሚ/ሩ እጅ ወጥቶ በህወሓትና በሱዳን እየተገዛ ያለው? ምን ያህሉ ሕዝብስ ነው መንግሥት እንደ ሰማይ ርቆበት የኦሮሞና የጉምዝ ነጻ አውጭ ነን በሚሉ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር የሚገኘውና እያለፈና እያገደመ አበሳውን እየበላ ያለው? የነዚህ ጥያቄዎች መልስ በዓለ ሲመቱ ምን ያህሉን ሕዝብ መሪ አሳጥቶታል ለሚለው ሌላ ጥያቄ መልስ ይሆናል።

ምርጫ ቦርድ አሸናፊው ፓርቲ ብልጽግና መሆኑን አሳውቋል፡፡ ምርጫ ሳይካሄድባቸው በቀሩትም ሆነ ምርጫው ዘግይቶ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኘው የምርጫ ውጤት ለውጥ አያመጣምና ብልጽግና መንግሥት መመስረት ይችላል ብሎ ሰጠው በተባለው ፈቃድ መሠረት በዓለ ሲመቱ መካሄዱ የታወቀ ነው። ነገር ግን፣ ምርጫ ቦርድ በነዚህ ምርጫ ባልተካሄደባቸውና የምርጫ ውጤታቸው ዘግይቶ በተገለጸባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ከሚወክሉት የብልጽግና ተመራጮች መካከል ጠቅላይ ሚ/ር ለማሳጨትና ለማስመረጥ ያለውን መብት የቀማ ሕገ-ወጥ አካሄድን መከተሉ ሊካድ አይገባም። ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ የነዚህ አካባቢዎች ሕዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትርነትም ሆነ ለሚኒስትርነት ለታጩ ሰዎች በተወካዮቹ አማካይነት የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጽ የመስጠት መብቱን እንዳይጠቀም ማድረጉ ትንሽ ስህተት አይደለም። እነዚህ ከመንግሥት ምስረታ ተሳትፎ ውጭ እንዲሆኑ በምርጫ ቦርድ የተፈረደባው ሕዝቦች ለኹለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤ የማሳጨት፣ ለአፈ-ጉባኤነት ለታጩት ሰዎችም የተቃውሞና ድጋፍ ድምጽ የመስጠት መብታቸውን የተገፈፉ መሆኑም ሌላው ሊረሳ የማይገባው ነጥብ ነው። ምርጫ ቦርድ የብልጽግና የፖለቲካ ‘ባህል’ ከኢሕአዴግ የተወረሰ ነው፤ በሕይወት ያለ ጠቅላይ ሚኒስትርን በሌላ መተካት የማይታሰብ ነው፤ በኢሕአዴግ ባህል መሰረት ጠቅላይ ሚ/ር ፈላጭ ቆራጭና በፓርላማ ድራማ ተጀቡኖ ሁሉንም ነገር ለመወሰን መብት ያለው ብቸኛው ሰው ነው፤ በሚል እሳቤ ይህን ስህተት ሰርቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።

አንዳንድ ሰዎች ምርጫው ጥርስ ያለው ፓርላማ ለመመስረት እንደሚያስችል፣ ሌላው ቢቀር ብልጽግና ቢያሸነፍ እንኳ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ከዐቢይ አሕመድና የሶማሌ ክልል መሪ ከሆኑት ከሙስጠፌ ለአገሪቱ የተሻለ መሪ የሚሆነውና ሠላም ለማስፈን የሚበጀው ማን ነው በሚል የጦፈ ክርክር ሊገጥሙ እንደሚችሉ ተገምቶ ስለነበረ፣ የሶማሌ ክልል ተወካዮች ሳይታወቁና በቦታው ሳይገኙ የመንግሥት ምስረታ መካሄዱን በአሉታ ተመልክተውታል።

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መጠነ ሰፊ የእስራት ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ሠፊ ሕዝባዊ ቅቡልነት አላቸው የሚባሉ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ቡድን አመራሮች ታስረዋል። በኦሮሚያ ምድር በሚካሄደው ምርጫ ግዙፍ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኦፌኮ አመራሮቹን ጨምሮ በሺሕ የሚቆጠሩ አባላቱ መታሰራቸውንና ፓርቲው ከከፈታቸው 206 ቢሮዎች 203ቱ መዘጋታቸውን እየጠቀሰ ማማረሩ፣ ሌላው የኦሮሚያ ክልል ተፎካካሪ ይሆናል ሲባል የነበረው ኦነግ በመንግሥት ሴራ እየተሰነጣጠቅሁ ነው ብሎ እሮሮ እያሰማ መሰንበቱና የመሳሉት ጉዳዮች በምርጫ ቦርድ እንደ ኢምንት ጉዳዮች ተደርገው መታየታቸውና ቦርዱ በኦሮሚያ ክልል ፍትሐዊ ምርጫ አካሂጃለሁ ብሎ መኮፈሱ ትዝብት ላይ የጣለው ጉዳይ ነው። ምርጫ ቦርድ ክስ ተመስርቶባቸዋል በሚል ሰበብ በገፍ ስለታሰሩት ፖለቲከኞቹ ደንታ ቢስ ቢሆንም፣ የብልጽግና ዘመን እስራት ከህወሓት ዘመኑ እስራት የተለየ ነውን ብሎ ለመገምገም ፍላጎት አለማሳየቱ ሕዝብ አማራጭ እንዲያጣ አድርጓል ብለው ቅሬታ የሚያሰሙ ጥቂት ያልሆኑ ወገኖች እንዲኖሩ አድርጓል።

የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫ ቦርድ ራሱን በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ከነበረው ምርጫ ቦርድ የተሻልኩ ነኝ፣ የተሻለ ሥራ ሠርቻለሁ ብሎ ስለሚኮፈስ የብልጽግና ዘመን ምርጫ ውጤት ከህወሓት ዘመኑ የምርጫ ውጤት የተለየ ያልሆነው ለምንድን ነው ብሎ ከምርጫው ዋዜማ እስከ ምርጫው መባቻ የነበረውን አካሄድ እንዲሁም ራሱን ለመገምገም ፈቃደኛ ከመሆን ይልቅ “፣…ቀድሞውንም ወደ ሥራው ስንገባ ጥሩ ሥራ ብንሠራም ከሐሜት አናመልጥም ብለን ነበረ…” ብሎ ግድ የለሽነት በማሳየቱ ቦርዱ ለሕዝብም ሆነ ለዲሞክራሲ ብዙም ግድ የሌለው ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል።

ምርጫ ቦርድ ራሱንም ሆነ ምርጫውን ለመገምገም ግድ የሚሉት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ኹለቱ ጉልህና ወሳኝ ናቸውና ችላ ሊላቸው አይገባም። አንዱ ምክንያት አገሪቱ አይታው በማታውቅ መልኩ ዝርክርክ በሆነና መያዣና መጨበጫው በማይታወቅ የአስተዳር ሥርዓት ውስጥ የከተታት ብልጽግና በገፍ መመረጡ ሲሆን፣ ሌላው ምክንያት ደግሞ ቀድሞ በኢሕአዴግ ስም ተሰልፈው ሕዝብን የጎዱትና የጠቀሙት ፖለቲከኞችና ካድሬዎች በብልጽግና ስም ተጀቡነው ከክልል እስከ ፌደራሉ ያለውን ወንበር በጅምላ በሙሉ በሚባል መጠን መቆጣጠራቸው ግራ አጋቢ መሆኑ ነው። አዎ! እነዚህ ጉዳዮች ምርጫ ቦርድ ሌላው ቢቀር ምርጫውን መገምገም እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ናቸው። ሠላም የጠፋባቸው አካባቢዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያችን በብዙ አካባቢዎች ከተራ ግጭት እስከ ሙሉ ጦርነት የምታስተናግድ አገር ሆናለች። ሕልውናዋ አደጋ ላይ ነው። ሰላም መታጣቱ ሳያንስ የኑሮ ውድነቱና ድኅነቱ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ነው። ከተወለዱበት ‘ክልል’ ውጭ መኖር ከመቼውም ጊዜ በባሰ ደረጃ አደገኛ ሆኗል። አገሪቱ በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ውድቀት ላይ ከመሆኗ በላይ ከኃያላኑ ጋር ያላት ግንኙነት አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ገብቷል። ለእነዚህና ለሌሎች ውድቀቶች ዋና ተጠያቂ የሆነው ብልጽግና በገፍ መመረጡ ‘የዚህ ምርጫ ችግር ምን ላይ ነው?’ ብሎ ለመጠየቅ የግድ የሚል ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ አይመለከተኝም ከማለት አልፎ ስኬታማ ሥራ ሠርቻለሁ ብሎ በመኩራራት ላይ ይገኛል። ምርጫ ቦርድ ውሸትና ስድብ የብልጽግና ቡድንና የአክቲቪስቶቹ ፖለቲካዊ ባህል እየሆነ መምጣቱን በሚገባ ያያልና ምን አገባኝ ባይነቱ ትዝብት ላይ የሚጥለው ነው፡፡

ግዛቸው አበበን በአድራሻቸው gizachewabe@gmail.comማግኘት ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com