የእለት ዜና

የተራዘመ ጦርነት እና የተባባሰው የሕዝብ ችግር

መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነት፣ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው 18 ቀናት ይቀሩታል። ጦርነቱ የተጀመረው ጥቅምት 24/2013 በትግራይ ክልል ይሁን እንጅ ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የትግራይ አጎራባች ወደሆኑት አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተጀመረው ጦርነት ለስምንት ወራት፣ በትግራይ ክልል ተወስኖ ቢቆይም በትግራይ ክልል ከሕወሓት ጋር ውጊያ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰኔ 21/2013 ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ነበር ሕወሓት በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ጥቃት ማድረስ የጀመረው። ሕወሓት በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ጥቃት ሲፈጽም የፌደራል መንግሥት “የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ ነኝ” በማለት ሕወሓትን ሊገዳደር ወይም ወደ ኹለቱ ክልሎች ዘልቆ እንዳይገባ የመከላከል ሥራ አለመስራቱ ሲገለጽ ነበር።

የፌደራል መንግሥት መካላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ያስወጣው “የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ አውጃለሁ” በማለት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ሕወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚያደርሰው ጥቃት መባባሱን ተከትሎ፣ የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ማንሳቱን የፌደራል መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ማንሳቱን ቢገልጽም፣ ሕወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖችን ፣እንዲሁም በአፋር ክልል ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ሲሰነዝር ማስቆም አልቻለም። ሕወሓት የተቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል አካባቢዎችን እንደለቀቀ ቢገለጽም፣ ባለፈው ማክሰኞ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ስድስት የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ መንግሥስት ገልጿል።

መከላከያ ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ከኹለት ወራት በላይ መስቆጠሩን ተከትሎ፣ ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ችግሮች ተባብሰው እንደቀጠሉ አዲስ ማለዳ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ እየተከታተለች በሰራቻቸው ዘገባዎች ላይ መገለጹ የሚታወስ ነው።

በተለይ ሕወሓት በተቆጣጠራቸው በሰሜን ጎንደር፣ በዋግምህራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜን ወሎ ዞኖች የንጹሐን ዜጎች ግድያ፣ አፈና፣ የሴቶች መደፈር፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ እንዲሁም የረሃብ ችግር መከሰቱን በተደጋጋሚ ሲገለጽ የነበረ ጉዳይ ነው። አዲስ ማለዳም ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ያለውን በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ችግር ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።

ሕወሓት በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ረሃብ ተከስቶ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ ቢሆንም፣ ረሃብ ለተደቀነባቸው ንጹሀን ዜጎች የምግብ እርዳታ ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው። የምግብ ድጋፉ በዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በኩል እንዲቀርብ ለማድረግ መንግሥት ሁኔታዎችን አመቻችቶ ድጋፉ እየተደረገ ነው ተብሏል።

ይሁን እንጅ ረሃብ ለተጋረጠባቸው ዜጎች የተላከውን የምግብ አቅርቦት ሕወሓት እየተጠቀመበት እና የእርዳታ መጋዘኖችን እየዘረፈ መሆኑ ተገልጿል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ንጹሐን ዜጎች፣ አሁንም በችግር ላይ መሆናቸው እየተገለጸ ነው። ድጋፍ አድራጊ አካላት ወደ አካባቢው የሚልኩት ድጋፍ ጦርነት እየተካሄደ ባለባቸው እና ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ተደራሽ መሆን እንዳልቻለም እየተነገረ ነው።

የሰሜኑ ጦርነት ገና ከጅምሩ፣ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ እና የተራዘመ ጦርነት እንዳይሆን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሙያዎች ሲወተውቱ እንደነበር የሚታወስ ነው። አዲስ ማለዳም በጦርነቱ ላይ የሚያጠነጥኑ ዘገባዎችን በሰራችበት ጊዜ በተለይ ወታደራዊ ባለሙያዎች ጦርነቱ የተራዘመ ከሆነ ውስብስብ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉ እና ጦርነቱ ከመነሻው አልፎ ሌሎች ክልሎችን ማጣቀሱ አሁን ላይ ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ወታደራዊ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የጦርነቱ መራዘም ለጦርነቱ መስፋፋትና ላስከተላቸው ችግሮች መነሻ መሆኑን የሚገልጹት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማኀበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ ናቸው።

በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ዘልቆ የገባው ሕወሓት በያዛቸው አካባቢዎች የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም መንግሥት እስካሁን በአፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዱ የዜጎችን ሕይወት ከእለት እለት እየፈተነው ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሮችን ሰብል ሰብስቦ ወደ ትግራይ ለመውሰድ ዘመቻ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ሕወሓት የደረሱ ሰብሎችን ሰብስቦ ወደ ትግራይ ለመውሰድ የተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙት እንደ ራያ ቆቦ ያሉ አካባቢዎች እና በዋግምህራ ዞን የሚገኙ አካባቢዎች ይገኙበታል። አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት እትሟ ሕወሓት ከሰሜን ወሎ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ሰብስበው እንዲወስዱ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጥሪ ማቅረቡን ዘግባ ነበር። ይህ ድርጊት በዋግህምራ ዞን በሚገኙ አካባቢዎች እየተደገመ መሆኑን አዲስ ማለዳ በዞኑ ቆይተው በቅርቡ ከተፈናቀሉ ሰዎች ሰምታለች።

አሁን ላይ የሚታየው ችግር ተባብሶ በመቀጠሉ መንግሥት ዜጎችን ከተራዘመ ችግር እና ከሞት ለመታደግ አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ታመነ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል። ሻላቃው እንደሚሉት ከሆነ፣ መንግሥት እስካሁን ዜጎችን ከችግር ሊያስወጣ የሚችል እርምጃ በሕወሓት ላይ ያልወሰደው፣ በአንድ ጊዜ የሚቋጭ የውጊያ ኦፕሬሽን ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያመላክት ወታደራዊ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

ሻለቃው፣ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ይመስላል ያሉት፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተፈጠረው ስህተት፣ ጦርነቱን እንዲስፋፋ እና የተራዘመ ጦርነት እንዲሆን የተፈጠረበት ሁኔታ ዳግመኛ እንዳይፈጠር በማሰብ ጦርነቱን በአንድ ጊዜ ለመጨረሽ እየተዘጋጀ ሊሆን እንደሚችል ወታደራዊ ግምታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ፣ በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ላይ የሚደርሰው የረሃብ፣ የግድያ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ በመሆኑ፣ መንግሥት በአፋጣኝ አርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ሊታደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግሥት ጦርነቱን በአፋጣኝ አጠናቆ ዜጎችን መታደግ ካልቻለ ዜጎችን ከጦርነት ቀጠና የሚያወጣበት ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል።

ዜጎችን ካሉበት ችግር ለማውጣት ያማያዳግምና አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ ባለሙያው እንደ ኹለተኛ አማራጭ ያስቀመጡት መፍትሔ፣ ዜጎችን ከጦርነት ቀጠና ማውጣት የሚቻልበትን ስልት መፍጠርና እንዲወጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል። “መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ካልቻለ፣ በውጊያ ቀጠና ያሉ ዜጎችን ማዳን የሚችልበትን ሁኔታ ማሰብ አለበት” ሲሉ ሻለቃው አማራጭ ሀሳብ አቅርበዋል።

ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ቀድሞውኑ ጥቃት ሲደርስባቸው መከላከያ ደጀን ሆኖ ከጦርነት ቀጠና ሊያወጣቸው ባለመቻሉ የተፈጠረ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ አሁንም ቢሆን መከላከያ የሚጠብቀውን ሕዝብ ጦርነት ቀጠና ላይ ትቶ መንቀሳቀስ እንደሌለበት ጠቁመዋል።

መንግሥት በጦርነቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የማያዳግሙ መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁሙት ባለሙያው፣ ይህ ሲባል ግን “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” የሚባለው አባባል እንዳያጋጥም ጥንቃቄ እንደሚሻ አመላክተዋል።
ለሰሜኑ ጦርነት እልባት መስጠት የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን እና ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ፣ እንዲሁም የተራዘመ ጦርነት እንዳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በፖለቲካ ባለሙያዎች ገና ከጅምሩ ቢገለፁም ጦርነቱ የተራዘመ መሆኑ አልቀረም።
የጦርነቱ መራዘም ያስከተለውን ችግር በዋነነት በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ላይ የበረታ ቢሆንም፣ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ላይ ተጽኖ እንደፈጠረ ይገለጻል። ጦርነቱ ከፈጠራቸው ተጽእኖዎች መካከል፣ ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ የጸጥታ ችግር ያለባቸው ሌሎች አካባቢዎች ትኩረት እንዲነፈጋቸው እንዳደረገ ይነገራል።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል እና ካማሺ ዞን ያለው የጸጥታ ችግር፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የመንግሥትን የኃይል ሚዛን ለማዛባት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ሻለቃ ታመነ ይገልጻሉ። መንግሥት ዝንባሌውን ወደ ሰሜኑ ጦርነት ማደረጉን ተከትሎ፣ በሌሎች አካባቢዎች የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር ክልሎች ትኩረት ሰጥተው ሊከላከሉ እንደሚገባ ሻለቃው ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እንደተከሰተው ቦታው በተደጋጋሚ ንጹሐን ዜጎች የሚገደሉበት አካባቢ ቢሆንም፣ ዜጎችን ከሞት የሚታደግ መፍትሔ አልተገኘም። እንደ ሻለቃው ገለጻ ከሆነ፣ በምስራቅ ወለጋ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ችግሩን ለማስቀረት ፈቃደኛ ካለመሆኑ የመነጨ ካልሆነ፣ ጥቃት የሚፈጸመው ታጣቂ ቡድን ከክልሉ ልዩ ኃይል አቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።

በመሆኑም፣ የክልሉ መንግሥት ንጹሐን ዜጎችን ለጥቃት ለመታደግ ከቸልተንነት በጸዳ አሰራር ችግሩን ሊያስቆም እንደሚገባ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም የማይከላከል ከሆነ፣ ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ጋር የሚተባበሩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ቀዳዳዎችን ክልሎች ያላቸውን የጸጥታ ኃይል ተጠቅመው መከላከል እንዳለባቸው ባለሙያው ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!