የእለት ዜና

በአንድ ቢሊዮን ብር በአዲስ አበባ የተገነባው “ኃይሌ ግራንድ” ሆቴል ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው

በአንድ ቢሊዮን ብር በአዲስ አበባ የተገነባው ኃይሌ ግራንድ የተሰኘ የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ፣ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ “ኃይሌ ግራንድ” በሚባል ስያሜ ያስገነባው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን የኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት መልካሙ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የሆቴሉን ሙሉ ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግም አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ይፈጃል ብለዋል። ዳይሬክትሩ አክለውም፣ ሆቴሉ ባለ አስር ፎቅ ሲሆን፣ እንደ ሌሎች የኃይሌ ሪዞርቶች ሁሉ ደረጃውን የጠበቀ እና ከ10 ሺሕ ካሬ ሜትር በሚበልጥ ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ሆቴሉ የተገነባው የድሮው ኮረብታማ ሆቴል የነበረበትን ቦታ በመግዛት መሆኑንና ይበልጥ ለማስፋት ከመንግሥት ተጨማሪ ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተጠይቆ በሂደት ላይ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ሆቴሉ በውስጥ የተለያዩ መገልገያዎችን የያዘ ነው የተባለ ሲሆን፣ መዋኛ ገንዳ፣ ሜዳ ቴነስ፣ ጂም ቤት፣ ዲኤስ ቲቪ ቤት፣ ጸጉር ቤት፣ እንዲሁም የወንዶችና የሴቶች ስቲም አለው።

እስከ አንድ ሺሕ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ኹለት ትላልቅ የመሰብሠቢያ አዳራሾች፣ ሌሎች ስድስት መለስተኛ አዳራሾች እንዲሁም ምድር ቤት ጭምር ያለው መኪና ማቆሚያ አካቷል። ሰፊ ባር እና ባለ ኹለት ፎቅ ስፓ ከመያዙም ሌላ፣ ተፈጥሯዊ ወብትን የሚገልጽ የአትክልት እና የፏፏቴ ቦታም እንዳካተተ ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም፣ ከ160 በላይ የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በተለይ አስረኛ ፎቅ ላይ ያሉት ደግሞ የራሳቸው ሳሎን እና ኪችን ያላቸው ለቤተስብ እንደመኖሪያነት የሚያገለግሉ አፓርትመንቶች ናቸው።
ኃይሌ ግራንድ ሆቴል ከቅንጡ ሆቴሎች የሚመደብ እና የተገነባበት ቦታ ከፍታማነት ከተማዋን በሁሉም አቅጣጫ ለማየት የሚያመች ነው ሲሉ መልካሙ መኮንን አክለው ተናግረዋል።

ግንባታውን ‹ኤስ ኤ› የሚባል ደረጃ አንድ የአገር ውስጥ ተቋራጭ ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ በማጠናቀቅ ያስረከበ መሆኑ፣ እና አሁን ላይ በኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ድርጅት ሠራተኞች የማስዋብ እና የማጠናቀቅ ስራ (finishing work) ብቻ እንደሚቀረው ተገልጿል። እንዲሁም በቅርብ ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ነው የተገለጸው።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ አዲስ አበባ ዙሪያ ሱሉልታ ከሚገኘው ያያ ቪሌጅ ቀጥሎ አዲስ አበባ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስገነባው ሆቴል ነውም ተብሏል።

አዲስ አበባ ውስጥ እየተገነባ ያለው ኃይሌ ግራንድ ሆቴል፣ በሌሎች ከተሞች ከሚገኙ የኃይሌ ሪዞርቶች በከፍታው እና በስፋቱ የሚልቅ ሲሆን፣ ከኃይሌ ሪዞርቶች ውስጥ ብቸኛው ባለ አምስት ኮክብ ሆቴል እንዲሁም የኃይሌን ሙዚየም የያዘ እንደሆነም ነው የተገለጸው። ለግንባታ ጥራት ሲባልም አብዛኞቹ የግንባታ ቁሳቁሶች ከውጭ አገር የሚገቡ ናቸው ተብሏል።

ሆቴሉ ለኹሉም የማኅበረስብ ክፍል አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በተለይ ግን ስብሠባዎችን፣ ቅንጡ ዝግጅቶችና መስተንግዶዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።
ኃይሌ ግራንድ ሥራው ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር እስከ ሦስት መቶ አምሳ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።

በመጨረሻም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የመጀመሪያውን ሪዞርት 2010 ላይ በሐዋሳ ከከፈተ ጀምሮ፣ በጎንደር፣ ሱሉልታ፣ አዳማ፣ አርባ ምንጭ፣ ሻሼመኔ እና ዝዋይ ከተሞች በአጠቃላይ ወደ ሰባት የሚሆኑ ሪዞርቶችን የከፈተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ የሚያሰገነባው ኃይሌ ግራንድን ጨምሮ በደብረ ብርሃን፣ ወላይታ ሶዶ እና ኮንሶ ከተሞች ሌሎች ሪዞርቶችን እያስገነባ እንደሚገኝ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com