የእለት ዜና

በትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ ለነበሩ ተፈናቃይ መምህራን ደሞዝ መክፈል ተጀመረ

ደሞዛቸው ተቋርጦባቸው የነበሩ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስዎች ውስጥ ሲያስተምሩ ከነበሩ መምህራን መካከል፣ የራያ እና መቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን ደሞዝ አንደተከፈላቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ የትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ላለፉት ኹለትና ከዚያበላይ ለሆኑ ወራት ደሞዝ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። መምህራኑ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተው እስካሁን ያልተከፈላቸውን የወር ደሞዝ መከፈል መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙት የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች አራት ሲሆኑ፣ ራያ፣ መቐለ፣ አክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርስቲዎች ናቸው። የአራቱም ዩኒቨርስቲ መምህራን የወር ደሞዝ ባለፉት የክረምት ወራት ሳይከፈላቸው ቢቆይም፣ የራያ ዩኒቨርስቲ መምህራን የሦስት ወር ማለትም ከሰኔ/2013 እስከ ነሐሴ 2014 ደሞዝ የተከፈላቸው ሲሆን፣ የመቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን ደግሞ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ/2014 የኹለት ወር ደሞዝ ተከፍሏቸዋል። የወር ደሞዝ ከፍያው የተቋረጠው በአራቱም ዩኒቨርስቲዎች ቢሆንም፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የአክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሰቲ መምህራን የተቋረጠባቸው ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው እና በሒደት ላይ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

ዩኒቨርስቲዎቹን በበላይነት ሲያስተዳደር የነበረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከመስከረም ወር ጀምሮ መምህራን በአካል በመገኘት አቴንዳንስ ትፈርማላችሁ እንደተባሉ መምህራኑ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ደሞዝ የተከፈላቸው መምህራን የመስከረም ወር ግን ገና እንዳልተከፈላቸው ጠቁመዋል።

የተቋረጣባቸው ደሞዝ የተከፈላቸው የራያ እና መቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የጠየቃቸውን ማስረጃዎችና መስፈርቶች ቀድመው በማሟላታቸው መሆኑ ተገልጿል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጠየቀውን ማስረጃና መስፈርት ያላሟሉ የኹለቱ ዩኒቨርስቲ መምህራን ግን ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ተጠቁሟል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለመምህራኑ ደሞዝ ለመክፈል ከጠየቃቸው መስፈርቶች መካከል፣ እስካሁን ከሚያስተምሩበት ዩኒቨርስቲ ደሞዝ ሲከፈላቸው የቆዩ መሆኑን የሚረጋግጥ የባንክ ሪፖርት፣ የሚሰሩበት ዩኒቨርስቲ ቋሚ ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ድብዳቤ ማለትም ከዩኒቨርስቲው የተሰጣቸውን የደረጃ ምደባ (ጂኤጅ) ደብዳቤ እና የሠራተኛነት መታወቂያ ማቅረብ ናቸው።

ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መምህራኑ የባንክ ሪፖርት እና ከሚሠሩበት ዩኒቨርስቲ አለመልቀቃቸውን የሚረጋግጥ የቋሚ ሰራተኛ ደረጃ ምደባ ደብዳቤ የጠየቀው በሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ወይም ሥራ ቀይረው ከዩኒቨርስቲው ደሞዝ እንዳይቀበሉ ለማረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል።

የተቋረጠባቸው ደሞዝ ያልተከፈላቸው የአክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን እየጠየቁ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ካሟሉ ደመወዛቸው እንደሚከፈላቸው ይጠበቃል።
በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት አሁንም ድረስ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የዩኒቨርስቲዎቹ መምህራን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊታወቅ አለመቻሉን መምህራኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ደሞዝ የተከፈላቸውም ይሁን ያልተከፈላቸው መምህራን በሌላ ሥራ እንዳይሰማሩ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ አቅርበው “አይቻልም” መባላቸውን ተናግረዋል። የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በውል ያላወቁት መምህራኑ ችግራችን መፍትሔ ማግኘት አለበት ብለዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በጦርነቱ ምክንያት መዘጋታቸውን ተከትሎ መምህራን ብቻ ሳይሆኑ፣ በዩኒቨርስቲዎቹ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ቢቀመጡም እስካሁን ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት መፍትሔ እንዳልተገኘላቸው አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ለተማሪዎቹ ቢገልጽም፣ እስካሁን የተገኘ አማራጭ የለም ተብሏል። ሌሎች ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ማስመረቃቸው የሚታወስ ነው።

ዩኒቨርስቲዎችን በበላይ ሲመራ የነበረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ በተቋቋመው አደረጃጀት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር የተጠቃለለ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ዩኒቨርስቲዎች ተጠሪነታቸው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሆኑ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!