የእለት ዜና

የንግድ ትርዒት – የአዳዲስ እድሎች አውድ

ዓለማችን የግብይትና የንግድ ትስስር መንገዶችን በየጊዜው በማሻሻል አዳዲስ መንገዶችና አካሄዶችን በተለያየ ጊዜ አስተናግዳለች። በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሁም በአካል ሰዎች የሚገናኙባቸው መድረኮችም በተለያየ ጊዜ ተፈጥረው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ከዚህ መካከል አንደኛው የንግድ ትርዒት ነው።

አገራት በየዘረፉ ለተለያዩ ዓላማዎች የንግድ ትርዒቶችን ያስተናግዳሉ፤ ያካሂዳሉ። ኢትዮጵያም በተለያየ መስክ የአገር ውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ አካላትን ያሳተፉ የንግድ ትርዒቶችን አከናውናለች። እነዚህ የንግድ ትርዒቶች አዳዲስ ሐሳብ የተገኘባቸው፣ አዳዲስ ዕድሎች የተፈጠሩባቸውና በሮች የተከፈቱባቸው ሆነው ያውቃሉ። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ጎብኚዎችም ይሳተፉባቸዋል።

ምንም እንኳ ኮቪድ 19 ወረሽኝ እንዲህ የሰዎች መሰባሰቢያ የሆኑ መድረኮች እንዲዘጉ ቢያደርግም፣ አሁን ላይ ዳግም እንቅስቃሴዎች አንድ ብለው እየጀመሩ ይመስላል። አዲስ ማለዳም ከጥቅምት 4-6/2014 በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተሰናዳው አራተኛው የአግሮፉድ እና የፕላስቲክ ህትመት ማሸጊያ የንግድ ትርዒት ላይ ተሳትፋ ይህን ታዝባለች።

ይህ የንግድ ትርዒት በጀርመኑ የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ፌር ትሬድ እና በኢትዮጵያው ፕራና ኢቨንትስ የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው። ትርዒቱ አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለቱን የሚወክሉ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነውበታል። በዚህም የግብርና፣ የምግብ እና መጠጥ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን፣ የፕላስቲክ ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና መፍትሄዎች ቀርበዋል።

የፕራና ኢቨንትስ መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ለማ የንግድ ትርዒቱ የተዘጋጀበትን ምክንያት ሲያስረዱ አራት ዋና ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ጠቅሰዋል። አንደኛው ባለድርሻ አካላት መካከል የንግድ ትስስርን ማጠናከር ነው። ይህም በአምራችና ተጠቃሚ፣ በአስመጪና አከፋፋይ፣ በውጪ እና በአገር ውስጥ ኩባንያዎች መካከል ያለ ነው።

ሌላው ደግሞ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስተዋወቅ ይረዳል የሚል ሲሆን፣ በሦስተኛነት የጠቀሱት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ አንጻር ያለውን ፋይዳ ነው። በመጨረሻም በዘርፉ ያለውን እውቀትና ግንዛቤ ለማሻሻልና ለማሳደግ፣ እርስ በእርስም መረጃን ለመለዋወጥ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

‹‹በኢትዮጵያ በምግብ ራስን መቻል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው›› ያሉት ነብዩ፣ ይህ የንግድ ትርዒት ሲዘጋጅ አንድም በዚህ በምግብ ራስን የመቻል ጥረት ውስጥ በቴክኖሎጂ፣ በአስፈላጊ ግብዓት እንዲሁም በመፍትሔ ሐሳቦች ለማገዝ በማለም ነው ብለዋል።
የንግድ ትርዒቱ መዘጋጀት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ (እአአ 2017)፣ አንድ ዓመት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ ከመቅረቱ በቀር፣ በተከታታይ በነበረው ሂደት ለውጦች እንደታዩ ነብዩ ተናግረዋል። እንዲህ ያሉ ክዋኔዎች ከግብርና ምርት ጋር በተያያዘ በጎ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችል እድል እንደሆነም ጠቁመዋል። ለኢትዮጵያም ትልቅ እድል እንደሆነ አንስተው፣ ክዋኔው በምሥራቅ አፍሪካ በዘርፉ የሚካሄድ ግዙፍ የሚባል ትርዒት ነው ሲሉ አክለዋል።

ሔኖክ መስፍን በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብርና ንግድ እና የገበያ ልማት ዳይሬክተር ናቸው። በበኩላቸው እንዲህ ያሉ የንግድ ትርዒቶች በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ።

አያይዘውም ‹‹ኢትዮጵያ በመሬት፣ በውሃና በሰው ኃይል ከፍተኛ ሀብት አላት። ነገር ግን በሚገባው ልክ እየተጠቀምን አይደለም። እንዲህ ያሉ ክዋኔዎች ሲኖሩ ቴክኖሎጂ ለማስገባት እድል ይሰጠናል። እንዲሁም ያለውን አቅም ባለሀብቶች ዐይተው፣ መጥተው ኢንቨስት ያደርጋሉ። በዚህም ለአርሶ አደሩ የተሻለ ገበያ ይፈጥራሉ።›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ከውጪ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምግብና መጠጦች ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚወጣ ያወሱት ሔኖክ፣ እነዚህ ግን በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በንግድ ትርዒቶች በሚፈጠሩ አዳዲስ እድሎችና ዕይታዎች ታድያ የውጪ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ከውጪ የሚገቡ የታሸጉ የግብርና ውጤት የሆኑ ምግብና መጠጦችን በአገር ውስጥ አምርቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ፣ አልፎም ወደ ውጪ በመላክ ገቢ ለማምጣት እንደሚያስችሉ አንስተዋል።

ለዛም ግን እነዚህ በንግድ ትርዒት ላይ የሚታዩና የሚቀርቡ ሐሳቦችና አዳዲስ መንገዶች በተግባር ወርዶ ሊሠራባቸው እንደሚገባ እሙን ነው። ለግብርና ትኩረት የምትሰጠው ኢትዮጵያም እንዲህ ያሉ መንገዶችን ያለማንገራገር ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ መፍትሔ አመንጪነት ልትቀይራቸው እንደሚገባ ሁሉም ይስማማሉ።

ከጥቅምት 4-6/2014 በስካይላይት ሆቴል በተካሄደው በዚህ የንግድ ትርዒት ከአስራ አንድ አገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከፈርንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከጣሊያን፣ ከኩዌት፣ ከናይጄሪያ፣ ከሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ከቱርክ እና ከአሜሪካ የተውጣጡ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com