የእለት ዜና

በወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያዎች ላይ አስገዳጅ ደረጃዎች ጸደቁ

የሽሮ፣ በርበሬ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ጠጅ እና አረቄ አስገዳጅ ደረጃዎችም ለመጀመሪያ ጊዜ በምክር ቤቱ ቀርበው ጸድቀዋል

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ምክር ቤት መስከረም 20/2014 ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው በምግብና የግብርና ውጤቶች ዘርፍ፤ የወተት እና የወተት ተዎጽኦ ማቀነባበሪያዎች ላይ 14 አዲስ፣ 17 በክለሳ፣ እንዲሁም 4 አስገዳጅ ደረጃዎችን ማጽደቁ ተገለፀ።

ምክር ቤቱ የምግብና ግብርና ዘርፍን ጨምሮ፤ በ7 ዘርፎች ላይ 332 አዲስ፣ 190 የተከለሱ እንዲሁም 184 በነበሩበት የቀጠሉ በድምሩ 706 ደረጃዎች ላይ የመጨረሻ ረቂቆች ቀርበውለት ሁሉንም ደረጃዎች መርምሮ ማጽደቁን የኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር ይልማ መንግስቱ አስታውቀዋል።

ከጸደቁት ደረጃዎች ውስጥ በምግብና ግብርና ዘርፍ ውስጥ የሚገኘው የወተት እና የወተት ተዋጽኦዎች ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የጸደቀው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በ1994 ሲሆን፣ ደረጃውም በፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ እንዲተገበር ተወስኖ የጸደቀ ነበረ።

“በአሁን ሰዓት በአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ በሚውለው ወተት ላይ ሕብረተሰቡ አራት ዓይነት ፍላጎቶች አሉት” ያሉት ይልማ፣ እነሱም ጥሬ ወተት፣ በማቀነባበሪያ የተቀነባበረ ፓስቸራይዝድ ወተት፣ የዱቄት ወተት እንዲሁም የፈላ ወተት ወይንም (UHT) መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

እነዚህ አስገዳጅ ደረጃዎች መጽደቃቸው፣ በወተት ዕሴት ሰንሠለት ላይ የሚስተዋሉትን አግባብ ያልሆኑ የውኃ መቀላቀል፣ የአያያዝ ጥንቃቄና ንጽህና ጉድለት፣ የማቀነባበር እና የማሸግ ሒደት ጥራት ጉድለትና መሰል የወተት ባህሪን ሊቀይሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ፣ አገራችን ከዘርፉ በጤና፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ረገድ በይበልጥ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሎ በምክር ቤቱ በመታመኑ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ በወተት ግብይት ሥርዓት ውስጥ የጥራት፣ የአቅርቦት አናሳነት፣ የቁጥጥር አቅም ውስንነት፣ የዘርፉ አለማደግ እና በዕሴት ሰንሠለቱ ላይ የግብይት ሥርዓቱ አለመስተካከል እንደችግር የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ይህንንም ለማስተካከል ደረጃውን አስገዳጅ አድርጎ በተጠና መንገድ ቁጥጥር የማከናወን፣ የመኖ ደረጃዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ የማድረግ፣ የግንዛቤና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት፣ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮችን የማስተሳሰር እና የመደገፍ ሥራዎች በኤጀንሲው በመሠራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በምክር ቤቱ የጸደቁት አዲስ አስገዳጅ ደረጃዎችም የወተት ሰብሳቢዎች ወተት ከሚሰበስቡበት ዕቃ ጥራት ጀምሮ፣ እስከ የማመላለሻ ትራንስፖርት ምቹነት፣ የማቀናበር እና የማሸግ ደረጃዎች ጥራት ድረስ የሚያካትት መሆኑንም ነው ይልማ ያስረዱት።

ከዚህ በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ ሲጠኑ ቆይተው ደረጃቸውን በማዘጋጀት ለመጀመሪያ ጊዜ 6 የአገር በቀል ምርቶች ማለትም የሽሮ፣ የበርበሬ፣ የቆሎ፣ የበሶ፣ የጠጅ እና የአረቄ ደረጃዎችም በምክር ቤቱ ቀርበው መጽደቃቸውን የገለጹት ይልማ፤ እስከ አሁንም ድረስ ምርቶቹ አለም ዓቀፍ የንግድ መግባቢያ ስያሜ ስላልነበረቻው ደረጃ ሳይሰጣቸው መቆየቱንም ተናግረዋል።

የእነዚህ አገር በቀል ምርቶች ደረጃዎች መጽደቅ የሕብረተሰቡን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር፣ ምርቶቹ እራሳቸውን ገላጭ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር፣ እንዲሁም የገበያ ትስስር በመፍጠር በአለም ዓቀፍ ደረጃ ምርቶቹ የሚተዋውቁበትን ዕድል ከመፍጠር አንፃር የሚኖራቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑንንም አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በምክር ቤቱ ደረጃቸው ቀርቦ የፀደቀው 7ቱ ዘርፎች የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ የምግብና ግብርና ውጤቶች፣ በመሠረታዊና አጠቃላይ ዘርፎች አዲስ፣ የተከለሱ፣ እንዲሁም የነበሩትን በማስቀጠል ደረጃዎቻቸው የጸደቁ ሲሆን፣ በተጨማሪም በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና 3 አዳዲስ ደረጃዎች፤ በኤሌክትሮ-ሜካኒካል ዘርፍ 2 አዳዲስ ደረጃዎች፣ በጤና ዘርፍ 9 አዳዲስ ደረጃዎችን መርምሮ ማጽደቁንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ደረጃ በማውጣት እና በማጽደቅ በጣም ሀብታም ነች። ነገር ግን የጸደቁትን ደረጃዎች በተግባር በማዋል ላይ ግን ከፍተኛ ችግር ይታይባታል” ያሉት የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦንሳ ባይሳ ናቸው።

ቦንሳ እንደሚሉት ከሆነ፣ ኤጀንሲው የዜጎችን ጤንነትና የአካባቢን ደህንነት ለማስጠበቅ አለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም የቴክኒክ እና የሥልጠና ዕድሎችን በማመቻቸት የአገር ውስጥ ምርቶች አለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በመሥራት ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም፣ ደረጃዎቹ ክህሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ከማበርከታቸው በተጨማሪ ከሕብረተሰቡ ጤናና ደኅንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ የሸማቾችን ጥቅም ከማስጠበቅ፣ እንዲሁም ተቆጣጣሪ አካላት የክትትል ድጋፍ እና ቁጥጥር ተግባራትን ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com