የእለት ዜና

‹ኮላብ ሲስተምስ› በ‹ኢግል ሒልስ› ክህደት ተፈጽሞብኛል ሲል አስታወቀ

ድሮም ዘንድሮም የሚባል የቀደምት (ክላሲክ) መኪናዎች ትዕይንት በማዘጋጀት የሚታወቀው ኮላብ ሲስተምስ ድርጅት፣ በለገሀር ባቡር ጣቢያ ከኢግል ሒልስ ጋር በአጋርነት ሊያዘጋጀው የነበረውን የመኪና ትዕይንት እንዳይካሄድ በማድረግ ኢግል ሒልስ ክህደት ፈጽሞብኛል ሲል ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በኮላብ ሲስተምስ ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው የሚሰሩ እና ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ኹለተኛውን የድሮም ዘንድሮም ትዕይንት በታሪካዊው ለገሀር ግቢ ውስጥ ግንቦት 10/2013 ለማዘጋጀት ቦታውን በጊዜያዊነት ከሚያስተዳድረው ኢግል ሒልስ ኢትዮጵያ ፈቃድ በማግኘት ተጨማሪ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።

ለገሀር የድሮ መኪኖች ከውጭ መጥተው የሚራገፉብት ቦታ ስለነበር በተለይ ለድሮ መኪና ወዳጆች ልዩ ትዝታ ያለው ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ከሌሎች ስፍራዎች በተለየ ትኩረት ሰጥቶ ድርጅታችን ዝግጅቱን ለማድረግ ወስኖ ነበር የሚሉት ግለሰቡ፣ ‹‹ወራትን ከፈጀ ድርድር በኋላ የድርጅታችን ዋና ሐሳብ አስረድተን እና ተማምነን ድርጅታችን በየካቲት 20/2013 በኢሜል ለጠየቀው የአብረን እንሥራ ጥያቄ በመጋቢት 11/2013 ይሁንታውን አሳውቆናል። በይሁንታውም 10 ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላን ድረስ ዝግጅቱን ማዘጋጀት እንደምንችል የሚገልጽ ማረጋገጫ ደብዳቤ ሰጥቶናል›› ሲሉ ነው የተናገሩት።

ሆኖም በ2013 ሚያዚያና ግንቦት ወር በነበረው ከፍተኛ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኮላብ ሲስተምስ የታቀደውን ዝግጅት ለማድረግ ፈቃድ እንደማይሰጥ የገለጸ በመሆኑ፣ ድርጅቱ የቫይረሱ ስርጭት እስከሚቀንስ የዝግጅቱን ቀን ለማራዘም እንደተገደደ ነው የገለጸው።

ይህንንም ለኢግል ሒልስ በኢሜል አሳውቆ፣ ኢግል ሒልስም በሚያዝያ 23/2013 ለኮላብ ሲስተምስ በጻፈው ደብዳቤ ጊዜው ለኹላቸውም ከባድ መሆኑን ገልጾ፣ ነገሮች ሲስተካከሉ ድርጅቱ ወደ ሥራ መመለስ እንደሚችል ቃል ገብቶ ነበር ብለዋል።
ሆኖም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ኮላብ ሲስተምስ በአዲስ ዓመት የመኪና ትዕይንቱን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እያለ፣ ኢግል ሒልስ ከኮላብ ሲስተምስ ጋር ከአምስት ወራት በላይ የተደራደረበትን ዝግጅት ስሙን በመቀየር በተመሳሳይ የፕሮግራም ይዘት በራሱ ሊያዘጋጀው እንደሆነ ኢግል ሒልስ በራሱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ለጥፎ ማየቱን ገልጿል።

ይህም በኮላብ ሲስተምስ ውስጥ ድንጋጤ የፈጠረ፣ የድሮም ዘንድሮም ቤተሰብን እና በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ የድርጅቱ ስፖንሰሮችን ያሳዘነ በመሆኑ፣ ኮላብ ሲስተምስ ከኢግል ሒልስ ተወካዮች ጋር ለመነጋገር ምክሯል። ይሁን እንጅ ኢግል ሂልስ ከኮላብ ሲስተምስ ጋር የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው፣ ዝግጅቱን በራሱ እንደሚያዘጋጀው፣ እንዲሁም ሐሳቡ የራሱ እንደሆነ ገልጿል ሲል ነው ቅሬታ አቅራቢው ለአዲስ ማለዳ ያስረዳው።

ድርጅቱ አክሎም፣ ኢግል ሒልስ የመኪና ፌስቲቫል ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን የኮላብ ሲስተምስን ሃሳብ ሙሉ ዶሴ፣ ማርኬቲንግ ስትራቴጂ፣ የፕሮግራም ዲዛይን እና ዝርዝር ተግባራት ከወሰደ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስነምግባር የጎደለው ተግባር መፈጸም ከትልቅ ተቋም የማይጠበቅ ነው ብሏል።

አዲስ ማለዳ በኮላብ ሲስተምስ በተነሳው ቅሬታ መነሻ በማድረግ ከኢግል ሒልስ ባገኘቸው ምላሽ መሠረት ኢግል ሒልስ በበኩሉ፣ ኮላብ ሲስተምስ የቮልስ ዋገን መኪኖች ትርዒት ሚያዝያ 30/2013 ለማዘጋጀት እንዳሰበ በመግለጽ የድርጅታችንን ቅጥር ግቢ ትርዒቱን ለማቅረብ እንዲጠቀምበት ጥያቄ በማቅረቡ፣ ድርጅታችን መጋቢት 17/2013 በጻፈው ደብዳቤ የተጠቀሰውን የቮልስ ዋገን መኪኖች ትርዒት በቅጥር ግቢያችን ውስጥ ሚያዝያ 30/2013 ማካሄድ እንዲችል ጥያቄውን በቅድመ ሁኔታ ተቀብሎት ነበር ብሏል።

ነገር ግን፣ ኮላብ ሲስተምስ የቅደመ ሁኔታ ፈቃዱን ከድርጅታችን ከወሰደ በኋላ ቅድመ ሁኔታዎችን ተነጋግሮ ሳይፈራረምና ሌሎች ለትርዒቱ አስፈላጊ የሆኑ ሁነቶችን ለድርጅታችን ሳያሳውቅ ቆይቶ የትርዒቱ መካሄጃ 3 ቀን ሲቀረው በላከው የኢሜል መልዕከት በኮቪድ ሥርጭት ምክንያት ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘት አለመቻሉን ገልፆ፣ ተለዋጭ ጥያቄ እስከሚያቀርብ ድረስ ትርዒቱን ላልተወሰነ ጊዜ ያራዘመው መሆኑን ቢያሳውቅም፣ ከዚያ ቀን በኋላ ድርጅታችን ዝግጅቱን በራሱ ለማድረግ ማስታወቂያ እስከሚያወጣ ድረስ ኮላብ ሲሰተምስ ትርዒቱን እንደገና ለማድረግ ስለማሰቡ ምንም አይነት ማስታወቂያ ለድርጅታችን አላከም ሲል ነው የገለጸው።

የመኪና ትርኢት ይፋዊ ዝግጅት እንደመሆኑ ማንም የባለቤትነት ጥያቄ ሊያቀርብበት እንደማይገባ ጠቅሶ፣ ድርጅታችን የሌላን ድርጅት ሐሳብ የወሰደ ተደርጎ መወሰዱ አሳዛኝ ከመሆን ባለፈ ስም ማጥፋት ነው ሲልም አሳስቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com