የእለት ዜና

በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በምትገኘው ወልድያ ከተማ የአተት በሽታ መከሰቱ ተሰማ

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በምትገኘው የወልድያ ከተማ የአተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) በሽታ እንደተጋረጠባቸው ባሳለፍነው ጥቅምት 8/ 2014 ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
“ቤታችንን ለቀን ወዴት መሄድ እንችላለን?” ብለው በጦርነቱ የሚደርስባቸውን ችግር ተቋቋመው እስካሁን ሳይወጡ በከተማው ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች የአተት በሽታ ተጋርጦባቸዋል የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ለበሽታው መከሰት ዋነኛ መንስኤው በከተማው የውኃ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ የቆሸሸ ወራጅ ውኃን ከወንዝ ቀድተው በመጠቀማቸው መሆኑን አመላክተዋል።

ስለ ወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ከምንጮቻችን መረዳት የተቻለው፣ የቆሸሸ ወራጅ ውኃን በመጠቀማቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቅ በርካታ ሰዎች ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ሰለባ መሆናቸውን ነው።

ከርሃቡ በተጨማሪ አተት የተባለው በሽታ ሌላ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል የሚሉት ቦታው ላይ በአካል የነበሩት ነዋሪዎቹ፣ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ጤና ጣቢያውንና ሆስፒታሉን ስላወደሙት የአተት ሕሙማኑ ሕክምና ለማግኘት መቸገራቸውን አመላክተዋል።
አክለውም፣ የስኳርና የደም ግፊት ሕመም ያለባቸው ሰዎች ያላቸውን መድኃኒት በመጨረሳቸው የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በተደጋጋሚ እየጠየቁ ቢቆዩም፣ እስካሁን መድኃኒት ባለማግኘታቸው ባሳለፍነው ሳምንት ከ10 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ለሞት መዳረጋቸውን ነው የተናገሩት።

አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ እንደሰማችው ከሆነ፣ ህወሓት የወልድያ ከተማን ሲቆጣጠር ለከተማው ብርሃን ከመስጠት ባሻገር፣ እህል ለማስፈጨት የሚረዱ ዘመናዊ ወፍጮዎችን እንዲተከሉ፣ እንዲሁም የተጣራ ውኃ በየ ቄየው እንዲገባ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረውን የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ላይ ውድመት አስከትለውበታል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ምግባቸውን የሚያዘጋጁት በድንጋይ ወፍጮ እየፈጩ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት የወልድያ ከተማን ከተቆጣጠረበት ከነሐሴ ወር መግቢያ 2013 ጀምሮ በከተማው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የለም የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ከተማውን ለቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የከተማው ነዋሪዎች ወራጅ ውኃን ለመጠጣት በመገደዳቸው ለአተት ሕመም ዳርጓቸዋል ሲሉ ነው የአይን ምስክርነታቸውን የሰጡት።

ከመረጃ ምንጮቻችን መካከል ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ወጣት፣ አካባቢያቸውን ለቀው ያልወጡ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች፣ መብራትና ውኃ ከተነፈጋቸው ሦስት ወራት ማስቆጠራቸውን የገለጸች ሲሆን፣ እስካሁን የዝናብ ውኃን ለመጠጥነት ሲጠቀሙ ቢቆዩም ከሦስት ሳምንታት ወዲህ ዝናብ መዝነቡን ስላቆመ የወንዝ ውኃ ነው ለመጠጥነት የሚውለው ብላለች።

ወጣቷ አያይዛም በከተማዋ ያለ ማንኛውም ሰው ከኹለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ የማይችል ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድኑ በየግለሰቡ ቤት እየዞረ ብር የመውሰድ ተግባሩንም እንዳላቆመ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸችው።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ፣ “ወደ ትግራይ ክልል እንኳን የመድኃኒትና የምግብ ዕርዳታ እየገባ መሆኑን እየሰማን ነው፣ ሌላው ቢቀር ቀይ መስቀል እንኳን በአማራ ክልል ውስጥ የርሃብና የመድኃኒት ዕጥረት ገጥሞናል ብለው ሲለፍፉ ዝምታን የመረጠው ለምን ይሆን? መንግሥትስ ምነው ያስተዳድረናል ብለው የመረጡት ዜጎች ችግር ሲገጥማቸው ዝም ብሎ መመልከትን የመረጠው?” በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ በወልድያ ከተማ የተከሰተው የአተት በሽታ ከእስካሁኑ ችግር በላይ ሌላ መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር ሆኗልና የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ምን እየተሠራ እንደሆነ ለመጠየቅ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊ ተስፋ ሚካኤል አፈውርቅ ስልክ የደወለች ሲሆን፣ ዝርዝር ለመናገር ቀጠሮ ብታገኝም በድጋሚ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሐሳባቸውን ማካተት ሳይቻላት ቀርቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com