የእለት ዜና

ኮሜርሻል ኖሚኒስ የጉልበት ብዝበዛ እያደረሰብን ነው ሲሉ ሠራተኞቹ ተናገሩ

የኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በሠራተኞቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ በደልና የጉልበት ብዝበዛ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰ ይገኛል ሲሉ መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር አባላት ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የሠራተኞች ማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አብርሃም አድኖን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አሁን ላይ ኮሜርሻል ኖሚኒስ ከ30 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ድርጅቶች ሠራተኛ ማቅረብ ከጀመረበት ከ2004 ጀምሮ ሠራተኛውን እያንገላታ ነው ብለዋል።

ከሠራተኞቹ ውስጥ አብዛኞቹ ጥበቃ፣ ፅዳት፣ ተላላኪ፣ ሹፌር፣ ብር አጃቢ፣ ኤሌክትሪሺያና የመዝገብ ቤት ባለሙያ ናቸው ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ለአንድ የንግድ ባንክ ጥበቃ ሰባት ሺሕ 144 ብር የሚወጣ ሲሆን፣ ለእኛ የሚደርሰን ግን ኹለት ሺሕ 160 ብር ነው ብለዋል። በዚህም በስማቸው ከንግድ ባንክ ሰባት ሺሕ 144 ብር ወጭ እንደሚደረግና ቀሪው አራት ሺሕ 984 ብር በኮሜርሻል ኖሚኒስ አላግባብ እንደሚቆረጥ ነው ያመላከቱት።

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ፣ እንዲሁም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ለሠራተኞች የመደራጀት መብት የተፈቀደ ቢሆንም፣ ኤጀንሲው ግን ማኅበሩን ለመበተን እንደሚጥር እና በማኅበሩ ውስጥ መብታቸውን የሚጠይቁ ግለሰቦችን እየተከታተለ እንደሚያባርር ብሎም ደሞዝ እንደሚያግድ ጨምር ተናግረዋል።
የማኅበሩ አባላት ለብዙ ጊዜያት ችግሮቻቸውን ለተለያዩ አካላትና ተቋማት፣ ማለትም ለአዲስ አባበ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ለኢፌዲሪ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለኮሜርሻል ኖሚንስ እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ቢያመለክቱም ይስተካከላል ጠብቁ ከመባል ውጭ ምንም መፍትሔ እንዳላገኙ ገልጸዋል።

አንድ ሠራተኛ ከ60 ቀን የሙከራ ቅጥር በኋላ ቋሚ ሠራተኛ መሆን እንዳለበት በአሠሪና ሠራተኛ ዐዋጁ ላይ የተደነገገ ቢሆንም፣ እኛ ግን ለስምንትና ለዘጠኝ ዓመታት ውላችን እየታደሰ የኮንትራት ሠራተኛ ነን ሲሉም ነው የተናገሩት።
እንዲሁም አንድ ሠራተኛ ለጡረታ የሚቆረጥበት ሰባት በመቶ ብቻ ሆኖ ሳለ፣ ኮሜርሻል ኖሚንስ ግን ከራሱ ላይ መቁረጥ የነበረበትን 11 በመቶ ጨምሮ 18 በመቶ የሠራተኛ ጡረታ የሚቆርጠው ከሠራተኛው አንደሆነ ጠቁመዋል።

የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የሚቆረጠው ከዕቃ ብቻ እንደሆነ ነበር የምናውቀው የሚሉት የማኅበሩ አባላት፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት፣ ለዓመት ፈቃድ፣ ለ‹ፐብሊክ ሊያቢሊቲ ኢንሹራንስ›፣ ለበዓል ቀን ክፍያ፣ ለወሊድ ፈቃድ፣ ለሱፐርቪዥን፣ ለዳኝነት፣ ለቁሳቁስ በሚል ከደሞዛችን ይቀነሳል ብለዋል።
“መንግሥትም ይሁን የግል ድርጅቶች ለሚፈልጉት ሥራ በቂ የሰው ኃይል በመኖሩ፣ አሠሪና ሠራተኛ በቀጥታ መገናኘት ሲኖርባቸው፣ ብዙ የድለላ ሥራ የሚሠሩ ኤጀንሲዎች በመሀል በመግባትና ከሠራተኛው ደሞዝ ከግማሽ በላይ በመወስድ ያላግባብ ትርፍ የሚያግበሰብሱ እና የሰውን ሕይወት የሚያጎሳቁሉ ሆነው ሳለ፣ መንግሥት ለምን እንደማያስቆማቸው ግራ ገብቶን የተውነው ጉዳይ ነው” ብለዋል።

የኮሜርሻል ኖሚኒስ ዳይሬክተር ጀኔራል ጥላሁን ፀጋዬ (ኮ/ር) በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ አብዛኛዎቹ በማኅበሩ የተነሱ ቅሬታዎች ሐሰት መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ኮሜርሻል ኖሚኒስ ተቋማት ጊዜ ኖሯቸው ዋና ሥራቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ወጭ ቆጣቢ እንዲሆኑ የሦስተኛ ወገን አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል። በዚህም በኤጀንሲው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስንስተዋል።

የሠራተኞችን ደሞዝ በተመለከተም፣ ሙሉ ጥቅማጥቀምን ጨምሮ ሠራተኞች በአማካይ ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር እንደሚደርሳቸውና ከሌሎች ኤጀንሲዎች የተሻለ እንደሚከፈሉ ገልጸው፣ በአንድ ሠራተኛ ስም ከተቋማቱ ከምናገኘው ገንዝብ ውስጥ ግዴታ ለሥራ ልብስ እና ለተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች እንቆርጣለን ነው ያሉት። የሚቆረጠው ቫትም አገልግሎት ስለሆነ ግዴታ ነው ብለዋል።

ከቋሚነት ጋር በተያያዘ፣ እኛ ቋሚ የሚባል ሥራ ስለሌለን ማንኛውንም ሠራተኛ ቋሚ ማድረግ እንደማንችል በግልጽ አሳውቀናል ሲሉ ነው የገለጹት።

እንዲሁም፣ መጀመሪያ ሲቀጠሩ ኹሉንም ነገር አውቀውና ተስማምተው እስከገቡ ድረስ ካልተመቻቸው ለቀው መውጣት እንጂ የተቋሙን ስም ማጠልሸት አይገባም ብለዋል። ከዚያ ውጭ ሠራተኞችን የሚያሰፈራሩ፣ ከዐዋጁ ውጭ ሰልፍ የጠሩና የትምህርት ማስረጃቸው ሐሰተኛ ሆኖ ያገኘናቸውን ግለሰቦች ከሥራ አግደናል ሲሉ ተናግረዋል።

ኮሜርሻል ኖሚንስ ኃ/የተ/የግ/ማ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን የተቋቋመ እና ለሦስተኛ ወገን አገልለግሎት የሚሰጥ 13 የሚደርሱ አግልግሎት ሰጪ ሥራዎች ላይ የተሠማራ ተቋም መሆኑ ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ በተነሳው ቅሬታ ላይ ከአዲስ አበባ ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረገቸው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com