የእለት ዜና

ሕወሓት ከ300 በላይ መኪናዎች አዘጋጅቶ በውርጌሳና ውጫሌ ያሉ ንብረቶችን “ዘርፏል” ተባለ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል በሽብርተኛነት የተፈረጀው ህወሓት ከ300 በላይ ተሳቢ መኪናዎችን አዘጋጅቶ በደላንታ፣ ውርጌሳና ውጫሌ አካባቢ ያሉ የመንግሥትና የበርካታ ግለሰቦችን ንብረት “መዝረፉን” የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች የተናገሩት፣ ባሳለፍነው ሳምንት (ጥቅምት 2014 ኹለተኛ ሳምንት) ሽብርተኛ የተባለው ህወሓት ውርጌሳና አካባቢውን በመቆጣጠር ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለሞት እንደዳረገና፣ ከ300 በላይ ተሳቢ መኪናዎችን አቅርቦ የግለሰብና የመንግሥት ንብረቶችን ወደ ትግራይ ክልል ዘርፎ ማጓጓዙን ነው።

ከውርጌሳ እስከ ውጫሌ ድረስ እዲሁም፣ በደላንታ በኩል ከ300 በላይ የሚሆኑ ለዕቃ መጫኛ አገልግሎት የተዘጋጁ ተሳቢዎችን በየአስፓልቱ ዳር አይተናል የሚሉት ሰሞኑን ከአካባቢው ወደ ደሴና ባህር ዳር ያቀኑ ነዋሪዎች፣ ሽብርተኛ የተባለው ህወሓት የግለሰቦችን ቤት እየከፈተ የተለያዩ ዕቃዎችንና እህሎችን ጭምር እየጫነ መሰንበቱን ነው ያመላከቱት።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ባሳለፍነው ጥቅምት 8/2014 ከደሴ ከተማ 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን የአምባሰል ወረዳ ዋና ከተማ ውጫሌን መቆጣጠሩን ያብራሩት ወደ ደሴ የመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ የሐብሩና የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ደሴ እየተመሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በቅሎ ማነቂያንና ፀሐይ መውጫን ተቆጣጥሮ የቆየው ታጣቂ ቡድኑ፣ ባሳለፍነው ጥቅምት ስምንት 2014 የደላንታ ዋና ከተማ ወገል ጤናንም መቆጣጠሩን የገለጹ ሲሆን፣ የደላንታ ሆስፒታል ማሽኖችንና መድኃኒቶችንም ጭምር በመኪና ጭኖ ወስዷቸዋል ብለዋል።
በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ ነው በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ደላንታን የተቆጣጠረው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ መከላከያው አካባቢውን ሲለቅ ምንም አይነት ተኩስ አለመኖሩ ህወሓት ያለ መሰናክል እንዲገባ ሳያግዘው አልቀረም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከሦስት ሳምንታት በፊት በጋሸና አካባቢ የደረሱ ሰብሎችን አጭዶ እየወሰደ ቢቆይም፣ ከሳምንት በፊት በደረሰበት የአየር ኃይል ጥቃት አካባቢውን ለቆ እንደወጣ ያመላከቱ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተዘጋጀበት ጊዜ አካባቢው በድጋሚ በቡድኑ በቁጥጥር ሥር እንደዋለና በድጋሚ ዘረፋ እያከናወነ መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።

አክለውም፣ ታጣቂ ቡድኑ ተቆጣጥሮት የነበረውን ቦታ እንዲለቅ ተደርጎ መቆየቱ፣ “የሕዝቡ እርዳታ ስላለበት ነው” በሚል እሳቤ አሁን ላይ አካባቢውን በድጋሚ ሲቆጣጠር በንጹሐን ላይ አስከፊ ጥቃት ከመፈጸሙም በተጨማሪ፣ የግለሰብ ቤቶችንም አንድ በአንድ እየፈተሸ ንብረቶችን እየጫነ ነው ብለዋል።
በጋሸናና በላሊበላ መካከል በሚገኘው ድብኮ አካባቢ፣ እንዲሁም ዋድላ ደላንታና ጫና አካባቢ ይህ ዘገባ በተዘጋጀበት ወቅት በከባድ መሳሪያ የታጀበ ጦርነት መከፈቱ የተመላከተ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ንጹኃን ሴቶችና ሕፃናት ተገድለዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች አያይዘውም፣ በጋሸና በሚገኘው አምባ ጋሸና በሚባለው አካባቢ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ምሽግ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ አካባቢው በድጋሚ በቁጥጥር ሥር መሆኑ ጥቃቱን ይበልጥ አስከፊ አድርጎታልና “መከላከያ ሠራዊቱ እንኳን ሊመከትልን፣ ያዝ ለቀቅ እያደረገ ለአስከፊ ግድያ አሳልፎ እየሰጠን ነውና መንግሥት ኃላፊነቱን የማይወጣው እስከመቼ ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

አክለውም፣ ሽብርተኛ የተባለው ህወሓት እየሰነዘረው ያለው የንጹኃን ጥቃት ከእስካሁኑ ለየት የሚያደርገው ገጽታ መኖሩን የገለጹ ሲሆን፣ ይኸውም በተለይም በአምባሰል ወረዳ የታጣቂ ቡድኑ ከባድ መሣሪያ በተደጋጋሚ መተኮሱን ተከትሎ በርካታ ንጹኃን ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን ነው የጠቆሙት።
በሐይቅ ከተማ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን 40 ሰላዮች በመገኘታቸው የአካባቢው ሰዎች ወደ ደሴ ከተማ እያቀኑ መሆናችወን ያመላከቱ ሲሆን፣ የደሴ ከተማ አስተዳዳር አበበ ገብረ መስቀልም ምንም እንኳ የተፈናቃዮች ብዛት እየጨመረ ቢመጣም እስካሁን በደሴ ከተማ ምንም አይነት ጥቃት አልተፈጸመም ብለዋል።

አክለውም የአካባቢውን ሚሊሻ፣ ታጣቂና ወጣት በማደራጀት ጥቃት ለመሰንዘር የሚገሰግሰውን ቡድን ለመመከት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት።
አዲስ ማለዳ ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሰይድ አሕመድ ስልክ ብትደውልም ስልክ ሊያነሱ ባለመቻላቸው ጉዳዩን በማስመልከት ያላቸውን ሐሳብ ማካተት ሳይሳካላት ቀርቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com