የእለት ዜና

የዶሮ እና እንስሳት ሀብት ላይ ያተኮረ ዓውደ-ርዕይ ሊካሄድ ነው

29ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት ዕርባታ ባለሙያዎች ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ፣ 10ኛው የኢትዮ ፓልተሪ ኤክስፖና 6ኛው የአፍሪካ እንስሳት ዓውደ-ርዕይ እና ጉባኤ ከፊታችን ከጥቅምት 18 እስከ 20 በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል፣ እንዲሁም ከጥቅምት 22 እስከ ኅዳር 22/2014 ድረስ በበይነ-መረብ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
ዓውደ- ርዕዩና ጉባኤውም ከተለያዩ አገራት የተዉጣጡ የዕሴት ሰንሰለቱን የሚወክሉ የዘርፉ ዋና አንቀሳቃሾች የሚሳተፉበትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናትና ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት እንደሚሆንም አዘጋጆቹ ‹ፕራና ኤቨንትስ› እና መቀመጫውን ሱዳን ያደረገው ‹ኤክስፖ ቲም› ባሳለፍነው ሐሙስ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
የ3 ቀናት ቆይታ እንደሚኖረዉ በተነገረዉ እና የዶሮ እና እንስሳት ሀብት ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚህ ዓውደ-ርዕይና ጉባኤ ላይም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ7 አገራት ማለትም ከጀርመን፣ ሐንጋሪ፣ ዮርዳኖስ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስኮትላንድና ሱዳን የተውጣጡ 50 ኩባንያዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።
ይህን በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የሚካሔደውን ዓውደ-ርዕይም ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
መድረኩ ለዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችና ግብአቶች የሚቀርቡበት ከመሆኑም ባሻገር፣ በዶሮ እና የእንስሳት ሀብት ላይ የሚታዩ ችግሮች በመፈተሽ መፍትሔ የሚሆኑ ግብዓቶች የሚገኙበት እንደሚሆንም የፕራና ኤቨንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነብዩ ለማ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት/ፋኦ/ ሪፖርት እንደሚያመለክተዉ ኢትዮጵያ በ2030፣ 456 ሺሕ ቶን የከብት ሥጋ፣14 ሺሕ 231 ቶን ወተት፣ 96 ሺሕ ቶን ዶሮ፣ 54 ሺሕ ቶን እንቁላል እንዲሁም 265 ሺሕ ቶን የበግና ፍየል ስጋ እንደምትጠቀም ግምቱን አስቀምጧል።
የአገራችን መንግስትም ባስቀመጠው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ መሠረት በ2022 የወተት ምርትን 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ሊትር፣ የሥጋ ምርትን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ የዕንቁላል ምርትን 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ የዶሮ ሥጋ ምርትን 106 ሺሕ ቶን፣ የአሳ ምርትን 247 ሺሕ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን 152 ሺሕ ቶን ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com