የእለት ዜና

በቦረና ዞን በዝናብ ዕጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተገለጸ

የቦረና ዞን ነዋሪዎች በዝናብ ዕጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ለውኃ፣ለምግብና ለጤና ችግር መጋለጣቸው ነው የተነገረው።
ድርቁ የተከሰተው በዞኑ በ2013 የበልግ ዝናብ በቂ ባለመሆኑና የ2014 የመኸር ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት እንደሆነ ነው የተገለጸው። በድርቁ የተነሳም በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በደረሰው ድርቅ 539 ሺሕ 679 የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የውኃ ዕጥረት እንዳጋጠማቸው ታውቋል። ከዚህም ውስጥ 177 ሺሕ 553 ለሚሆኑት ብቻ በቦቴ ውኃ እንዲያገኙ መደረጉ ተሰምቷል።
እስካሁን በደረሰው የምግብ ዕጥረትም 6 ሺሕ 398 ሕፃናት፣ 9 ሺሕ 78 እናቶችና 2 ሺሕ 226 አዛውንቶች ላይ የጤና ችግር መድረሱ ተገልጿል።
እስካሁንም ለ118 ሺሕ 864 ሰዎች የምግብ ዕርዳታ የተደረገ ሲሆን፣ 166 ሺሕ 136 የሚሆኑት ደግሞ ተጨማሪ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተብራራው። በተከሰተው ድርቅም 7 ሺሕ 540 ከብቶች የሞቱ ሲሆን፣13 ሺሕ 641 የሚሆኑት ደግሞ በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ተገልጿል።
እንስሳቶቹን ከአደጋው ለማትረፍ ዞኑ 2 ሚሊዮን 463 ሺሕ 214 ቤል ሳር ከመንግሥት መጠየቁም ተጠቁሟል።
አሁን ላይ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች እንደቀጠሉ ቢሆንም፣ ከችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አንፃር ግን በቂ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
እንዲሁም ከ200 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችም ሮቶዎችንና በቂ ውኃ የሚፈልጉ መሆናቸው ሲገለጽ፣ በዞኑ በ2009 ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ የነበረ መሆኑና በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በሕዝብ ትብብር ማገገም ተችሎ እንደነበር ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com