የእለት ዜና

ችግራቸው እንደብዛታቸው የጨመረ ተፈናቃዮች

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰና ሕዝብ መፈናቀል ከጀመረ ቢከራርምም እንደሠሞኑ አሳሳቢ የሆነበት ወቅት አልተፈጠረም። በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካቶች ወደ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በመትመማቸው እነሱን ለመደገፍ የሚደረገውን እርዳታ የማከፋፈልና የማዳረስ ስራውን አዳጋች አድርጎታል። የሚፈናቀለው ቁጥር በጨመረው ልክ ተጨማሪ ድጋፍ ካመገኘቱ በተጨማሪ፣ ተፈናቃዮቹ የሚያርፉበት ቦታ አጥተው ውጭ ሜዳ ላይ በጥቅምቱ ንፋስ ውሎ ለማደር ተገደዋል። የተፈናቃዮቹን ችግር የአዲስ ማለዳው ብንያም ዓሊ የሀተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ ተመልክቶታል።

ግለሰብ ከኖረበት ማኅበረሰብ ተለይቶ ለመፈናቀልና ተሰዶ ወደሌላ ቦታ ሔዶ ለመኖር የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። የሕብረተሰቡ አካል የሆነ ማኅበረሰብ ግን በጅምላ መኖሪያውን ትቶ የሚፈናቀለው ወይ በጦርነት አሊያም ድርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ሽሽት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ሲከሰት የመጀመሪያው ባይሆንም፣ አሁን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰውና ዓመት ሊያስቆጥር ቀናት የቀሩት ጦርነት፣ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ የተፈናቃይ ቁጥር የታየበት ነው። ከሺሕ ዓመት በፊት በነበረው በዮዲት ዘመን በርካታ ተፈናቃዮች እንደነበሩ ቢነገርም፣ መንግሥቷ ለ40 ዓመት የዘለቀ ስለነበር ያን ያህል ሰው ተፈናቅሎ እንዳልቀረ የሚናገሩ አሉ። የ8ኛው ሺሕ ዘመን መጀመሪያ ተብሎ በሚታወቀውና ከ500 ዓመት በፊት ከነበረው ከግራኝ አሕመድ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የኦሮሞ መስፋፋት እየተባለ የሚታወቀው የረጅም ጊዜ የጦርነት ሒደት እስካበቃበት ዘመን ድረስ ግን የተለያዩ ፀሐፊዎች እንደሚያስቀምጡት፣ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውን ለመገመት የሚያስቸግር የተለያዩ ማኅበረሰቦች ከቄያቸው ተፈናቅለውና ተሰደው በዛው ቀርተዋል።

ከዘመነ መሳፍንት አንስቶ እስከ አሁን ያለውን ሒደት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው፣ የሆነ ማኅበረሰብን እወክላለሁ የሚል ቡድን የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እያነሳሳ እርስ በርስ የተዋጋንበት እንደነበረ የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። በእነዚህ ጦርነቶች ያሸነፈ ሥልጣን ይይዛል እንጂ ጦርነቶቹ ሕዝባዊ ስላልነበሩ ያን ያህል ሕዝብ የሚፈናቀልባቸው አልነበሩም።

የውጭ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ጠቅልለው ለመያዝ በተደጋጋሚ በሞከሩባቸው አጋጣሚዎችም ቢሆን ሕዝብ የአሁኑን ያህል አልተሰደደም ነበር። ጣሊያን አምስት ዓመት ያህል ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ስትሞክር አርበኞች ጫካ ከመግባታቸውና፣ ሌሎች መኳንንቶች እየሸሹ በየገጠሩ ከመቀመጣቸው ውጭ በሕዝብ ደረጃ የተፈናቀለ እንዳልነበር ለማወቅ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ በቂ ይሆናል።

በዘመናችን በተከሰቱት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ሆነ በደርግ ይመራ የነበረው መንግሥት ከዘመኑ አማጺያን ጋር ባደረገው ጦርነት ወቅት የአንድ ማኅበረሰብ አባላት በጅምላ አልተፈናቀሉም ነበር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ በተገነጠለችበት ሒደት በርካቶች ከምጽዋና ከተለያዩ ግዛቶች ተፈናቅለው ስደተኛ ተብለው ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም፣ አሁን ያለውን ያህል ብዛት ስላነበራቸው በየቀበሌው እንዲሰፍሩ ተደርጎ ድጋፍም ከመንግሥት ስለተደረገላቸው ያን ያህል ችግር አላጋጠማቸውም ነበር። ኢትዮጵያ የነበሩ ኤርትራውያን በጦርነቱ ወቅት ሲባረሩም የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ከአሁኑ ጋር የሚነጻጸር አልነበረም።

አምና ጥቅምት መጨረሻ ግድም ሕግ ማስከበር ነው እየተባለ የተጀመረው ውጊያ በኹለት ሳምንት ተገባደደ ተብሎ ማብቃቱ ቢነገርም፣ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ጦርነቱ እያገረሸ አድማሱንም እያሰፋ እስካሁን ዘልቋል። ውጊያው በተቀሰቀሰበት የመጀመሪያው ምዕራፍ የመንግሥት ኃይሎች ሙሉ ትግራይን ሲቆጣጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎች እንደነበሩ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገብ ቆይቷል። የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመው ጎረቤት አገር የተሰደዱ ናቸው ተብሎ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ተዋጊ ናቸው ከተባሉት ውጭ በአገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ የተፈናቀሉ ብዙ ቁጥር አልነበራቸውም።

የመንግሥት ሠራዊት ትግራይን በተቆጣጠረ ወቅት ለደኅንነቱ ሰግቶ ግዛቱን የለቀቀ የመኖሩን ያህል፣ ከያለበት እየተመለሰ የተቀላቀለም እንደነበር በተለያየ አጋጣሚ ሲነገር ቆይቷል። መንግሥት ለቆ ነው በተባለው አጋጣሚ የህወሓት ጦር ትግራይን መልሶ እስኪቆጣጠር የተፈናቃይ ቁጥር ያንን ያህል የሚጠቀስ አልነበረም። ይህ ማለት ግን የደኅንነት ስጋት ሳይሰማው በየቤቱ ቆይቶ የተራበ የለም ማለት አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ተራበ በሚል ዓለም አቀፍ ዘመቻ መንግሥት ላይ ጫና እስኪፈጠር ድረስ በመቀስቀስ ዕርዳታ በስፋት እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል።

በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ ግን የሆነው ማንም ያልጠበቀው ነበር። የጥሞና ጊዜ በሚል የተሰጠውን ዕድል እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ጦሩን በደንብ እንዲያዘጋጅና አሁንም ድረስ ለብዙዎች ስጋት ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል። ቡድኑ ከትግራይ ግዛት የሰበሰባቸውን እና እንደልብ ያስታጠቃቸውን በርካታ ታጣቂዎች ድንገት በየሁሉም አቅጣጫ በማዝመት የአማራና የአፋር የተለያዩ ግዛቶችን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ችሏል።

የጎንደርና የወሎ ሰሜናዊ ግዛቶችን እንዲሁም የአፋርን ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር የቻለው የህወሓት ታጣቂ ቡድን፣ እያደር ይዞታውን እየጨመረ አሁንም ድረስ አዳዲስ ቦታዎችን በመውረር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ በየከተማውና በየጥሻው እንዲጠለል ማድረጉ የየዕለት ዜና ከሆነ ከራርሟል።
ከከተማ ከተማ ደጋግመው ከሦስትና አራት ጊዜ በላይ እየተፈናቀሉ ያሉ ሚሊዮን ሊደርሱ የሚችሉ ተፈናቃዮች በየቦታው መስፈራቸውን የሚናገሩ አሉ። መንግሥት በሚያውቃቸው መጠለያ ጣቢያዎች የተመዘገቡትን ብቻ ስለሚያሳውቅ፣ በየዘመድ አዝማዱ ቤትና ቤት ተከራይተውም ሆነ በየገጠሩ የተጠለሉትን ሲጨምር የተፈናቃዩ ቁጥሩ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በተለያዩ ግዛቶችና መጠለያ ጣቢዎች የሚገኙት ተፈናቃዮች አስፈላጊውን ዕርዳታ በበቂ ሁኔታ ሳያገኙ እያደር ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል። ቁጥራቸው እንደችግራቸው እያደር የጨመረባቸው ተፈናቃዮች፣ እንደ አጀማመሩ የሚረዳቸው ሲቀንስ ብዛታቸው ግን እያደር ጨምሯል። የስደተኛው ቁጥር አሁን ለመብዛቱ ብዙ ምክንያቶችን ተፈናቃዮቹ ራሳቸው መናገር ቢችሉም፣ ከቁጥሩ አንጻር የሕዝቡን አጠቃላይ ሥጋት የሚያሳይ ነው። ታጣቂ ቡድኑን ፈርተው ባለሥልጣናትና ሹመኞች ቢፈናቀሉ ባይገርምም፣ ተራው ሕዝብና አርሶ አደሩ ሳይቀር መፈናቀሉ ለታጣቂ ቡድኑ ሕዝቡ ያለውን አመለካከት በግልጽ የሚያስረዳ እንደሆነ የሚያመላክቱ አሉ።

የመንግሥት ኃይል ትግራይን በተቆጣጠረ ጊዜ ከነበረው እውነታ ጋር እያነጻጸሩ የሚናገሩ እንደሚሉት፣ ሕዝብ ለምን ይህን ያህል ስጋት ተሰማው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ጦርነቱ የሥልጣን ወይም የግዛት ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ላይ በተመሠረተ ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ ስጋቱ ከመቼው ጊዜ በላይ አሁን ጨምሯል። ታጣቂዎቹ ተቆጣጠሯቸው በተባሉ አካባቢዎች ሕዝብ ላይ እየተፈጸሙ እንደሆኑ የሚነገሩ አስከፊ ድርጊቶች ለተፈናቃዩ ቁጥር መጨመር በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከተለያዩ የሰሜን ወሎ ግዛቶች በየተራ እተፈናቀሉ አሁን ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደባርቅና ባህርዳር ዘንዘልማ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ተፈናቃዮች ከተጋረጡባቸው የተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች በተጨማሪ አሁንም ሥጋቱ እያደር እየጨመረባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

ከዋግ ኽምራ የሰሜን ወሎ ግዛት ተፈናቅለው ባህርዳር የተጠለሉ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዕገዛና በተለያዩ ግብረ ሠናይ ተቋማት ድጋፍ እየተደረገላቸው ቢሆንም፣ በቂና ዘላቂ ባለመሆኑ ሥጋቱ አሁንም አለባቸው። መቼ እንደሚመለሱ ካለማወቃቸው በተጨማሪ፣ በቆይታቸው ወቅት ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ይናገራሉ። ከችግሮቻቸው መካከል በመጠለያ ጣቢያው የቁስል በሽታ ብዙዎች ላይ በመከሰቱ በርካቶች ጥለው እንዲወጡም ምክንያት ሁኗል። ወጥቶ የመታከሚያ አቅም ስለሌላቸው የባሰባቸው ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ ባሉበት ለሕመም መዳረጋቸውን በባለፈው ሳምንት ዕትማችን ማስነበባችን ይታወሳል።

ከሰሜን ጎንደር የተለያዩ ግዛቶች ተፈናቅለው ደባርቅና በአቅራቢያው የሚገኙ ወደ 40 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ቢኖሩም እንደሌሎቹ ትኩረት አለማግኘታቸው ይነገራል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ከጦር ቀጠናዎቹ ሸሽተው የመጡትን እያዋጣና ተራ እየገባ ቢንከባከብም፣ ጊዜው በመራዘሙ ምክንያት ረጂው በመሰላቸቱ፣ እንዲሁም አቅሙ በመመናመኑ እንደበፊቱ ድጋፍ እንደማያገኙ ይጠበቃል።

እነዚህ የቅርብ ጊዜ ተፈናቃዮች አነሰም በዛ የሚያገኙትን ድጋፍም ሆነ የተሰጣቸውን ትኩረት ያህል በጥቂቱም ቢሆን ያላገኙ እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል ከወለጋ የተለያዩ ቀጠናዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የዕልቂት ተግባራት ምክንያት ቁጥራቸውና መዳረሻቸው እንኳን በቅጡ የማይታወቅ ተፈናቃይ ዜጎች አሉ። በየደርግ ዘመን በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ተደርገው የነበሩ የወሎ ድርቅ ተጠቂዎች፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወልደው በከበዱበት ከኦሮሚያ ክልል መኖር አትችሉም ተብለው ሲፈናቀሉ ቆቦን በመሳሰሉ የወሎ ግዛቶች እንዲሰፍሩ ተደርጎ ነበር። የእነሱና የሌሎች መሰል ተፈናቃዮች ችግር ሳይፈታ እነሱን ጨምሮ አስተናግደዋቸው የነበሩ ማኅበረሰቦች አሁን ራሳቸው ተፈናቃይ ሆነዋል።

መፈናቀል በይፋ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት መከሰት ከጀመረ ሦስት ዓመት ተቆጥሯል። ቡራዩ በተከሰተው ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሳቢያ የተፈናቀሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረገ ጥረት አብዛኞቹ እንዲመለሱ ቢደረግም፣ ንብረትና ሀብታቸው ጠፍቶባቸው መመለስ ሳይችሉ በዛው የቀሩም እንዳሉ ሲዘገብ ነበር። ሌላው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የተፈናቀለባቸው የጉጂ ማኅበረሰቦችም ተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ መፍትሔ እንደተገኘ ቢነገርም፣ አሁን ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የተከታተላቸው የለም።

በአንጻሩ በሱማሌና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች ከተሞች ተከስቶ በነበረ ግጭት ሳቢያ የኹለቱም ማኅበረሰቦች አባላት ለመፈናቀል ተገደው ነበር። ከኦሮሚያ ግዛት የተፈናቀሉት ሱማሌ ክልል ገብተው ስለተደረገላቸውም ሆነ ስላጋጠማቸው ችግር ብዙም የተሰማ ነገር የለም። በተቃራኒው፣ ከሱማሌ ተፈናቅለው የነበሩ ብዛታቸው በእርግጠኝነት የማይታወቅ በርካታ ተፈናቃዮች፣ የአገሪቱ መዲና ወደ ሆነችው አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ የብሎኬት ቤት በመንግሥት ወጪ ተሠርቶላቸው በዘላቂነት እንዲሰፍሩ መደረጉ የፈጠረውን ልዩነትና ፖለቲካዊ ውዝግብ የሚረሳ የለም። ለየትኛው ኢትዮጵያዊ መደረግ የነበረበት ትኩረት ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሰጥቶ፣ ከእነሱ በፊትም ሆነ በኋላ የተፈናቀሉ በርካቶች ዕድሉን ሳያገኙት ቀርቷል። ይህ አይነት ድጋፍ በአጣዬ ከተማ ላይ ተፈጽሞ የነበረውን ውድመት ተከትሎ ለተሰደዱትም የተሰጠ አልነበረም።

የተፈናቃይ ብዛት እየጨመረ የመጣበት የአሁኑ ጦርነትም ቢሆን ተፈናቃዮችን እያደር እያበዛ ያገኙት የነበረውን ትኩረትም እያደር እንዲቀንስ ያደረገ ነው። መንግሥት ትኩረቱ ጦርነቱ ላይ እንደሚሆን ቢታወቅም፣ የተፈናቃዩ ብዛት እያደር እንዳይጨምር ለማድረግ ውጊያው ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚገባው ደጋግመው የሚናገሩ የማኅበረሰብ አንቂዎች አሉ። የጦርነቱ ማብቂያ ካልታወቀ የስደተኞች ቁጥር ብቻ ሳይሆን አገር ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች ጭምርም ቁጥራቸው ስለሚጨምር ሰብዓዊ ቀውሱን ለመገመት እንደሚያስቸግር ይታመናል።

ከኹሉም ተፈናቃዮች ቁጥራቸው በርካታ የሆነው በደሴና በኮምቦልቻ የሚገኙት የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች ናቸው። ከተለያየ ከተሞች በተደጋጋሚ እየተፈናቀሉ በኹለቱ ከተሞች የሚገኙ እነዚህ ተፈናቃዮች ከግማሽ ሚሊዮን እንደሚልቁ ይነገራል። ከሌላው አካባቢ በተሻለ የድጋፍ ሰጪዎችን ትኩረት በማግኘታቸው የተሻለ ዕርዳታ ቢያገኙም ከቁጥራቸው አንፃር በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ደሴ ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን አነጋግራ መረዳት እንደቻለችው፣ ድጋፉ እያደር ቢቀንስም፣ ችግራቸው እየጨመረ እንደሆነ ነው። በመጀመሪያ ሰሞን እንደነበረው ማኅበረሰቡም ሆኑ ባለሀብቶች ስለማይረዱ ምገባው በመጠንም ጭምር ቀንሷል ይላሉ። ችግሩ ይህ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እንደ አዲስ የሚመጡ ተፈናቃዮችን መዝግቦ እኩል ዕርዳታውን ለማከፋፈል ስለሚያስቸግር ብዙዎች ለቀናት ተቸግረው እንደሚቆዩ ይናገራሉ።

አንዳንድ ተፈናቃዮች በስማችን የሚመጣውን ዕርዳታ በተገቢው መንገድ አናገኝም እያሉም ቅሬታ ያቀርባሉ። ለሴትና ሕፃናት ቅድሚያ እየተባለ በተደጋጋሚ ድጋፉ እንዲዘለን ይደረጋል የሚሉት ተፈናቃዮች፣ ከኹሉም ነገር በጊዜ ወደአገራችን በቶሎ እንድንገባ ቢደረግ ብለው መንግሥትን ይጠይቃሉ። በቆየን ቁጥር ተፈናቃዩ ይጨምራል የሚሉት እነዚህ በመጠለያ የሚገኙት የሰሜን ወሎ ነዋሪዎች፣ ጦርነቱ በአፋጣኝ እንዲቆም ማድረግ የሚገባውን ተግባር በርብርብ መንግሥት ማከናወን እንደሚገባው ከችግራቸው በመነሳት ለማስረዳት ሞክረዋል።

በሌላ በኩል፣ ኮምቦልቻ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተፈናቃዮችንም አዲስ ማለዳ አነጋግራለች። መጠለያ አጥተው ሜዳ ላይ፣ የሚነጠፍም አጥተው ሌት በብርድ ቀን በፀሐይ ሀሩር የሚቃጠሉ መኖራቸውን ለመረዳት ችላለች። በተለይ ከባለፍው ሳምንት ጀምሮ በተደረገ የተፋፋመ ጦርነት ከድሬ ሮቃ አካባቢ የተፈናቀሉት ነዋሪዎች፣ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኘው ጃራ የመጠለያ ጣቢያ ዱር ውስጥ ሸራ ወጥረው ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች እንደ አዲስ ኮምቦልቻ ገብተዋል። በነበሩበት ቦታ ያን ያህል ትኩረት ሳያገኙ ተቸግረው የቆዩት እነዚህ ተፈናቃዮች ኮምቦልቻ ቢገቡም እንደጠበቁት መስተንግዶ አላገኙም።

ኮምቦልቻ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በር ከፍተውላቸው እንደገቡ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት አስተባባሪ የተደረጉ ተፈናቃይ ግለሰብ ናቸው። ኑረዲን ሲራጅ መሐመድ የተባሉት የሐብሩ ወረዳ ተፈናቃይ እንደነገሩን፣ ከጃራ ጀምሮ አብረዋችው የመጡ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከሌሎች አካባቢም የሚመጡት አሁንም ቁጥራቸው እያደር እየጨመረ ነው። ትምህርት ቤቱ ባሉት ክፍሎች ሁሉ 80 ገደማ ሰው እየገባ በመሙላቱ ከ2 ሺሕ የሚበልጥ ተፈናቃይ በረንዳ ላይና በየሜዳው ለማደር ተገዷል። በየቀኑ ያለውን መንገላታት ጨምሮ ያለምንም የሚነጠፍ ነገር ለማደር የተገደዱት ተፈናቃዮች ኮሚቴ መሥርተው ችግራቸውን ለማስረዳት ቢሞክሩም እስካሁን ተገቢውን ምላሽ አላገኙም። ዩኒቨርስቲዎችም ሆኑ ቦታ ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ማረፊያ እንዲሰጧቸው እየጠየቁ ቢሆንም፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ለቁር የተጋለጠው ተፈናቃይ መጠለያ ካገኘው በብዛቱ እጅግ ይልቃል።

ተፈናቃዮች ከኮምቦልቻ ቀጥለው ወዳሉ ሐርቡንና ከሚሴን ወደመሳሰሉ ግዛቶች ሔደው እንዲጠለሉ ሐሳብ ቢቀርብላቸውም፣ በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ይኖራሉ በሚል ስጋት ከኮምቦልቻ ለማለፍ እንዳልፈቀዱ አስተባባሪው ጠቁመዋል። የጦርነቱ አቅጣጫ በአጭር ጊዜ ካልተቀየረም ምን እንደሚውጣቸው በመሥጋት ተፈናቃዩ በከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግለሰቦችን አስተባብረው ያገኙትን እርዳታ በተለያዩ መጠለያዎች ሲያከፋፍሉ የነበሩን አዲስ ማለዳ አነጋግራለች። ዳንኤል አደራ የተሰኙት እኚህ ግለሰብ እንደነገሩን፣ የውጭና የአገር ውስጥ አብሮ አደጎቻቸውንና የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻቸውን በማስተባበር እርዳታ አሰባስበው በየቦታው ያከፋፍላሉ። በድሬ ሮቃ ጃራ መጠለያ እንዲሁም በኮምቦልቻ ያሰባበሰቡትን ድጋፍ ሲያደርሱ ያገኘናቸው እኚህ አስተባባሪ፣ እስካሁን ከ10 በላይ መጠለያዎች በመገኘት ያሰባሰቡትን ቢያደርሱም፣ ችግሩ በመቀነስ ፈንታ እየጨመረ መምጣቱን ከተመለከቱት በመነሳት ይናገራሉ።

የተፈናቃዩ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ ከፍጥነቱ አኳያ እርዳታ ማቅረብ አለመቻሉን ይጠቁማሉ። መንግስትም ሆነ ግብረሰናይ ተቋማት ለብቻ የሚገፋ ችግር አለመሆኑን ተረድተው ሊረባረቡ ይገባል ይላሉ። ሁሉም ሰው በኋላ ከሚያዝን በቻለው የሚያውቃቸውን በማስተባበር በአፋጣኝ እርዳታ ሊያደርስ ይገባል ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት ይናገራሉ።

ጦርነት አስከፊ መሆኑን ሕፃናት ጭምር የሚያውቁት እንደሆነ ቢታመንም፣ ያለጉልበት ሠላም እንደማይገኝ ግን ይታወቃል። አንድ በጥባጭ እስካለ ሌላው የጠራ ውኃ መጠጣት አይቻለውም እንደሚባለው፣ አደፍራሹን ለማራቅም ሆነ ደግሞ ከምንጩ እንዳይደርስ ከተፈለገ፣ ሲነገረው እምቢ ካለ ሌሎቹ ተዋግተውም ሆነ ገፍተው መልሶ እንዳይደርስ የማድረግ ግዴታ እንደሚኖርባቸው ይታወቃል። በዚህ ግርግር ሳሩ ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው በጥባጩ ባለበት አካባቢ ያለውና እስከታች የሚፈሰው ውኃ ከበፊቱም የበለጠ መደፍረሱ ይጠበቃል።

ሌላ ምንጭ ሔዶ መጠጣት እንደማይችል አደፍራሹ ከተረዳ እስከሞቱ ድረስ ለመመለስም ሆነ ቦታውን ላለመልቀቅ ሊዋጋ ይችላል። ይህ የጦርነት ሕግ እንደተጠበቀ ሆኖ በውጊያው መራዘም የተቸገሩ ሌሎቹ ጠጪዎች ጥማቸውን ታግሰው መሞት ስለማይችሉ እንደመጀመሪያው አደፍራሽ እነሱም ዘግይተውም ቢሆን ብዙ ነገር ከተበላሸ በኋላ መቀላቀላቸው አይቀርም። ይህ ሒደት ከኹለቱም ወገን ብዙዎች እንዲያልቁ ምክንያት ቢሆንም፣ አቅም የሌላቸውን ከመጠጫ ቦታው በብዛት ማፈናቀሉ አይቀርም። እነዚህ የተፈናቀሉት ቦታቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ ካልተደረገ በቆዩበት ቦታም አስፈላጊውን አቅርቦት ካላገኙ ኹለቱንም ተፋላሚ ወገኖች፣ “ገለል ብላችሁ ቀጥሉ አሊያም ምንጩን ለእኛ ልቀቁልን” በማለት በኹለቱም ወገኖች ላይ እንዲነሱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የበርካቶችን ሥጋት በምሳሌነት ማስቀመጥ ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com