የእለት ዜና

ተወርቶ የሚረሳው የወለጋ የዜጎች ሰቆቃ

በኢትዮጵያ የዜጎች ግድያ፣መፈናቀል እና በረሀብ አለንጋ መገረፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቋጫ እያጣና እየተባባሰ መጥቷል። በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተለያዩ ዞኖች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚደርሰዉ ሰቆቃ እጅግ እየከፋ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
ግድያዉ አየተባባሰ የመጣዉ ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ነዉ። ሦስት ልጆቹ እና ባለቤቱ የተገደሉበት አንድ አርሶ አደር፣ “እባካችሁ የልጆቼን እና የባለቤቴን አስከሬን ጅብ እንዳይበላው ቅበሩልኝ” ሲል እያለቀሰ ለመገናኛ ብዙኀን የተናገረበት ሐቅ የቅርብ ጊዜ መራራ እዉነት ነዉ። ግድያዉ የተፈጸመዉ እንደሚከተለዉ ነበር።

የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዲላ ጎጎላ እና ሰቀጀርቢ በተባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል ከሰበሰቧቸው በኋላ የተኩስ እሩምታ በመክፈት በርካታ ሰዎችን በመግደል ልጅን ከእናትና ከአባቱ፣ ባልን ከሚስቱ፣እህትን ከወንድሟ ለይተው፣ እናትን የወላድ መካን አድርገዋል።
አንድ ዘመዴ የተባለ ታዳጊ ደግሞ “እናት እና አባቴ የት እንዳሉ አሁን አላውቅም፤ ጥይት ሲተኩሱብን ነው የተለያየነው” በማለት ሐዘኑን በእንባ አጅቦ ተናግሯል። በወቅቱ ከፌዴራል መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የእጅ ስልክ ላይ ቢደወልም ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል።

ይህ ሰቆቃ በተፈጸመ በኹለተኛዉ ቀን በዚሁ ዞን ሌላ ግድያ ተፈጽሟል። የመከላከያ ኃይል አካባቢውን ለቆ ሲወጣ ሕዝቡ “ገላችሁን ሒዱ ወይም ይዛችሁን ሒዱ” ብሎ የመከላከያ ተሽከርካሪ (ኦራል) አግዶ ቢለምንም፣ መከላከያም “ታዘን ነው የወጣነው” የሚል አጭር መልስ ሰጥቶ ጥሎ ወጣ። ኦነግ ሸኔም በመከላከያ እግር ገብቶ የቀበሌውን ሕዝብ ለስብሰባ እፈልጋችኋለሁ ብሎ የተኩስ እሩምታ በመክፈት በአንድ ቀን ብቻ ከ200 በላይ ንጽኃን ሰዎች በግፍ እንደገደለ ነው ከሞት የተረፉት የተናገሩት።
“እባካችሁ ለወሬ ነጋሪ እንኳን አትርፉን” ሲሉ ሰቆቃቸዉን በየጫካዉ እየሸሹ መናገራቸዉን በርካታ መረጃዎች ጠቁመዋል።

በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ድልድላ ሰቀጀርቢ ላይ በኦነግ ሸኔ ጥቃት የተገደሉት አስከሬናቸው እየተነሳ እያለ ሌላ ጥቃት እየተፈጸመ እንደነበረ በጊዜዉ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በዞኑ በጃርቴ እና በአእምሮ ወረዳ በሚገኙ የሐሙስ ገበያ እና የወበራ ቀበሌዎች “የሽብር ቡድኑ ቤት ንብረታችንን ከዘረፈ በኋላ አሁን ደግሞ የለበስነውን አልባሳት ከገላችን ላይ እየገፈፈ ነው” ሲሉ ነዋሪዎቹ መናግራቸዉ ይታወሳል።

ቡድኑ እስካሁን አንዳንድ አነስተኛ ከተሞችን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ በሚያደርገው እንቅስቅሴም ተሽከርካሪዎችን ይጠቀማል። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት ከጫካ እየወጡ ሳይሆን፣ በከተሞች ዙሪያ ከመሠረቱት ካምፕ ወደ ገጠር በመውረድ ነው። ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ በገጠር ያለው አርሶ አደር እየሸሸ የነበረዉ ከአስፓልት መንገድ እርቆ ወደ ጫካ ነበር ። ግድያዉ አየቀጠለ ሔዶ በዛዉ ተመሳሳይ ሳምንት፣ በምስራቅ ወለጋ በአንድ ቀን አዳር 29 ሰዎች ታርደው መገኘታቸውን ተዘግቦ ነበር። ይህ ሁሉ ስቃይ በዜጎች ላይ ሲፈጸም የክልሉ አልያም የፌዴራሉ መንግሥት አንደበይ ተመልካች እጁን አጣጥፎ መቀመጡ ነዋሪዎቹን ያሳዘነ ድርጊት ነዉ። የመንግሥት አካል ሲጠየቅ ኃይል የለኝም ከማለት በዘለለ ችግራቸዉን ለማድመጥ እንኳን ዝግጁነት እንዳልነበረዉ ነዋሪዎች አሁንም ይናገራሉ።

መንግሥት የመጀመሪያ ሥራዉ የሆነውን የሚመራዉን ሕዝብ ደኅንነት ለማረጋገጥ ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል። የክልሉ መንግሥትም ችግሩ ከአቅሙ በላይ ከሆነ ለፌዴራሉ መንግሥት ማሳወቅ ይገባዋል። ይህ ባልሆነበት ኹኔታ ጉዳት የደረሰባቸዉ ዜጎች መንግሥትን የክፉዉ ድርጊት ተባባሪ እንደሆነ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። አዲስ ማለዳን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትን ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቁም ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው መንግሥት የዜጎቹ ደኅንነት አያሳስበዉም ወይ ወደሚለዉ ድምዳሜ እንዲደረስ ብዙዎችን አድርጓል።
ግድያዉ በ 2014ም አላባራም። በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ አስራ ስድስት ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ መስከረም 7 ቀን 2014 በስለት ተገድለው መገኘታቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዜና ምንጮች ተናግረዋል ።

ታጣቂዎቹ በወረዳው ቦቃ በተባለች ቀበሌ ውስጥ ድንገት በመግባት አስራ ስድስት ሰዎችን አፍነው ውልማይ ወደሚባል አካባቢ ይዘዋቸው እንደሄዱ እና ኹሉንም በስለት ቆራርጠው እንደገደሏቸው ቤተሰቦቻቸው አስረድተዋል። የቦቃ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሸሽተው የወረዳው መቀመጫ ወደሆነችው ኪረሙ ከተማ መግባታቸውን ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል።

“የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጠንከር ሲሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይመጡና ተደራጅታችሁ ተከላከሉ ይሉናል። ሕዝቡ ወጥቶ በኦነግ ሸኔ ላይ ጥቃት ሲፈጽም ደግሞ ኦሮሞ ገደላችሁ ይሉናል” ሲሉ ነዋሪዎቹ ያሉበትን የችግር አዙሪት ያብራራሉ።
ከስር ኦነግ ሸኔ በግፍ ያባርረናል፣ ከላይ የመንግሥት ሰዎች ተመለሱ ብለው ወደ ገዳዮቹ ይመልሱናል የሚሉት የግፉ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች፣ እየሞትን ያለነው ከታችም ከላይም ነው ይላሉ። ሞታችንን እንኳ ምናለ በአግባቡ ቢሰማ እያሉም ይወቅሳሉ።

ከጥቅምት 6፣2014 ጀምሮም ለተከታታይ ለአራት ቀናት በምስራቅ ወለጋ የከፋ የዜጎች ግድያ ተፈጽሟል። ከ43 ሺሕ በላይ ዜጎችም ጥቃቱን በመሸሽ ተፈናቅለዉ እንደሚኙ የዞኑ አስተዳደርና የጸጥታ አካላት አስታዉቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በበኩሉ ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት በምስራቅ ወለጋ በሚገኙ ሊሙ፣ ጉደያ ቢላ፣ ኪረሙ፣ሌቃ ዱለቻ፣ በዲጋና ቸከሆሮ በሚባሉ 5 ወረዳዎች እና ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ ኡሙሩ ወረዳ መሆናቸዉን ዘርዝሯል።

አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፣ ለነገ ሳይል፣ በክልሉ የሚገኙትን፣ ከሞት የተረፉትን ሕይወት እንዲታደግ በተደጋጋሚ ጥሪ ይቀርባል።

አዲስ ማለዳም ስለተፈናቃዮቹም ሆነ በአካባቢው በሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ ስለሚፈጸም ጥቃት በየጊዜው ዘገባዎችን ስትሠራ ቆይታለች። አርሶ አደሩ በየተገኘበት ከሚፈጸምበት ግድያ ባሻገር ንብረቱ ይዘረፋል። ነጋዴውም ሸቀጡን ይዞ ሲወጣ እየተነጠቀ ለተደጋጋሚ ኪሳራ መዳረጉ መዘገቡም ይታወሳል።
በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ዜጋን በየጊዜው እንደሚገድል የሚነገርለት ኦነግ ሸኔ፣ በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ከተባለ ወዲህ ያን ያህል ለውጥ እንዳልመጣላቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። እንደሰሜኑ ጦርነት የወለጋው ጉዳይ ትኩረት ባለማግኘቱ አሁንም ግድያውና መፈናቀሉ አልቆመም። አልፎ አልፎ ዕርምጃ ተወሰደ እየተባለ በሚዲያ ጭምር ቢነገርም፣ ለወሬ ሽፋንና ሕዝቡን ለማረጋጋት ካልሆ በቀር መሬት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አለማምጣቱን ለማየት ከሚፈጸመው ግድያ መደጋገም መረዳት ይቻላል።

ለመንግሥት እጅ ሰጡ፣ ተጸጽተው ተመለሱ ተብለው አቀባበል የሚደረግላቸው የታጣቂ ቡድኑ አባላት ጉዳይም ብዙ መነጋገሪያ የሆነ ነው። የቡድኑን ባንዲራ እንደለበሰ ከመንግሥት እጅ መግባቱ የሚነገርለት የአሸባሪ ቡድን አባል በምን ሕግ መሠረት ይቅርታ ተደርጎለት ወደ ማኅበረሰብ እንደሚቀላቀል የተብራራ ነገር አለመኖሩ ብዙዎችን ቅር እያሰኘ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ቤተሰብ የሞተባቸው፣ ንብረት የወደመባቸውና ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች እንዲህ ዓይነት ተግባርን ሲያዩ በመንግሥት ላይ ያላቸውን አመኔታ እንዲያጡ ያደርጋል ብለው ሒደቱንም የሚተቹ አሉ።

በወለጋ የሚኖሩና የጥቃት ዒላማ የሚደረጉት የሕብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው የጸጥታ ኃይሎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይህ ሆኖ ሳለ የጸጥታ አካሉ ነዋሪውን ለአደጋ አጋልጦ የሚወጣበት ሁኔታን መርምሮ መንግሥት ውስጥ ሆነው ሌላ ተልዕኮን የሚያስፈጽሙ ስለመኖራቸው አመላካች መሆኑን የሚጠቁሙ አሉ።

የወለጋ ጉዳይ ሰው ሲገደል እየተነሳ መፍትሔ ሳይፈለግለት እየተዳፈነ ሲቆይ፣ መልሶ ግድያ ሲፈጸምና መነጋገሪያ ሲሆን በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለው ችግር ላይ ሌላ ተደራቢ ችግር ከመፈጠሩ በፊት መንግሥት እንደሌላው አካባቢ ለቦታው ትኩረት ሰጥቶ ሕዝቡን ከጥቃት ሊታደግ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ቢነገርም ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ካልቻለ ቢያንስ ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲያድኑ ሊፈቅድና ሊያግዛቸው ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com