የእለት ዜና

ሱስና ሱሰኝነት

ቸርነት አዱኛ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው። የገቢ ምንጩ የቀን ሥራ ሲሆን፣ በሥራ ቦታ ከተዋወቃት የአሁኑ ባለቤቱ ጋር አንድ ወንድ ልጅ አፍርተው ነበር። ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት ግን ያላሰቡት ክስተት ገጠማቸው። የ16 ዓመት እድሜ ላይ የነበረው የመጀመሪያና ብቸኛ ልጃቸው በድንገት የሆድ መቁሰል ሕመም አጋጠመው። ቸርነትና ባለቤቱ ልጃቸው እንዲድንላቸው በተቻላቸው አቅም ሁሉ ታገሉ። ልጃቸውም የሕክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ በመጨረሻም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

‹‹ልጄን በድንገት ካጣሁት በኋላ ሕይወት ጨልሞብኝ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እንደሚባለው አባባል መኖርን ቀጠልኩ።›› ይላል ቸርነት። ከዛ በኋላ በተከተሉት ዓመታት ቸርነት እንደ ቀደመው ጊዜ ወደፊትን ተስፋ እያደረገ መሥራትም ሆነ ለተሻለ ኑሮ ጥረት ማድረግን ተወ። ከቤተሰቡ ጋር መስማማት አቁሞ በየዕለቱ ጭቅጭቅ ውስጥ ገባ።

ቸርነት ለወትሮው የቀን ሥራ ሠርቶ ወደ ቤቱ በሚሄድ ሰዓት በሞት ለተለየው ልጁ የሚያስፈልገውን ይዞለት ይሄዳል። ልጁም ከበር ላይ ጠብቆ ይቀበለው ነበር። ነገር ግን አሁን ልጁን ማየት፣ ማቀፍና አብሮት መሆንን እንደማይችል ትዝ ሲለው፣ ትውስታውን መሸሽ ሲፈልግ አካባቢው ላይ በሚገኙ የምሽት ቤቶች ጎራ ማለት እንደጀመረ ያስታውሳል። በድንገት ከገጠመው የሀዘን ስሜት ለመውጣት የጀመረው ልምድም ቀስ በቀስ ከፍተኛ ሱስ ውስጥ እንደከተተው ያወሳል።

ሲውል፣ ሲያድር፣ ሲከርም ቸርነት የአልኮል መጠጦችን በተገኘው አጋጣሚ ከመጠጣት ወደኋላ የማይል ሰው ሆነ። በጠዋት ቀኑን የሚጀምረው አልኮል ተጎንጭቶ፤ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ በመሆኑም በሚኖርበት አካባቢ ጠጥቶ በመንገዳገድ ታዋቂ የሆነ ሰው ሆነ።
ቸርነት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ ከዚህ አልፎም የአልኮል መጠጥ ሱስ በሽታ የመከላከል አቅሙን አዳክሞ በጤናው ላይ እክልን ፈጠረበት። በተጨማሪም ከቀን ሥራ የሚያገኘውን ገቢ ለመጠጫ በማዋሉ ከባለቤቱ ጋር መግባባት እንዳቃተው፣ በወቅቱ የቤት ኪራይ መክፈል እንደተሳነው እና በኑሮ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንዳሳደረበት ያስታውሳል።

በሕይወቱ ውስጥ የሱስ አስከፊነት ተመልክቶ ለማቆም ቢሞክርም እንደ አጀማመሩ በቀላሉ ሊተወው አልቻለም። አንድ ልጁን በድንገት በሞት ካጣው ዓመታት ቢቆጠሩም፤ ሀዘኑን ለመርሳት የገባበት የአልኮል መጠጥ ሱስ አብሮት እንደቀረ ይናገራል። ‹‹አትጠጣ እንጂ! ለምንድን ነው የምትጠጣው? ብሎ የሚጠይቅ ማንም የለም። እኔ ልጄ ዳግም ላይመለስ እንደሄደ እያወቅኩም መናፈቄን አልተውኩም።›› አለ ቸርነት፤ በሐዘን መንፈስ ሆኖ።

ሌላ ታሪክ፤ ‹‹እንደ ቀልድ ለጥናት በሚል ከዶርም ጓደኞቼ ጋር በዩነቨርሲቲ አካባቢዎች ተማሪዎች በኅብረት ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ውስጥ እየሄድን ነበር መቃም የጀመርነው።›› የምትለው እመቤት ስዩም ናት።
እመቤት ትውልድና እድገቷ ባህርዳር ነው። ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ወደ ሌላ ከተማ ተሻግራ የማኔጅመንት ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች። የኹለተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ነበር የምታጠናው ትምህርት ስለከበዳት ለማንበብ በሚል ሰበብ ጫት መጠቀም የጀመረችው። የዶርም ጓደኞቿ ከዛ ቀደም ‹ጫት ከተቃመ በኋላ የሚጠናው ጥናት አይረሳም› እያሉ ይነግሯት ነበርና፣ የከበዳትን ትምህርት ቀላል እንዲያደርግላት በሚል እየቃመች ማንበብን ተያያዘችው።

ለጥናት ብላ የጀመረችው ጫት መቃም ልምዷ ሆነ። ካልቃመች ድብርት፣ መጨናነቅ እና እረፍት ማጣት ውስጥ ትገባ ጀመር። ያም ብቻ አይደለም፣ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ገጠማት። ትምህርቷንም በሚሰማት ተለዋዋጭ ስሜት የተነሳ በስርዓት መከታተል እንዳቃታት እመቤት ለአዲስ ማለዳ ትገልጻለች።
አሁን እመቤት ትምህርቷን ለመጨረስ አንድ ዓመት ይቀራታል። ከጫት ሱስ የጸዳ ሕይወት ለመኖር ፍላጎት ቢኖራትም እንደ ቀልድ ለጥናት ብላ ከገባችበት ሱስ እንደ ቀላል መውጣት እንዳቃታት ጠቅሳለች። ያለባትን ሱስ ለማቆም ሙከራዎች እያደረገች ቢሆንም ከምርቃት በኋላ ወደ ቤተሰብ ስትመለስ የሚኖራት የሕይወት ዘይቤ ግን ገና ከአሁኑ ጭንቀት ውስጥ ከቶኛል ትላለች።

ማንኛውም ሰው ለራሱ፣ ለቤተሰቡም ሆነ ለአገር ሲል ከተለያዩ ሱሶች መቆጠብ እንደሚያስፈልገው እና ተማሪዎች ለትምህርት፣ ለጥናትና መሰል በሚሉ ምክንያቶች ብለው የማያውቁትን ነገር እንደ ቀልድ ባይገቡበት መልካም ነው ስትል ትመክራለች። ‹‹ምክንያቱም እኔ እንደ ቀልድ ገብቼ ሕይወቴ ላይ እንድቀልድ ሆኛለሁ።›› ስትል ትናገራለች።

አዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ በሱስ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ እነዚህ ከላይ የተነሱ ባለታሪኮች፣ ከገጠማቸው አስከፊ እና ጎጂ የሥነ ልቦና እንዲሁም የኢኮኖሚ ጫና ለመውጣት የተለያዩ ሙከራዎችንም በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳም ይህ ጉዳይ በማንሳት ከተለያዩ ባለሞያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርጋለች።

‹‹አንድን ነገር ደጋግሞ ማድረግና ይህን ድርጊት ሳያከናውኑ በመቅረት ምክንያት በሰው ላይ ድብርት እና ምቾት ማጣት የሚሰማ ከሆነ፣ በድርጊቱ ሱስ ውስጥ ገብቷል ይባላል።›› ያሉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና መምህር ግሩም ሰብስቤ ናቸው። በማኅበረሰቡ ዘንድ ሱስ ተብለው የሚታሰቡት ጫት፣ ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ ሺሻ እና አደንዛዥ ዕፆች ሲሆኑ ሌሎች እንደ ወሲባዊ ግንኙነት፣ የጸብ እና መሰል ጎጂ ልምምዶች መኖራቸውን አንስተዋል።

መምህሩ ከሦስት ዓመት በፊት በአዳማ ከተማ ቤት ለቤት እና በማኅበረሰብ ላይ በሠሩት ጥናት 422 ናሙና ወስደው፤ ከዛ መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች መካከል ከጫት፣ ሲጋራ እና አልኮል እንዲሁም ሺሻ በአጠቃላይ ወይም ከእነዚህ በአንዱ ሱስ ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጠው እንደነበር ያወሳሉ።

በጥናቱ ውስጥ ‹ማኅበረሰቡ ለሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች መጠቀም ያጋልጣል የሚሉት ምንን ነው?› የሚለው ጥያቄ የተካተተ ሲሆን፤ ሰዎች በአቻ ግፊት፣ በብስጭት፣ ለመዝናናት በሚልና ባለማወቅ እንደገቡበት መልሰዋል። ሰዎች ሱስ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሱሱ ለጊዜው ደስተኛ ቢያደርጋቸውም ደግመው ወደ ድብርት ስለሚገቡ ከሱስ ለመላቀቅ ፍላጎት ቢኖራቸውም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያቅታቸው በጥናቱ የተሳተፉ መልስ ሰጪዎች ገልጸዋል ሲሉ መምህሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰዎች ሱሱኛ መሆናቸው ለትዳር መፍረስ፣ ለገንዘብ እጥረት፣ ለአካላዊ እና ለሥነ ልቦና ችግር መጋለጣቸውን በሚመለከትም ጥናት እንዳደረጉ ያወሳሉ። የሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ ሰዎች እንዲሁም ከሱስ ለመውጣት ፈልገው ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያላወቁትን በሚመለከት፤ በአንጻሩ ወደ በጎ ልምምድ መቀየር፣ ሱሰኛ ከሆኑ ሰዎች እና ለሱስ በብዛት አጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች መራቅን ለማስተማር እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

ይህን ጉዳይ በሚመለከት የሥነልቦና ባለሞያ እና የሕይወት አሠልጣኝ (life coach) ኤባ ተስፋዬ (ኤባ.ቲ) ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል። እንደ ኤባ ገለፃ ሰዎች ወደ ሱስ የሚገቡበት ምክንያት የሚለያይ ሲሆን በአብዛኛው ግን አንድ ሰው ከሌላኛው ሰው ጋር እንጂ ለብቻ ሆኖ ሱስ ውስጥ የመግባት ልምድ የለውም ብለዋል።

ሰዎች ከቤተሰባቸው፣ ከጓደኛቸው፣ ከሚመለከቷቸው ፊልሞች፣ ከሚወዷቸው ሰዎች እና ከማኅበረሰብ በሚሰጠው አመለካከት ምክንያት ወደ ሱስ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

‹‹ሱስ እንደዓይነቱ በሰው ላይ የሚያደርሰው የአካል እና የሥነ ልቦና ተፅዕኖ የሚለያይ ነው›› ብለዋል። በአካል ላይ ለምሳሌ አልኮል መጠጥ የሚጠጣ ሰው ካልጠጣ የአካል መንቀጥቀጥ ሊያደርስ ይችላል፤ ከሥነ ልቦና አንፃር ሰዎች ለድብርት፣ ለጭንቀት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የእንቅልፍ እጦት እና በሽታ የመከላከል አቅምን መቀነስ ያስከትላል ብለዋል።

ኤባ ከሱስ ሕይወት ለመላቀቅ እንደ አንድ መፍትሄ የሚያነሱት ከሱስ ማገገሚያ ማዕከልን ነው። ሱስን በአንዴ በቀጥታ ከማቆም መጥፎ የሆነውን ልምድ ወደ ጥሩ ልምድ መተካት እንደሚገባም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት ከሚፈለጉበት መጠን አንፃር ጥቂት በመሆናቸው በሰፊው መሠራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አማኑኤል ሰለሞን የአዲስ ሕይወት የእጽና አልኮል ሱሰኝነት ሕክምናና ማገገሚያ ማዕከል (New Life Rehab Center) አስተዳዳሪ ናቸው። ማዕከሉ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሳይካትሪስት በሆኑት በነርስ ይገዱ ሀብቱ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2016 በእንቁላል ፋብሪካ አካባቢ የተመሠረተ ማዕከል ነው።

አማኑኤል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የነርስ ይገዱ ልጅ በሱስ ውስጥ የነበረና በኋላም ከሱስ መላቀቁን መነሻ በማድረግ ይህ ማዕከል ሊመሠረት እንደበቃ አውስተዋል። የሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን፤ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጫትና አደንዛዥ ዕጽ በሚወስዱ በየትኛውም የዕድሜ ክልል እና ፆታ ላይ የሚገኙ ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ በመሄድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም አንስተዋል።

ማዕከሉ ሱስ ውስጥ የገቡና የነበሩ ከ291 በላይ ታካሚዎች በተኝቶ ማከም እና ከ380 በላይ ታካሚዎች በተመላላሽ እያገለለ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ባላቸው አቅም ለ12 ወንዶች ብቻ ተኝተው እየታከሙ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም የቅድመ ሱስ መከላከያ ትምህርትና ሥልጠናዎችን ለወጣቶች ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ሰለሞን አረዳድ በኢትዮጵያ ካለው የሱስ አምጪ ንጥረ ነገር ተጠቃሚ ብዛት አንፃር አገልግሎት የሚሰጡ ከሱስ ማገገሚያ ማዕከላት እጥረት አለ። በመሆኑም በመንግሥት እና በሚመለከታቸው አካላት በኩል ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com