የእለት ዜና

መፍትሔ ያልተቸረው የጦርነቱ ቀጠና

አፈወርቅ እንዳየሁ በአማራ ክልል መቄት ወረዳ ሸደሆ መቄት ሆስፒታል በፋይናንስ ሥራ አገልግሎት እየሰጡ የቆዩ ናቸው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ከሐምሌ ማገባደጃ 2013 ጀምሮ በአካባቢው ነዋሪዎችና በራሳቸው ላይ የደረሰባቸውን ድርጊት በምሬት ያስታውሳሉ። ግለሰቡ እስካሁን መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ እንዳልቸረው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደሚከተለው ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

በመቄት ወረዳ በነበሩበት ወቅት በታጣቂ ቡድኑ በደረሰባቸው ድብደባ፣ አካባቢውን ሲያስታውሱ የማይረሳ ጠባሳ እንዲያድርባቸው እንዳደረገ ይናገራሉ። አፈወርቅ የመቄት ወረዳ ነዋሪዎች ኹሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠዋል። የሞት ዕጣ ፈንታ ከደረሰባቸው ንጹኃን ዜጎች ይልቅ ጠዋሪ፣ ቀባሪ አጥተው የሚንከላወሱ አዛውንቶች እና በየፀበል ቦታው ተጠግተው የዕለት ምግባቸውን ለመለመን ሲንከራተቱ የተመለከቷቸውን ጨቅላ ሕፃናት ሲያስቡ ወደማይቀረው ሞት የሔዱት እንደሚሻሉ ያወሳሉ።

አፈወርቅ ባሳለፍነው ሐምሌ 27/2013 የሕክምና ቀጠሮ ሰለነበራቸው ወደ ባህር ዳር ከተማ በማቅናት የሕክምና አገልግሎቱን አግኝተው ወደ መቄት ወረዳ፣ ገረገራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የመኖሪያ ቦታቸው ከምሽቱ ኹለት ሰዓት እንደገቡ ይገልፃሉ።
ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ግን ሁኔታዎች ተቀያይረውባቸዋል። መከላከያና ልዩ ኃይሉ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ቦታውን ሲቆጣጠር ሊያደርስ በሚችለው የጥቃት ስጋት የተናጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሐምሌ 28/2013 እረፋዱ ላይ ቤታቸውን ለቀው ሠላም ወዳለባቸው አጎራባች ቦታዎች ሲተሙ ተመልክተዋል።

ሁኔታው ያላማራቸው አፈወርቅ ልጆቻቸውን ሠላም ወዳለባቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ማድረስ እንዳለባቸው ተገንዝበው ወደ ተግባር ቀየሩት። ልጆቻቸውን ወደ ገዳምና ወደ ቤተሰቦቻቸው አድርሰው ንብረታቸውን ለመጠበቅ ወደ ቤታቸው እንደተመለሱ አካባቢው የተለመደውን ሠላም ሳያጣ ቢቆያቸውም፣ በማግስቱ ግን ነገሮች እንዳልነበሩ ሆነዋል ይላሉ።

ሐምሌ 29/2013 በመቄትና በዋድላ ድንበር ላይ ከባድ ውጊያ ሳይከፈት እንዳልቀረ አፈወርቅ እንዳየሁ ሲያስረዱ ይደመጣሉ።

ነገር ግን የተጀመረው ጦርነት ሥራችውን ሊገድበው እንደማይገባ ያመኑት አፈወርቅ፣ የተለመደውን ሥራቸውን ለመከወን ወደ ሸድሆ መቄት ሆስፒታል በማቅናት 34 ታካሚዎችን በማገልገል ቢቆዩም፣ ከምሽቱ ኹለት ሰዓት ገደማ ወደ ሆስፒታሉ ጥቃት በመሠንዘሩ የሞቱትም ሞተው ያሉት ደግሞ የህወሓት ታጣቂ ቡድኖች ከሆስፒታሉ እንዳስወጧቸውና የሞቱትን ሰዎች ለመቅበር ቢለምኗቸውም ታጣቂዎቹ ስላልፈቀዱ አስከጧት ሳይቀበሩ እንዳደሩ አብራርተዋል።

አፈወርቅም ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው የህወሓት ታጣቂዎች እጅ ከገቡ ጀምሮ ታጣቂ ቡድኑ “አንተ ፖሊስ ወይም ታጣቂ ነህ፤ ስለአካባቢው ያለውን እውነታ አውራ” በማለት እንደጠየቋቸውና ፖሊስም ታጣቂም እንዳልሆኑ ቢነግሯቸውም ሊያምኑዋቸው ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ለድፍን ሦስት ሰዓት እንደበደቡዋቸው ሲያስታውሱ፣ ሰው ሆኖ የመፈጠር ጥላቻ እንዳደረባቸው ይናገራሉ።

ከድብደባው በተጨማሪ ስልካቸውን በመውሰድ አሳፋሪ ተግባርንም እንደፈጸሙባቸው ያመላከቱት አፈወርቅ፤ “አሁንም ቢሆን ተደምስሰዋል፣ ሠላም ነው ይባላል እንጅ” እስካሁን የአካባቢው ማኅበረሰብ እየሞተ ነው ያለው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰሞኑን በመቄት አካባቢ የደረሰውን የበቆሎ እሸት አገዳው እንኳን ሳይቀራቸው ጭነው እየወሰዱ ነውና መንግሥት ሠላም ያለበትን የኦሮሚያ አካባቢ ሰብልን ከመጎብኘት ጦርነቱ ባለበት አካባቢ የሚሞቱ ንጹኃንንና በታጣቂ ቡድኑ የሚጫነውን ሰብል ሊጎበኝና መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

በአገራችን የተጋረጠው ጦርነት ምንም መፍትሔ ሳይበጅለት በየወቅቱ የበርካታ ንጹኃን ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ ነዋሪዎችን ከቀያቸው እያፈናቀለና በመንግሥትና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ውድመት እያስከተለ መሆኑ ከተሰማ ዓመት ሊሞላው ትንሽ ቀናት ብቻ እንደቀሩት ይታወቃል።
ለዚህም እስካሁን የሆነውንና እየሆነ ያለውን ችግር መመልከትና በየወቅቱ የሚዘግቡትን የውስጥና የውጭ የሚዲያ ተቋማትን ዘወር ብሎ ማየት በቂ ነው።

ጦርነቱን ቀልብሶ ሠላምን ለማስፈን ኹሉም ሰው ኃላፊነት እንዳለበት ቢታመንም፣ ለችግሩ መፍትሔ ማጣት ዋነኛ ምክንያቱ የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣት ነው በማለት ቅሬታ የሚያቀረቡ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል።
ምንም አንኳ ማንኛውም ሰው ሠላምን የማስፈን ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ብዙኀኑ ሰሞኑን ለሚስተዋለው ለችግሩ መባባስ እንደምክንያት የሚጠቅሱት መንግሥት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ጀምሮ “ስልታዊ ማፈገፍፈግ” በሚል ሰበብ ለተቃሪኒ ቡድኑ ከባድ መሣሪያን እያስረከበ ሕዝቡን የማስጨረስ ተግባሩን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው የጥቅምት 2014 የመጀመሪያ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ያደረጉት የሰብል ጉብኝትና ያስተላለፉት መልዕክት በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉትን ዜጎች የዘነጋ ነው የሚለው ጉዳይ ሰሞኑን በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ ሰሞኑን ያደረጉት የስንዴና የቦለቄ ምርት ጉብኝት መልካም ጎን ቢኖረውም፣ “መጀመሪያ መቀመጫዬ ላይ ያለ እሾህ ሊወጣ ይገባል” እንዲሉ በየጊዜው ሞትና ዝርፊያ እያጋጠማቸው መሆኑን ደጋግመው የሚናገሩ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉ ዜጎችን ችግር ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ የቸልተኝነት ድርጊት ነው የሚሉ በርካታ ቅሬታ አቅራቢዎች አሉ።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ከሰጡት ግለሰቦች መካከል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ወጣት፣ ስለ “ማጀቴ ያረጀ ችግር” መፍትሔ አለማግኘት፣ ከሰሞኑ የመንግሥት የሰብል ጉብኝትና በማጀቴ የአርሶ አደሮች ጤፍ ከመቃጠሉ ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ወጣቱ አንደሚናገረው ከሆነ፤ “ማጀቴ” በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኝ የወረዳ ምድቧ የማይታወቅ ከተማ ናት። ከተማዋ በ1987 በደረሰባት የጎርፍ አደጋ ወረዳነቷ ወደ መኮይ (አንጾኪያ) ወረዳ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ለብዙ ጊዜ የወረዳ ይመለስልን ጥያቄ እስከ ፌደራል መንግሥት ድረስ ተጠይቆ ምንም አይነት መፍትሔ እንዳልተገኘለት ያወሳል። በ2008 በዚሁ ተመሳሳይ ጥያቄ ምክንያት በአካባቢው ነዋሪች ዘንድ መናቆር እንደተፈጠረና በኋላም መንግሥት ውሳኔ ሳይሰጠው እንደቀረ አስታውሶ፣ በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች እርስ በእርሳቸው መቃረናቸው ሰሞኑን ለተቃጠለው የአርሶ አደር የጤፍ ክምር “ኦነግ ሸኔን መርተው ያሳዩት በዚህ ጉዳይ ቂም የያዙ ሰዎች” ሊሆኑ እንደሚችሉ የብዙዎች ጥርጣሬ ነው ሲል ይናገራል።

ወጣቱ አያይዞም ይህ ያረጀ ችግር መንግሥት መፍትሄ ቢሰጥበት ኑሮ እየደረሰ ያለው መፈረካከስ ባልደረሰ ነበር ያለ ሲሆን፣ ሰብል ከመጎብኘት በፊት ለሚቃጠሉ ሰብሎች ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችንና ሽብርተኛ የተባሉት ኦነግ ሸኔና ህወሓት በንጹኃን ላይ የሚያደረሱትን ግፍ ማስቆም ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ሲል ነው አስተያየቱን የሰጠው።

ሌላው ቅሬታ አቅራቢ ጌጥዬ ያለው የተባሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሲሆኑ፣ “ብዙዎች ቅሬታ አንስተዋል፤ ቅሬታውም እውነተኛና የማያሻማ በመሆኑ እኔም አንዱ ቅሬታ የተሰማኝ አካል ነኝ” በማለት ንግግራቸውን ጀምረው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት በሚከተለው መልኩ ተናግረዋል።

እየተነሳ ያለው ቅሬታ እውነተኛና ተገቢ ነው የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ ከሞት አፋፍ ላይ ያለን አካል ቸል ብሎ ምንም ችግር ያልደረሰበትን ሰብል ከመጎብኘት ይልቅ፣ መንግሥት በቅድሚያ በጦርነት እየሞቱ ላሉት ንጹኃን ዜጎች የመከላከያ ሠራዊቱን በማጠናከር ችግራቸውን ሊቀርፍ ይገባ ነበር ብለዋል።
ጌጥዬ አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ላይ በነበረው የስንዴና የቦለቄ ጉብኝት ስለኮምባይነርና ስለፓምፕ እያብራሩ መሰንበታቸው መልካም ድርጊት ቢሆንም፣ በአንጻሩ በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ወራቶችን ላስቆጠረው ግድያና የንብረት ውድመት ቅድሚያ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባ ነበር። አክለውም ይህ አለመድረጉ ለችግሩ አትኮሮት አለመስጠቱን ከማመላከት ሌላ ምን ስያሜ ሊሰጠው ይችላል? በማለት ጠይቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል በግብርናው ልማት እንቅሰቃሴ ዙሪያ አሁን ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ሲወሳ አስተውያለሁ፣ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ በጦርነቱ እየደረሰ ያለው ችግር ግን ተረሰቷል የሚሉት ጌጥዬ፣ “አማራና ትግራይ እየተጣረሱበት ላለው ጦርነት መፍትሔ መስጠት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ነው ወይ? ለዚህ መፍትሔ ተጠምቶ ላረጀ ችግርስ መከላከያ፣ ልዩ ኃይልና ታጣቂን በማጠናከር ከሰብሉ ጉብኝት ቅድሚያ መደረግ የነበረበት ጉብኝት ሊሆን የማይችልበት መንገድ ምንድን ነው?” በማለትም ነው ተጨማሪ ጥያቄዎቸውን ያነሱት።

አያይዘውም “በኦሮሚያ ክልል ሲደረግ የሰነበተው ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ብቻ እንደሆኑ አድርገው በማሰብ፣ የሌላው ሕዝብ ችግር ግድ የማይሰጣቸው መሆኑን በይፋ ተናግረውበታል ብየ ነው የማምነው” ሲሉ ነው የተሰማቸውን የገለጹት።
አያይዘውም የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ “የሰሜኑ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ለሚመጡት ብዙ ዓመታት የሰሜኑ ሕዝብ አማራውም፣ ትግሬውም እንዲዳከምና እንዳይነሳሳ እየተሠራ ነው የሚሉት ጌጥዬ ያለው፣ ይህም ደግሞ ዝም ብሎ በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን፣ ዓላማው ሌሎችን ኢትዮጵያዊያን በወረራ እየያዘ ማንነታቸውን፣ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ኃይማኖታቸውን እየቀየረ የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ማልማት የሚፈልግ ይመስላል” ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት።

“መንግሥት ሕዝብ በጦርትነት እያለቀ መሆኑን በማንሳት የሕልውና ዘመቻ ያስፈልጋል ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት” እያለ የነበረውን የቀድሞ ቃሉን ሰሞኑን አርሲ ላይ በነበረው የሰብል ጉብኝት “ታጠቅ፤ ተደራጅ፤ ዝመት የሚባል ነገር ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም” ማለቱ “የምን ታመጣላችሁ ተግባር መሆኑንና እናንተ በጦርነት ተፋለሙ፣ የኦሮሚያ ክልል ግን ልማት ላይ ነው” የሚል መልዕክትን የሚያስተላልፍ ነው ብየ ነው የማምነው” በማለት ነው የተገነዘቡትን የተናገሩት።

አያይዘውም ጦርነቱ ገና እንዳልተቋጨ መንግሥት ራሱ በግልጽ እያወቀ፣ ጦርነቱን በመመከት ንጹኃኑን ከሞት መታደግ ሲገባው፣ “መታጠቅ ለትራክተርና ለኮምባይነር ነው” ማለቱ በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልል ከተከሸጸ ጀምሮ መፍትኼ ያልተቸረውን ችግር ቸል የማለት አንድምታን ያመላክታል በማለት ነው አስተያታቸውን የሰጡት።

አክለውም የውጫሌ ከተማ ባሳለፍነው ጥቅምት ስምንት 2014 በሕዝብ ተወካዮች ዘንድ ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው የህውሓት ቡድን የተያዘችው፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ሰብል እየጎበኙ በነበረበት ወቅት “ታጠቅ፤ ዝመት ማለት አያስፈልግም” ባሉበት ማግሥት መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ “በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ” እንዲሉ “መንግሥት በዛን ወቅት ከሰብል ጉብኝት በተጨማሪ የተኩስ አቁም ውሳኔ መልዕክት እንዳስተላለፈላቸው የተግባቡት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልንና ፋኖን ከጎን ጠላት እንዲወጋቸው በመተው አካባቢውን ለቆ በመውጣት ሕዝቡን ለሞትና ለዘረፋ አሳልፎ የመስጠት ተግባር አከናውኗል” ሲሉ አስተያታቸውን ይሰነዝራሉ።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ከአላማጣ ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ተቆጣጥሮታል ከተባለው የውጫሌ ከተማ ለመድረሱ ዋነኛ ምክንያቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን እየተከላከለ እንጅ እያጠቃ ስላልሆነ ነው የሚሉት ጌጥዬ ያለው፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ውጊያ የሚሰነዝረው፣ ተቃራኒ ቡድኑ ወደ መዲናችን ገስግሶ የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል ስትራቴጅክ ቦታዎችን ሲይዝ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ ሲሉ ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስተያየታቸውን የሰጡት።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com