የእለት ዜና

የአዲስ አበባን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ መሠራት አለበት ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ መኪኖች በብዛት መኖራቸው፣ እንዲሁም ከሕዝብ ፍሰቱ እና ከነዋሪው ፍላጎት ጋር ተያይዞ በየጊዜው የተሸከርካሪ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በከተማዋ አየር ንብረት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ለመቆጣጠር በሚያስችል ዕቅድ ላይ ባሳለፍነው ሐሙስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል። የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ በከተማዋ ብሎም እንደ አገር ተሸከርካሪዎች በዓመት ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ በጥናት ስለማይታወቅ ከፍተኛ የሆነ በካይ ጋዝ እንደሚለቁ እንጂ የሚለቁት የበካይ ጋዝ መጠን አይታወቅም ብለዋል። ይህም በከተማዋ ያለውን የአየርን ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር ችግር እንደሚሆን ነው የተጠቆመው። በዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች በከተማዋ የሚገኙ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ተሸክርካሪዎች በዓመት ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑ፣ ብሎም በከተማዋ ምን ያህል ዓመታዊ የኃይል ፍጆታ እንዳለ ጥናት በመሥራት እና የካርቦን ልቀት መጠኑን ለማወቅ እንዲያስችል በማድረግ የከተማዋን አየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ብሎም ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ተብሏል።

መንገዶች ሲገነቡም የአበባና የዛፎች መትከያ ኖሯቸው ለአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ተስማሚ እንዲሆኑ ተደርገው መገንባት አለባቸው ያሉት ተሳታፊዎች፣ ወደ ከተማዋ የሚገቡ አዳዲስ ተሸከርካሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁና አየር ብክለት ችግር የሚፈጥሩ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በማኅበረሰቡ ዘንድ የእግር ጉዞ እንዲበረታታ፣ የብስክሌት አማራጭ በስፋት እንዲኖር፣ እንዲሁም የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያድግ በማድረግ የአየር ብክለቱን ከመቀነስ በተጨማሪ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር ከተማ ለመፍጠር ያግዛል ነው የተባለው። በሌላ በኩል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚያስችል የአምስት ዓመት ዕቅድ ትግበራ ይፋ አድርጓል።

በዚህም፣ እንደ ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ አብዛኞቹ ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ እየጨመረ ባለው የሕዝብ ቁጥር እና ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አደጋ ጋርጦባታል። ጎርፍ፣ ከፍተኛ ዝናብ፣ የሙቀት መጠን መጨመር እና ድርቅ ተደጋጋሚ ክስተቶች ሆነዋል። በከተማዋ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው። ዕቅዱ በዋናነት 14 የቅነሳ እንዲሁም፣ 20 የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ያካተተ ነው ተብሏል።

በዕቅድ ትግበራው ውስጥ ጎርፍ እንዳይከሰት መከላከል፣ የአረንጓዴ ሽፋንን መጨመር፣ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ትኩረት ማድረግ እና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ማዘመን በዋናነት ተጠቅሰዋል።

እንዲሁም፣ በከተማ በሚደረገው ግንባታም ሕንፃዎች ብዙ መስታወት ስለሚገጠምላቸው የሚፈጥሩት የሙቀት መጠን በከተማዋ ላሉ ዕፅዋትና ሌሎች ብዝኃ ሕይዎቶች አስቸጋሪ በመሆኑ አንዱ የትግበራ ዕቅዱ ትኩረት እንደሆነ ተጠቁሟል። የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ዕቅዱ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ፣ በከተማዋ ነዋሪ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች የሚያስከትሉትን እንደ ጎርፍ፣ የውኃ ዕጥረት፣ የመሬት መንሸራተት እና የእሳት አደጋዎች ተጋለጭነትን በመቀነስ የመቋቋም አቅምን እንደሚያሳድግ ተመላክቷል።
ከግለሰብ ጀምሮ፣ ማኅበረሰቡ እና በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ተቋማቶች በጋራ በመሆን ኹሉም የድርሻውን እንዲወጣ መሥራት እንደሚያሰፈልግም ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com