የእለት ዜና

ለድንበር ላይ ንግድ ሕጋዊ አሠራር ይፈጥራል የተባለለት ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

ለድንበር ላይ ንግድ ሕጋዊ አሠራር ይፈጥራል የተባለለት ረቂቅ መመሪያ በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት እየጠበቀ እንደሆነ ተገለጸ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በአግባቡ የተሰነደ ሕጋዊ ማዕቀፍ እና ቅርጽ የሌለውን የድንበር ላይ ንግድን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብሎ ያመነበትን ጥናት ባለድርሻ አካል ለሆነው ጉምሩክ ኮሚሽን መላኩን አስታውቋል።
ረቂቁ የተዘጋጀው በ1994፣ በ16 አገራት የተመሰረተው እና በአሁኑ ጊዜ 21 አባል አገራት ባሉት የጋራ ንግድ ለምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት በሚል የተቋቋመው የተቀላጠፈ የንግድ ስርአት ሰነድን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። በ2010 እኤአ የጸደቀውን የተቀላጠፈ የንግድ ስርአት ሰነድን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ ነው።

ይህ የተቀላጠፈ የንግድ ሥርዓት ከቀረጥ እና ታሪፍ ቅናሽ ጀምሮ፣ ለግብይት የሚቀርቡ ግብዓቶችን ለይቶ የሚያስቀምጥ እንደሚሆን ተጠቁሟል። በተጨማሪም እስከ ምን ያህል ርቀት የድንበር ላይ ነጋዴዎች ገብተው መገበያየት እንደሚችሉ የሚያስቀምጥም ይሆናል።
በድንበር አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች የግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊነትን ያልተላበሰ የሆነው፣ ሥርዓቱ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ መሆኑን ይገልጻሉ። “ኹሉም ድንበር ላይ ያለ ነጋዴ ወደ መሀል ከተሞች ተጠግቶ በመሥራት ምርት ማቅረብ አይችልም፤ ምክንያቱም ኮንትሮባንድ ተብሎ ስለሚወሰድ። ይህም ነጋዴውን ከግምት ያስገባ አይደለም” ሲሉ በቶጎ ውጫሌ ከተማ ነጋዴ የሆኑት ፋራሃን አሕመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በደንበር ንግድ የመገበያያ የቦታ መጠን (ራዲየስ) በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለውም። እስከ ምን ያህል ዶላር ድረስም መገበያየት እንደሚቻል ግልጽ የሆነ ነገር የለም። የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ በመምጣጡ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር ከዚህ ቀደም በኹለቱም አገራት ገንዘብ ይገበያዩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በተለይ ከሱማሊያ ጋር ያለው የንግድ ትስስር እንደሚያሰጋቸው ፋራሃን ገለጸዋል።

ረቂቁ የሚመለከታቸው አካላት ከተወያዩበት በኃላ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚችል እና በመጨረሻም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጎረቤት አገራት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚጸድቅ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኹለትዮሽ ንግድ ትስስር እና ድርድር ዳይሬከተር ገብረጻድቅ ጣሰው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል ። የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደብሌ ቃበታ በበኩላቸው፣ ሕጋዊ ማዕቀፍ ለድንበር ነጋዴዎች መዘጋጀቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ቀጠናዊ ትስስር እንደሚያጎለበት ተናግረዋል። “የኮንትሮባንድ ንግድንም ለመቆጣጠር መልካም ኹኔታን ይፈጥራል። በቀጣይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እየተመካከርን እንሠራልን” ሲሉም ገልጸዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ “ሕገ ወጥ ንግድን የመከላከል አቅም ከመፍጠሩም በላይ የአገሪቱን የገቢ ወጪ ንግድ የምናውቅበት ነው” ያሉት ገብረጻድቅ፣ ሕጉ ሲጸድቅ የአካባቢው ነጋዴዎች መብታቸውን ተጠቅመው የመሥራት ነጻነት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው አሠራር የድንበር ላይ ንግድ፣ በተለይም በኬንያ በኩል፣ ያለምንም ሰነድ እስከ 2000 ዶላር ግብይት የሚፈቅድ ቢሆንም፣ ከነጋዴዎች ጋር በተደረገ ውይይት ወደ 5000 ዶላር እንዲያድግከሞያሌ ከተማ ነጋዴዎች ጥያቄ እንደቀረበ ገብረጻድቅ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ጋር መልካም የንግድ ትስስር ካላቸው አምስት ጎረቤት አገራት አንዷ ኬንያ ስትሆን፣ ከኮቪድ ወረርሽን መከሰት በፊት ባለው ዓመት 75 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሸቀጥ ወደ ኢትዮጵያ ልካለች። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ በ2009፣ 57 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ንግድ እንደፈጸመች የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል። የረቂቁ መዘጋጀት መልካም ጅማሮ መሆኑን በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናት እና ግንኙነት መምህሩ ኡርጌሳ ደሬሳ(ዶ/ር) ጠቁመዋል። ረቂቁ ወደ ሥራ ሲገባ በአገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ማኅበራዊ ትስስር ከማጠናከር በተጨማሪ በሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቸ የሚፈጸመውን ዝውውርን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

መምህሩ አክለውም፣ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን የገበያ ክፍተት በጎረቤት አገራት የገነዘብ ኖት በመገበያየት ክፍተቱን መሙላት ይቻላል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!