የእለት ዜና

ባንኮች ሠራተኛ ለመቅጠር ገንዘብ እየጠየቁ ነው ተባለ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙ ባንኮች ሠራተኞችን ለመቅጠር ገንዘብ እንደሚጠይቁ ተመርቀው ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
አንዳንዴ የሥራ ማስታወቂያው ከወጣ በኋላ ማን እንደሚገባበት አይታወቅም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የተወሰኑ ባንኮች ላይ እስከ 50 ሺሕ ብር ከፍለው የገቡ የምናውቃቸው ሥራ ፈላጊዎች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልግ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘ ሥራ ፈላጊ ወጣት እንደሚለው፣ በኹሉም ባንኮች አይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ ጉቦ እየተቀበሉ ሠራተኛ የሚቀጥሩ ግለሰቦች መኖራቸውን ይናገራል።
ወጣቱ አክሎም፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ባንኮች የበለጠ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ የሚቀጥሯቸውን ዜጎች በዕውቀታቸው መዝነው መሆን እንዳለበት ያስረዳል።

ሌላኛዋ በማኔጅመንት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላትና እስካሁን ሥራ ያላገኘች ወጣት እንደምትለው፣ “ብር ቢኖረኝ ኖሮ ብዙ ባንኮች ጋር የሚያስገቡኝ ደላሎች መኖራቸውን ብዙ ሰው ነግሮኛል። 30 ሺሕ ብር ከፍላ የገባች ልጅም አውቃለሁ። እኔ ግን አሁንም ድረስ ብር ሳይከፍሉ የሚቀጠሩ ልጆችን ስለማውቅ ደጋግሜ እሞክራለሁ እንጅ ብር ከፍዬ አልቀጠርም” ስትል ተናግራለች።

አሁን ላይ የቢዝነስ ትምህርቶች በስፋት ተደራሽ መሆናቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ሰው የዲግሪ ወረቀት የያዘ በመሆኑ፣ በዚያው ልክም እነዚህ የሙያ መስኮች ብዙ የሥራ ቦታዎች ላይ የሚያሳትፉ በመሆናቸው በዘመድ አዝማድና በሙስና ሥራ የሚያገኙ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ እንደሆነ ነው የሚነገረው።
ሥራ ፈላጊዎች ገንዘብ ከፍለው ባንክ እንዲቀጠሩ የሚያደርጉት በባንኮች ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው የሚሠሩ ሰዎች እንደሆኑ፣ በዚህም የፈተና ጥያቄ መስጠት ብሎም ብር እያስከፈሉ ሠራተኛ አድርጎ ማስገባት ዝንባሌ እየበዛ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ገልጸዋል።

ይህም በጥረታቸው ጥሩ ውጤት ይዘው የተመረቁ ዜጎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ ለጉዳት የሚዳርግ እና አገርንም ክፉኛ የሚጎዳ ነው ብለዋል። እንዲሁም ከጥበቃ እና ተላላኪ ጀምሮ እስከ ባለሙያ ድረስ በዘመድና በጥቅማ ጥቅም እንዲገቡ ማድረግ ልማድ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ የባንክ ባለሙያ በበኩላቸው፣ እርሳቸው በሚሰሩበት ባንክ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ የነበረ ግለሰብ የጓደኛውን እህት ሙያዋ ከባንክ ሥራ ምንም ዓይነት ተያያዥነት ሳይኖረው ተላላኪ ሆና እንድትግባ በማድረግ እና በሥራ ላይ እያለችም ትምህርት እንድትማር በማድረግ ዛሬ ላይ ትልቅ ኃላፊነት ላይ እንድትቀመጥ አድርጓል ብለዋል። አክለውም፣ የዚህች ሴት ወንድምም ሌላ ቦታ የተመሳሳይ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆኑ እህቱን ሥራ ላስገባለት ጓደኛው ውለታ እንዲሆን የቅርብ ዘመዱ እንዲቀጠር አድርጎለታል ሲሉ ተናግረዋል።

ባለሙያው በመጨረሻም፣ አሁን ላይ የተሻለ የደሞዝ ክፍያ ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመን እና ብዙ ሰው የዲግሪ ባለቤት ከመሆኑ የተነሳ ተወዳድሮ እንደማይሳካለት የሚያውቀው ሁሉ ከፍ ያለ ብር ከፍሎ መግባት ስለሚመርጥ ችግሩ ስር የሰደደ እና ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ሆኗል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት፣ በማንኛውም ዘርፍ ላይ በሙያው የሰለጠኑ ዜጎች ቢኖሩም በመሀል ደላሎችና ሙስና የሚፈልጉ ግለሰቦች በመብዛታቸው፣ ዕውቀትና ክህሎት የሌላቸው ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ሥራ እየገቡ፣ ገንዘብ ሳይኖራቸው ዕውቀት እና የሙያ ችሎታ ያላቸው ሰዎች እየተማረሩ እና ለጉዳት እየተዳረጉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com