የእለት ዜና

ዙሩ የበዛው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ

ስድስተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ገና ከውጥኑ ጀምሮ የተለያዩ እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደ አጠቃላይ ምርጫነቱ ሳይሆን፣ በተለያየ ጊዜ በዙር የሚደረግ ምርጫ ሆኗል። ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በኮቪድ 19 መካሄድ ባለበት ጊዜ አለመካሄዱን ተከትሎ፣ ለአንድ ዓመት ተራዝሞ ከሰኔ 14/2013 ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ እና መስከረም 20/2014 ከተካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ የቀጠለ ሦስተኛ ዙር ምርጫ ተወልዷል።

ምርጫውን በአንድ ዙር እንዳይጠናቀቅ ዋነኛ እንቅፋት የሆነው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ሲሆን፣ እስካሁን የተካሄዱት ኹለት ዙር ምርጫዎች እንደየቅደም ተከተላቸው ውጤታቸው ታውቆ መንግሥት ተመስርቷል። ምርጫውን በበላይነት ያሸነፈው ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ባሳለፍነው መስከረም 24/2014 አዲስ መንግሥት የመሠረተው በመጀመሪያ ዙር የምርጫ ውጤት ነው።

የምርጫውን ውጤት ተከትሎ አዲስ መንግሥት ይመሥረት እንጅ፣ ምርጫውን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ከመጀመሪያውን እና ኹለተኛው ዙር ምርጫ ውጤት በኋላ የተወለደው ሦስተኛ ዙር ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስደስተኛውን አጠቀላይ ምርጫ በአንድ ቀን ለማካሄድ አስቦ ሲሠራ ቢቆይም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በገጠሙ የጸጥታ ችግሮችና በፍርድ ቤት የተያዙ የምርጫ ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ምርጫውን ከኹለት ዙር አልፎ ወደ ሦስተኛ ዙር ለመግባት ተገዷል።

ምርጫ ቦርደ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ሁኔታ የምርጫ ሒደቱ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከመደበኛ አከባቢዎች አኩል መሔድ አልቻለም። ከጸጥታ ችግር በተጨማሪም በደምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ቦርዱ ችግር እንደገጠመው መገለጹ የሚታወስ ነው።

በዚህም ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል መወሰኑን ተከትሎ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በመጀመሪያው ዙር ባለመጠናቀቁ ወደ ኹለተኛ ዙር መሄዱ፣ ይህም አልበቃ ብሎ ምርጫው ለሦስተኛ ዙር መሽጋጋሩ አልቀረም።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች ውስጥ በአንዱ ብቻ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ እንደሚካሄድ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በመተከልና ካማሺ ዞን ሊካሄድ የሚገባው ምርጫ ወደ ሦስተኛ ዙር እንዲተላለፍ ሆኗል።

ባሳለፍነው መስከረም 20/ 2014 የተከናወነው ምርጫ በሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ በሱማሌ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ደግሞ በኢትዮጵያ 11ኛውን ክልል ለመመሥረት የሚደረገው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔን ጨምሮ፣ እንዲሁም በክልሉ ሰኔ 14/2013 ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የተካሄደ ነው።

ምርጫ ቦርድ ባካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄድ ካልቻለባቸውና ምርጫ ካልተካሄደባቸው አካባቢዎች የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል እና ካማሺ ዞኖች ናቸው። ቦርዱ በክልሉ ምርጫ አለማካሄዱን ተከትሎ አዲስ የሦስተኛ ዙር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል። የሦስተኛው ዙር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውጭ የሚገኙ አካባቢዎች ነገር ግን ምርጫ ያልተካሄደባቸውን ቦታዎች አላካተተም።

ቦርዱ ይፋ ባደረገው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት በክልሉ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ታኅሳስ 21/2014 የደምጽ መስጫ ቀን ሆነ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል። ቦርዱ በክልሉ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከማድረግ የመጨረሻ ውጤት እስከማሳወቅ ያሉትን ዕቅዶች ይፋ አድርጓል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች አከናውኖ ያጠናቀቀ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ምርጫ ባልተካሄደበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ 17 ምርጫ ክልሎች (በአብዛኛው የክልል ምክር ቤት) ምርጫ ያልተከናወነ መሆኑ አስታውቋል።

ቦርዱ በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ባለው የጸጥታ ችግር ምርጫ ማካሄድ አለመቻሉ የሚታወስ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ታኅሳስ 21 ለሚካሄደው ምርጫ ከባለደርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል። ቦርዱ በክልሉ የሚያካሂደው ምርጫ ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ ከሚመለከታቸው ፓርቲዎች፣ የክልል መስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እና ምክክሮችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል።

ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ የያዘውን ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የጸጥታ ሁኔታ ከተፈጠረ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን፣ የጊዜ ሰሌዳውን እና ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን የጸጥታ ሁኔታ ለፓርቲዎች እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅርቤያለሁ ብሏል።

ምርጫን ለማካሄድ በምርጫ ቦርድ እና በጸጥታ ተቋማት መካከል ሊደረጉ ይገባል ያላቸውን የትብብር አጠቃላይ መርሆች ይፋ አድርጓል። ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት በምርጫ ቦርድ እና በጸጥታ ተቋማት መካከል የሚኖረውን ትብብር ግልጽ የሚያደርጉ አጠቃላይ መርሆዎች ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል።

በዚህም ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁስ መመሪያ፣ የመራጮች ምዝገባ መመሪያዎችን፣ የዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ምዝገባ መመሪያ እና የድምፅ አሰጣጥና ቆጠራ መመሪያን ጨምሮ፣ ለምርጫዎች በተቀመጠው፣ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት የጸጥታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ተግባራትና መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች ይጠቁማል ተብሏል። የምርጫ ቦርድ ተግባራትን እና የምርጫ ማስፈጸሚያ መዋቅሮችን(ምርጫ ጣቢያ፣ የዞን ቢሮ፣ የምርጫ ክልል ቢሮ) ደህንነት በማስጠበቅ ተግባር ውስጥ የሚሊሻ አባላት መሳተፍ እንደሌለባቸው በመርሁ ተቀምጧል።
የጸጥታ ተቋማት ለእያንዳንዱ ተግባር የሚያስፈልገውን የጸጥታ ኃይል ቁጥር እና ስምሪት

መወሰን እንደሚችሉም ተጠቅሷል። የምርጫ ሒደት ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት የሰዎች፣ የተቋማትና የቁሳቁስ ደኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ፣ ወቅቱን የጠበቀና ውጤታማ ትብብር መደረጉን ለማረጋገጥ ሲባል ምርጫ ቦርድ በመንግሥት መሪነት በሚዘጋጁ የጸጥታ መድረኮች ለመሳተፍ ሙሉ ፍቃደኝነት እና ፍላጎት አለኝ ብሏል።

በመጀመሪያው ዙር እና በኹለተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ፣ አሁንም በሦስተኛውም ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ምርጫ የማይካሄድባቸው አከባቢዎች አሉ። በሦስተኛ ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ክልሎች ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአማራ ክልል 10፣ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ሲሆኑ፣ በክልል ደረጃ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን በኦሮሚያ ክልል ሰባት እና አማራ ክልል ዘጠኝ ናቸው።

በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት በመጀመሪያውም ይሁን በኹለተኛው ዙርም ምርጫ ያልተደረገባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ማጀቴ (ማኮይ) የምርጫ ክልል፣ አርጎባ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ሸዋሮቢት የምርጫ ክልል፣ ኤፌሶን የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ አርማጭሆ የምርጫ ክልል እና ድል ይብዛ የምርጫ ክልል ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰሜን ሽዋ ዞን ችግር የተከሰተባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ባለመካሄዱ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አሁንም በሦስተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ አካባቢዎች ያሉ ሲሆኑ፣ ቤጊ የምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል (ምዕራብ ወለጋ)፣ አያና የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ ገሊላ የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ አሊቦ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ)፣ ጊዳም የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!