የእለት ዜና

አሜሪካ ለምን በአፍሪካ ቀንድ ያልተገባ ጫና መፍጠር መረጠች?

የዋሽንግተን ሰዎች ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ብሔራዊ ጥቅም (National Interest)ን ነው ። ያ ደግሞ የደኅንነት እና ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎታቸውን ስጋት ላይ የሚጥል መስሎ ከታያቸው ብቻ ነው ።

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ላይ እንዴት?
የሦስቱ የአሜሪካ ሥጋቶች፡-
1) የኢትዮጵያ፣ኤርትራ እና ሱማሊያ ጥምረት
2) የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ
3) ለሰላማዊ የኃይል ፍጆታ የሚውለው የኒዩክሌር ኃይል ከሩስያ ጋር ያደረገችው ስምምነት

1) የኢትዮጵያ፣ኤርትራ እና ሱማሊያ ጥምረት – አሜሪካ በየመን ቀውስ እና በአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ምክንያት ምስራቃዊ የቀይ ባህር ዳርቻን እያጣችው ነው። በዚህም ዋና ኢላማዋ ምዕራባዊ ቀይ ባህር ቀጠና (ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እስከ ሱዳን ወደብ port sudan) ድረስ ያለው ነው። ይህን አካባቢ ደግሞ አዲሱ የኢትዮጵያ፣ኤርትራ እና ሱማሊያ ጥምረት በዘላቂነት የቀጣናውን ችግር በራሳችን እንፈታለን በሚል መንቀሳቀስ መጀመራቸው ዋሽንግተኖችን ሥጋት ላይ ጥሏቸዋል። ለአዲሱ ጥምረት ዋናዋ ሞተር ኢትዮጵያ ነች። ኢትዮጵያን ለእኛ ታዛዥ ማድረግ አለብን የሚል ዕሳቤ እያራመዱ ነው ።

2) የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ – ይህን ቀጠና አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዕለ ኃያላኑ ከባድ እሽቅድድም እያደረጉበት ነው። የጦር ሰፈር ግንባታ እና የወደብ ጂኦ ፖለቲካ ሽኩቻው አይሏል ። ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘንግተውት ነበር። ለነገሩ እርሳቸው እንኳን የዘነጉት ሙሉ አፍሪካን ነበር። ካርቱም ሱዳን ወደብ አካባቢ አዲስ ማዕከል በመመሥረት ከባቢያዊ ቅኝት የማድረግ ጅማሮ አላቸው ።

3) ለሰላማዊ የኃይል ፍጆታ የሚውለው የኒዩክሌር ኃይል ከሩስያ ጋር ያደረገችው ስምምነት
ሩስያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰላሚዊ ኃይል ማመንጫ የኒዩክሌር ግንባታ ሥምምነት ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር እየተፈራረመች ነው። ከኢትዮጵያ ጋርም እንዲሁ ተፈራርማለች። ያኔ የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና የሩስያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ አዲስ አበባ ውስጥ መፈራረማቸው በተሰማ ሰሞን የአሜሪካው ዩኒቨርስቲ ስታንፎርድ በ2018 አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር ። ኢትዮጵያ ወደ ኒዩክሌር ኃይል እየገሰገሰች ነው። ከእርሷ በስተጀርባ ራሽያ አለች በሚል አድልዎ የተጫነው አስተያዬት አስፍሮ ነበር ። ነገሩ በአዲስ መብላላት ሲጀምር ዳግም አሜሪካኖችም ያን የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ መጣጥፍ ያነቡ ጀምረዋል ። የኃያላኑ ዓላማ ከአፍሪካ ቀንድ እስከ ታላላቅ ሐይቆች ድረስ የአዲስ ካርታ ብወዛ ጅማሮ ነው ወይስ …

ሱዳንን ከኢጋድ የማስወጣት የግብጽ አሳሳች ውትወታ!
ኃያላኑ የአፍሪካን ቀንድ በአዲስ መበወዝ የሚቻለው የሱዳኑ ኦማር ሐሰን አልበሽር አስተዳደር ከተወገደ በኋላ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ያን የካርታ ብወዛ ቀጠናዊ ስትራቴጂያቸው በአሜሪካው ሐሳብ አፍላቂ መማክርት ለመንግሥት ወጋኝ ኩባንያ (Rand Corporation: 2000) በኩል ይፋ አድርገውት ነበር::

ከ11ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2011 ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ አዲስ አገር ሆነች ። አሁንም ሰዎቹ ዳርፉር ዳርፉር ማለታቸውን ቀጠሉ …ግን፣ 2019 ደረሱ፤ ሲጠሏቸው የባጁት ፕሬዚዳንት አል በሽር ከሥልጣን ተወገዱ ። ኃያላኑ መንግሥታት ለአካባቢያችን የነደፏቸው ግዛታዊ ማስተካከያዎችም ሆኑ ደኅንነታዊ አወቃቀሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ በተለያዩ አቅጣጫ እየጣሩ ይመስላሉ።

መጠንቀቁ ሳያስፈልግ አልቀረም ። የአፍሪካ ቀንድ እስከ ታላላቅ ሐይቆች አስፍቶ ታንዛንያን፣ ሩዋንዳንና ቡርንዲን እንዲያጠቃልል የተነደፈ “የታላቁ ቀንድ”(Great Horn) ሕልምም ሆነ ከዛሬ 21ዓመት በፊት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሙስቬኒ የነደፉት ስድስት ሪፐብሊኮች ፕሮጀክት ተግባራዊነት አሁንም በምዕራባዊያን የጂኦ ፖለቲካ ንሞና ራዳር ውስጥ ነው ። ይሳካል አይሳካም፣ ጊዜው ይፈቅዳል አይፈቅድም የሚሉ የጥያቄ ጋጋታዎች ሳይዘነጉ ።

የልዕለ ኃያላኑ የሱዳን አነባብሮሽ!
የካርቱም የጂኦ ፖለቲካ ሜዳ ከራሺያ እስከ አሜሪካ፣ ከቻይና እስከ ቱርክ፣ ከሕንድ እስከ ኳታር እያጋፋ ነው ። ወቅታዊው የካርቱም የሽግግር መንግሥት በኹለት ገመድ ተወጥሮ በሲቪል እና ወታደራዊ ሹማምንት ጉተታ እያስተናገደ ነው ። በዚህ የኃያላኑ ርኩቻ ካርቱም ራሷንም አድና ከጎረቤቶቿም ተታርቃ ለቀጣናው መረጋጋት ትሠራ ይሆን ወይስ በአሁናዊው ቀልበ ቢስነት ርምጃ ራሷንም ቀጣናውንም ወደ ባጀበት የደኅንነት አዙሪት እና ታሪኩ ሆኖ ወደ ተከተበበት የግጭት ቀጣናነት ይዛው ታዘግም ይሆን?

አፍሪካ መጣሁ… መጣሁ… የግብጽ ዲፕሎማሲ!
ግብጽ በዝነኛው መሪዋ ጋማል አብዱል ናስር ዘመን የነበራትን የዲፕሎማሲ ታሪክ ዳግም እየተገበረች ነው ። ያኔ ናስር፣ ተግባር ተኮር የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ይከተሉ ነበር። በአንድ አመት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ አገራትን የናስር ሚኒስትሮች ዙረዋል ።
የኢትዮጵያን ፓን አፍሪካ የወቅቱ እንቅስቃሴ ለመገዳደር ። ያኔ በእኛ ተረቱ ። ካለፈው አንድ አመት ጊዜ ጀምሮ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ከደርዘን በላይ የአፍሪካ አገራት ጉብኝት አድርገዋል። የጉዟቸው ዋና ዓላማ ያው ግልጽ ነው ። ግብጽ ከአሁን በፊት አፍሪካ ላይ የሠራችውን የዲፕሎማሲ ስህተት መድገም አትሻም።
ከስህተቶቿ መካከል በአውሮፓውያኑ 1973 የአረብ እስራኤል ጦርነት ወቅት የግብጽ (የአፍሪካ መሬት) በእስራኤል በመወረሩ በወቅቱ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ነበር።
ግብጽ ግን ያን ውለታ ከመጤፍ ሳትቆጥር ፊቷን ወደ ሀብታም ዓረቦች ማዞሯ በአፍሪካ የነበራትን ሚና እና ዝና አውርዶባታል ። ከካምፕ ደቬድ ስምምነት ማግስት ከአፍሪካዊያን ይልቅ አውሮፓ እና አሜሪካን ናፋቂ መሆኗ፣ ከ1992ቱ የማድሪዱ የሰላም ጉባዔ በኋላ ይዋቀራል የተባለው አዲሱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውሕደት ውስጥ መታቀፍ የበለጠባት ጊዜም ነበረ።
በዚህ ግርግር ግብጽ በአፍሪካ አህጉር ከተመሠረቱ በርካታ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውኅደቶችን ያነገቡ ቀጠና አባልነትን ሳታገኝ ውጭ ቀርታለች ። ለኢንዱስትሪ ሸቀጦቿ ገበያ ፈላጊ ለሆነችው ካይሮ ይህ በቀላሉ የማይታይ ስህተት ሆኖ አግኝታዋለች ።

ካርቱምን ከኢጋድ የማስወጣት የካይሮ ሴራ!
ግብጽ እና የቀድሞው የደኅንነት ሹም፣ ወታደራዊ ኢታማዦር ሹም የአሁኑ ፕሬዚዳንቷ አካሔድ እጅግ ውስብስብ እና ስልታዊ ሆኖ እናገኘዋለን ። አዲሶቹ ናስሮች ሱዳንን ከኢጋድ ያውም ራሷ በሊቀመንበርነት ከምትመራው ለማስወጣት ባጠመዱት ወጥመድ ቀዳሚ ያደረጉት አዲስ ወዳጅነት መመስረት ነው ። ሰሞኑን እንደምናስተውለው ያልተቀደሰ ጋብቻ ነው ። ከዚያ የካርቱም መለዮ ለባሾች አሻፈረኝ ባይነት ከኢጋድ የማስወጣት አካሔድ ይመስላል።
ይህ የካይሮ አካሔድ ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ ታላቁ ቀንድ ምስረታ አዲስ ካርታ ብወዛ ጋር ይገናኝ ይሆን?
የቀጣይ ሰው ይበለን …
ደሳለኝ ማናዬን በዚህ ኢሜል አድራሻቸው (dessalegnmanaye@gmail.com) ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com