የእለት ዜና

የዕርዳታ አሰባሳቢዎችና የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ፍጥጫ

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከተቀሰቀሰ እነሆ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። በዚህ ጊዜ ዉስጥ፣ የማይተካው ክቡሩ የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን በመተው ተፈናቅለዋል፤ተሰደዋል። ጦርነቱ ከተጀምረ ከጥቅምት 24፣2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀሌን ለቆ እስከወጣበት ሰኔ 18 ፣2013 ድረስ የተፈናቃይ ቁጥር ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነዉ ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን ፈጽሞ ተፈናቃይ አልነበረም ማለት አይደለም። በተለይ፣ በወልቃይት እና በራያ አካባቢ ሲኖሩ የነበሩ ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ወደትግራይ እና ወደ ጎርቤት ሱዳን ተሰደዋል።

መከላከያ መቀሌን ከለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ፣ የህወሓት ቡድን ከጫካ ወደ መቀሌ በመምጣት እንዲጠናከርና ጦሩን ወደአማራ እና አፋር ክልል አምጥቶ እንዲዋጋ ዕድል ሊያገኝ ችሏል። በዚህ ምክንያት በርካታ በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና በአፋር ኡዋ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ቀያቸዉን ለቀው ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህር ዳር፣ ደባርቅ እና ሌሎችም መጠለያ ጣቢያዎች በመግባት የስቃይ ኑሮ እየገፉ ይገኛሉ።

እንደ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን መረጃ፣ ቁጥራቸዉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚደርሰዉ ተፈናቃዮች በረሃብ፣ በበሽታ፣ በጉስቁልና ብሎም፣ በፀሐይና በቁር ሕይወታቸዉን እየገፉ ይገኛሉ። ለነዚህ ተፈናቃዮች ጥቂት የማይባሉ በአገር ውስጥ እና በውጪ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ አገር ዉስጥ ከሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር የዕርዳታ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለተጎጂ ወገኖች እንዲደርሳቸው እያደርጉ ይገኛል።
ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ቁሳቁሶች በትክክል ለተፈናቃዮች እንዲደርስ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እማኞች ገልጸዋል።

‹የወሎ ቤተ አማራ የበጎ አድራጎት ማኅበር› አስተዳዳሪ አራጋዉ ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ የችግሩን ጥልቀት በኹለት መንገድ ያዩታል፤ አንደኛ፣ ለተፈናቃዮቹ የሚመጣዉ ዕርዳታ ከተፈናቃዮቹ ቁጥር አንጻር እጀግ በጣም አነስተኛ መሆኑ ዋነኛው ተግዳሮት ነው። በዚህ ረገድ ረሀብ ጊዜ ስለማይሰጥ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ዜጎች በረሀብ እንዳይሞቱ የነፍስ አድን ዘመቻ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። በኹለተኛ ደረጃ ያስቀመጠዉ፣ የመጣውን ዕርዳታ ለተፈናቃዮቹ በማድረስ ሒደት ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ የማይሻሻለዉን የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችን ቅንነት የጎደለዉ የአሠራር መንገድን ነው።

“እንደማሳያ፣ ከወር በፊት ከወልቂጤ አማራ ተወላጆች 13 የጭነት መኪና ዕርዳታ እህልና ቁሳቁስ አምጥተዉ ደሴ ሲደርሱ ለመንግሥት አካል ከማድረስ ይልቅ ለኛ ማኅበር ለማስረከብ ደሴ ተገናኝተን ልንቀበል ስንል፣ የዞን ተወካዮች በመከልከል የራሳቸዉ አሠራር እንዳላቸዉ ገልጸዉ ዕርዳታውን ወደ ማከማቻ ክፍል ወስደዉታል” በማለት በማለት ይናገራል።

ይሁን እንጂ፣ ማኅበራቸዉ በደሴና ኮምቦልቻ ጠንካራ መሠረት ስላለዉ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ያሰባሰቡትን፣ አንድ ሚሊዮን ብርና ቁሳቁስ ዉርጌሳ ላሉ ተፈናቃዮች እራሳቸው ቦታዉ ድረስ በመሄድ እንዳስረከቡ አራጋው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በተመሳሳይ፣ ዕርዳታዉ ወደመጋዘን እንዲገባ ትዕዛዝ ቢደርሳቸውም ክፍ ወዳለዉ አመራር ቅሬታቸዉን ስለገለጹ፣ወደመጋዘን ሳይገባ ለተጎጂዎች ዕርዳታዉን ማድረሳቸዉን አብራርተዋል።

የተወከሉ አመራሮች የራሳቸዉ ዕርዳታውን የማከፋፈያ መንገድ ቢኖራቸዉም፣ ዕርዳታ ሊያደርሱ ከመጡት አካላት ጋር በቅንጅት ቢያከፋፍሉ ከትችት እና ተዓማኒነትን ከማጣት ይድናሉ በማለት አራጋዉ ሲሳይ መፍትሔ የሚለውን ሐሳብ ለአዲስ ማለዳ አጋርቷል።

በተመሳሳይ፣ የኢዜማ ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ በአፋር ክልል ልዩ ስፍራዉ ጭፍራ በተባለው የመጠለያ ቦታ ቁሳቁሶችን ለተጎጂወች ለማድረስ ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸዉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።በዕቅዳቸዉ መሠረት በጎንደር፣ በደሴ እና በአፋር ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ አልባሳት፣ የንጽሕና መጠበቂያ እና ደረቅ ምግቦች ለማድረስ ተንቀሳቅሰው ነበር። ዕርዳታውን በተለይ በአፋር ጭፍራ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት ለነበሩ ተጎጂዎች ሊያከፋፍሉ ሲዘጋጁ ፣በክልሉ የብልጽግና ካቢኔዎች ተከልክለዉ የነበረ ሲሆን፣ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ቀኑን ሙሉ ከፈጀ የማሳመን ሥራ በኋላ ሊያከፋፍሉ እንደቻሉ በማንሳት የችግሩን ክብደት ለአዲስ ማለዳ ዘርዝረዋል። በተመሳሳይ፣ ጭፍራ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ለዕርዳታ የተሰበሰበ 60 ኩንታል እህል መያዙን በአይናቸዉ መመልከታቸዉን ነግረዉናል።

በጭፍራ ት/ቤት የሚገኙት ተፈናቃዮች፣ አስተባባሪዎቹ ዕርዳታዉን በአግባቡ እንደማያደርሷቸዉ እንደነገሯቸዉ ዋና ጸሐፊዉ አክለዋል። የክልሉ ፖሊሶችም ዕርዳታዉ ለነሱም እንደሚያስፈልጋቸው ለአቶ አበበ አካሉ በተደጋጋሚ ሲወተውቷቸው እንደነበረም ትዝብታቸዉን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለግ ታዋቂ የአገራችን ኮሜዲያን በመስከረም 13/2014 ለደሴ ተፈናቃዮች 800 ሺሕ ብር የሚያወጣ ቁሳቁስ ከጓደኞቹ ጋር ሲያከፋፍል፣ ዕቃዎቹን ለመፈተሽ እንኳን የሞከረ የመንግሥት አካል አለመኖሩን በትዝብት ለአዲስ ማለዳ አጫውቷል። ”የአገርን ስም ለማጠልሸት የሚሠሩ አካሎች በመኖራቸው የሚገባው የዕርዳታ እህል መርዝ ሊሆን ይችላል። ተፈናቃዮቹን የሚጨረስ ቢሆን ማን ነዉ የሚጠየቀው በማለት፣ ግዴለሽነት ዋጋ ስለሚያስከፍል የሚመለከተው አካል ምግቦቹን በመፈተሽ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርግ” በማለት አሳስቧል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም እና የሕግ መምህር ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ለተፈናቃዮች በሚከፋፈል የምግብ አቅርቦት ሒደት ዉስጥ ኢፍትሃዊ ክፍፍል እንደሚደረግ ለአዲስ ማለዳ ትዝብታቸውን አጋርተዋል። ሕፃናትን ጨምሮ አሮጊቶችና አቅመ ደካሞች ዕርዳታውን ሳያገኙ ጎረምሶች በጉልበታቸዉ እንደሚቀበሉ አልሸሸጉም። ስለዚህ ቦታዉ ያሉ አስተዳደሮች ባስቸኳይ ይሄንን ችግር ማስወገድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የዲያስፖራው የተግባር ምክር ቤት የስካንዲኒቪያዋ ተወካይ ወ/ሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ፣ በራሳቸዉ ተነሳሽነት ከፈረንሳይ ለጋሲዮን የበጎ ፈቃደኞች ወጣቶች ጋር በመተባበር የዕርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ጀምረዉ በወጣቶች ማዕከል እያደራጁ ይገኛሉ። አዲስ ማለዳ በቦታዉ በመገኘት ወ/ሮ ኢትዮጵያን አነጋግራቸዋለች። እንደ ዕቅዳቸዉ ከሆነ 150 ኩንታል ዱቄት፣ የተለያዩ አልባሳት እና የቤት ቁሳቁስ ሰብስበዉ ፣በ15 ቀን ዉስጥ ጎንደር እና ደሴ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ማድረስ ነዉ። በጎ ፈቃደኞቹ በፈረንሳይ የወጣቶች ማዕከል ተሰባስበው፣የሚመጡትን ዕቃዎች በመቀበል፣ ልብሶቹን የመለየት ሥራ ሲሠሩ ተስተዉለዋል።

የወ/ሮ ኢትዮጵያ ዋና ሥጋት የተሰበሰበው ዕርዳታ በትክክል ለተጎጂዎች እንደየጉዳታቸው ልክ እንዴት ይደርሳል የሚለው ነው። እንደመፍትሔ ያስቀመጡት፣ ዕርዳታዉን ተፈናቃዮቹ ወዳሉበት ስፍራ በአካል በመሄድ፣ የጉዳታቸውን መጠን በማየት፣ እንደየአስፈላጊነቱ በእጃቸው መስጠት ነው። ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ የወ/ሮ ኢትዮጵያ ዕቅድ ተግባር ላይ መዋሉ አጠራጣሪ ነው። ስለዚህ አዲስ ማለዳ ይህ ችግር እንዴት መፈታት አለበት ስትል የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አቶ ደበበ ዘውዴን አነጋግራለች።

እንደኃላፊው ገለጻ፣ መንግሥት በተቀናጀ መንገድ ዕርዳታው በትክክል ለተጎጂዎች እንዲደርስ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል። በኢፌዴሪ አደጋ ሥጋት አመራር የበላይ ጠባቂነት፣ በሰመራ አና ባህር ዳር (Emergency Coordination Center) የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማሰተባበሪያ ማዕከል በማቋቋም፣ እንዲሁም በደሴ እና በጎንደር ተመሳሳይ ማዕከል በመመስረት የተቀናጀ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እርዳታዉ የሚገኘው ከመንግሠት፣ ከዓለም ምግብ ድርጅት፣ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እንዲሁም ከማኅበራትና ከኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞች መሆኑን ገልጸው፣ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በኹለቱ ማዕከላት የሚሠሩ ተግባራትን ሲዘረዝሩ፣ ተፈናቃዮቹን ከመመገብ በተጨማሪ፣በጤና፣ በውኃ፣ በንጽህና፤ በትምህርት እንዲሁም በሥነልቦና የማማከር ሥራ በሰፊው እየተሠራ እንደሆነም አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዕርዳታ አሰባሳቢዎቹ ለተጎጂዎች ዕርዳታውን ለማድረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከክልሉ የዞን አስተዳዳሪዎች የሚደርስባቸው እንግልት ለምን እንደተከሰተ አዲስ ማለዳ እንድታስረዳቸዉ አቶ ደበበን ጠይቃቸዋለች። በምላሻቸው፣“ዕርዳታ ስጪዎች እኛ ጋር በሚመጡበት ጊዜ ወደ ኹለቱ ማዕከላት እንዲያስገቡ ነው የምንነግራቸው። ምክንያቱም ሥርዓቱን የዘረጋነው ቅንጅት በተላበሰ መንገድ ዕርዳታውን ለተጎጂዎች በተሳለጠ መልኩ ለማዳረስ ሲባል ነው” በማለት ገልጸዋል። በአማራ ክልል ብቻ ወደ 1 ሚሊዮን ሕዝብ የተፈናቀለበት ሁኔታ በመኖሩ ማዕከሉ በትክክል ሙሉ መረጃ ስለሚኖረው፣ በየጊዜው የሚመጣው ዕርዳታ ማዕክል ዉስጥ ገብቶ ለተጎጂዎች ቢደርስ የተሻለ እንደሚሆን አስረድተዋል። ሌላዉ በማዕከሉ በኩል ዕርዳታው ቢከፋፈል የዕርዳታ ድግግሞሽ እንዳይከሰት ያደርጋል ብለዋል።

የማዕከሉ ሠራተኞች የተለያየ ሙያ ስለሚኖራቸው፣ ለምሳሌ ከተጎጂዎች መካከል በሽተኞች ሲኖሩ ቅድሚያ የመድኃኒት ዕርዳታ ማስፈለጉን ለማዕከሉ ይገልጻሉ። በዚያ መሠረት መድኃኒቱ ለበሽተኛዉ ይደርሳል። ሥራዉ በተናበበ መንገድ አየተሠራ ሳለ፣ አንድ የዕርዳታ ማኅበር መጥቶ የሰበሰበውን እራሱ ለማከፋፈል ቢሞክር ለሀብት ብክነት ከመዳረግ ውጪ ውጤቱ አመርቂ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

አክለዉም፣ በዕርዳታ አሰባሳቢዎች ላይ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በማመን፣ በተቻለ መጠን ችግሩን ለመቀነስ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የዕርዳታ አሰባሳቢዎቹም በሆደሰፊነት ታግሰው፣ዕርዳታቸውን በተዘረጋው ሥርዓት ቢያስረክቡ የተሻለ እንደሚሆን አበክረው ተናግረዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ የማሻቀቡ ነገር እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ የተከማቸው የዕርዳታ መጠን በቂ መሆን አለመሆኑን አቶ ደበበ ምላሽ ሲሰጡ፣ ዕርዳታው ከመንግሥት 70 በመቶ ፣ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና በጎፈቃደኞች የተቀረው ስለሚገኝ ለጊዜው ዕጥረት እንዳላጋጠማቸዉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ጦርነቱ እጅግ እየበረታ በመጣበት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካታ ተፈናቃዮች መጠለያ በማጣት የመከራ ሕይወት እየገፉ እንደሆነ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም፣ “መንግሥት ወይም የሚመለከተው አካል ከማለቃችን በፊት ሊደርስልን ይገባል፤ የምንተኛበት ፍራሽ ስለሌለን ደረቅ መሬት ላይ እየተኛን ብርዱን መቋቋም አቅቶናል” በማለት ምሬታቸውን አሰምተው ነበር። አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ነብስጡሮች እንዲሁም በሽተኞች በከፍተኛ እንግልት ውስጥ ከመሆናቸው የተነሳ ከዕለት ወደዕለት እየተዳከሙ እና ጤናቸዉ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን መታዘባቸዉን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወጣት ተፈናቃዮች አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳም የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሁሉንም ቅሬታ በማጤን፣ ችግሩን ከስር መሠረቱ በመንቀስ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሰጥ ተስፋ ታደርጋለች። ይህ ተቋም ከዕርዳታ አሰባሳቢዎቹ ጋር በቅርበት በመነጋገር በቅንጅት የሚሠራበትን መንገድ ቢያመቻች የተሻለ ዉጤት እንደሚመጣ ይታመናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!