የእለት ዜና

ታሪክን የምንረዳበትና የምንጠቀምበት መንገድ

በአግባቡ የተሰነደ ታሪክ ያላቸው አገሮች ታሪካቸውን በጥንቃቄ በመጠቀም የተሻለ መሆን ይቻላቸዋል። ታሪክ ማንነትን ለማወቅ፣ የዛሬን ክስተት ለመቃኘት፣ ተገቢ ወሳኔ ለመስጠት፣ ግንኙነት ለመመስረት እንዲሁም በጥቅሉ በብዙ መልኩ የዳበረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ይጠቅማል። ዓለምን ለመረዳትና ለውጥን ለማነጻጸርም ታሪክ ጉልህ ድርሻ አለው።

ከዓለም አገራት ውስጥ የተጣመመ እንኳን ቢሆን በማቃናት ታሪካቸውን በሚገባ ጥቅም ላይ ያዋሉና በታሪካቸው የገዘፉ አገራት አሉ። እንደ አብነትም ቻይና ጥንታዊነቷን፣ የነበራትን ጥበብና ባህል በሚገባ ማወቋ ለዛሬው ኃያልነቷ ትልቅ ስንቅ እንደሆናት ይነገራል።
እስራኤላውያንም ቢሆን ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን አገር ጥለው ከተበታተኑበት በመሰባሰብ የራሳቸው የሆነች አገር መመስረት የቻሉት ታሪካቸውን ተጠቅመው ነው።

ኢትዮጵያም ረዥም ዕድሜ ያላት አገር መሆኗን ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች ይስማሙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበረው ዘመን ተጠቃሽ ስትሆን፣ የሰው ዘር አመጣጥን በሚያጠናው ሳይንስም የሰው ዘር መገኛ መባሏ የሚታወቅ ነው። በዚህም በየዘመኑ ካደረገቻቸው ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ክንዋኔዎች የተገኝ አያሌ ጠቃሚ ታሪክ ያላት አገር በመሆኗ፣ ማንም አገር ታሪኩን ተጠቅሞ የዛሬ ኃያል ለመሆን ከሚያስችለው በላይ፣ በታሪኳ ገናና መሆን የምትችል አገር ናት።

የሉሲ መገኛ መሆን መቻሏን እንደትልቅ የታሪክ ሀብት ቆጥራ ብትጠቀምበት ዜጎቿን ወደሌሎች አገራት እንዲሰደዱ ከማድረግ ይልቅ በዓለም ለሚገኙ የሰው ልጆች ኹሉ መሰባሠቢያ ዕምብርት መሆን ትችል ነበር። ከሺሕ ዓመታት ገደማ በፊት ከጣራ ወይም ከላይ ወደታች ከአንድ ቋጥኝ በርከት ያሉ ቤተ መቅደሶችን መሥራት የቻለችበትን ታሪክ በሚገባ ብታጤን፣ ዛሬ የራሷን ግንባታ በውጭ መኃንዲሶች ከማሰራት አልፋ በዓለም ላይ ላሉ አገሮች ልክ እንደቻይና ብዙ ግንባታዎችን ትገነባ ነበር።

መካከለኛው ዘመን በፊውዳሊዝም ሥርዓት የወደቀ፣ የሳይንስና የባህል ዕድገት ያልነበረበት ኋላቀር ጊዜ ስለነበር በአውሮፓ የጨለማው ዘመን ተብሎ ይጠራል። በዚህ ጊዜ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ቶማስ ሞር፣ አውሮፓውያን ከኢትዮጵያ ተምረው ከጨለማው ዘመን እንዲወጡ እንደመከራቸው የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ቶማስ ሞር በዕውቀትና በጥበብ የዳበሩ ጥቁር ሕዝቦች መኖራቸውን፣ አሥተዳደራቸውም ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ አድርጎ ‹ዩቶፒያ› በሚል መጽሐፍ አቅርቦላቸው እንደነበር ይታመናል። ኢትዮጵያውያንም በጥንት ጊዜ ለሌሎች አገሮች አብነት መሆን የምትችል አገር እንደነበረች በሚገባ ቢረዱ ኖሮ፣ ዛሬ ማንም የሚዝትባትና በጉስቁልና የተሞላች ኢትዮጵያ አትሆንም ነበር ነው የሚሉት ምሁራኑ።

የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉም በአግባቡ ካለመሰነዱ ሌላ ተሰንዶ የተቀመጠውንም ሰዎች የሚተረጉሙበትና የሚጠቀሙበት ዓውድ ለአንድነትና ለእድገት የማይበጅ እንደሆነ ይገለጻል።
ታሪክ መጥፎውንም በጎውንም የያዘ እንደመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በአብዛኛው በጎ ያልሆነው የታሪክ ክፍል ነው። በጎ ያልሆነ ታሪክን መማሪያ ማድረግ ሲቻል፣ የመጥፎ ድርጊት መነሻ ከተደረገ ደግሞ ዛሬም ለነገ የሚሆን ሌላ መጥፎ ታሪክ ትቶ ያልፋል።
ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ታሪክ ተጠቅማ ሌላ በጎ ታሪክ መሥራት ሲገባት፣ አሁን እየሆነ ያለው ስለትናንት በተዛባና በተሳሳተ ታሪክ ዛሬንና ነገን ማበላሸት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

በዚህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታሪክን ወደኋላ ሔዶ በማጣመምና መልካም ያልሆነውን ብቻ ነቅሶ በማውጣት በማኅብረሰቡ መካከል አለመተማመንና መናናቅ ተፈጥሮ ተስተውሏል። በየቦታው እና በየጊዜው የሚፈጠሩ ፍጅቶችም የዚሁ ውጤቶች ናቸው። በታሪክ አረዳድ ላይ ያለው ሰፊ ልዩነት የሚፈጥራቸው ችግሮች እንደደራሽ ውኃ አገሪቱን እንደሚያናውጧት በርካቶች ያምናሉ።

ያሉት የታሪክ ሰነዶች ወገንተኝነት ያጠቃቸዋል ብለው የሚያምኑ የተለያዩ አካላት በየጊዜው እየተነሱ ያለማስረጃ የሚሰንዱት የታሪክ ዶሴ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ፈተና ሲሆን ይስተዋላል። መሆን የነበረበት ግን ባለፈው ታሪክ ውስጥ እኛ ተረስተናል ወይም ተበድለናል ብሎ የተሳሳተ ታሪክ ከመሰነድ ይልቅ፣ ያ እንዳይደገም መማርና መሥራት ነበር ሲሉ በርካታ ምሁራን በየአጋጣሚው ሲናገሩ ይሰማል።

የኢትዮጵያ ታሪክ በፖለቲካ ሴራ የተበከለው ከ1970ዎች ጀምሮ እንደሆነ ቢነገርም፣ ከደርግ በኋላ የተተካው መንግሥት ከትናንት ታሪክ ተምሮ መልካሙን በማስቀጠልና መጥፎውን እንዳይደገም ከመሥራት ይልቅ ቁርሾና አለመተማመንን የሚያጠነክሩ ታሪኮችን ሲመዝና ሲፈጥር መቆየቱ ይታወቃል። በዚህም በተለያዩ ከተሞች የታሪክ ውጤቶች ናቸው የተባሉ ለፍቅር የማይበጁ ሐውልቶች ተገንብተው ታይተዋል። የተሻለ እና አርቆ አሳቢ ትውልድ ብሎም እንደ አክሱምና ላሊበላ ያሉ ስመጥር ቅርሶች ላላት አገር፣ በርግጥ እንዲህ አይነት ሐውልቶችን መገንባት ፍቅርን መግደል ጥበብንም መቅበር መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።

አሁን ባለንበት ወቅትም፣ ለታሪክ ባላቸው ጥላቻ የተነሳ የወደፊቱን ጊዜ የሚያበላሽ ንግግሮችን የሚጭኑ ብዙ ሰዎች አሉ። እንዲሁም ባላቸው አናሳ የታሪክ ዕውቀትና የአጠቃቀም ክህሎት፣ ኃላፊነት በጎደለው ልቅ ንግግራቸው እና ድርጊታቸው መጭው የኢትዮጵያ ጊዜ የተሻለ እንዳይሆን የታሪክ ጥንተ አብሶ የሆኑ አካላት ቀላል አይደሉም።

“እገሌ የሚባለው ብሔር እገሌ ላይ እንዲህ አድርጓል” በማለት ሕዝቡ ውስጥ በከተቱት የጥላቻ ንግግር፣ የብዙዎች ሕይዎት ሲቀጠፍ እና ሲመሰቃቀልም ታይቷል።
የአሁኑ የእርስ በርስ ፍጅትም በዋናነት ከሥልጣን ጥማት የተወለደ ይሁን እንጂ፣ ውስጥ ውስጡን ሲነገር የኖረው የተጣመመ ታሪክም ለፍጅቱ እንደ አንድ መንስኤ እንደሆነ ነው የሚነገረው።
ሆኖም ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም ነውና የሚባለው፣ በትናንት ታሪክ ውስጥ በጎ ያልሆነውን በመተው፣ ከዚያ ይልቅ የሚጠቅም ብዙ ስላለ እሱን መሠረት አድርጎ ያማረ ነገ መገንባት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ጋዜጠኛ ሆነው የሚሠሩት ዲያቆን ማለደ ዋስይሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል። በዚህም ታሪክ ማለት የተኖረና ያለፈ ነገር ሆኖ፣ የሰው ልጅ ትናንት ያሳለፋቸውን ዘርፈ ብዙ የሕይዎት እንቅስቃሴዎች በሚገባ የሚሰንድ፣ የሚተነትንና የሚያከማች ትልቅ ሙያ ነው ብለውታል።

አንድ የትናንት ድርጊት ታሪክ ለመሆን ሳይንሳዊ መንገድ ተክትሎ በባለሙያዎች መሠራት አለበት፣ ሳይንሳዊ መንገድ ተከትሎ ያልተጣራ ሰነድም ሆነ የተወራው ሁሉ ታሪክ መሆን አይችልም ነው ያሉት። ያለፈን ነገር ሁሉ እንደ መረጃ ምንጭነት ከመያዝ ባለፈ ታሪክ ነው ብሎ መጥራት እንደማይገባም ተናግረዋል።

ታሪክ የባለ ታሪኮች ስለሆነ ባለፉት ሰዎች ታሪክ ላይ ብቻ ሙጥኝ ከማለት ዛሬ ላይ የሚኖር ሰውም የራሱን መልካም ታሪክ ሠርቶ ማለፍ እንዳለበት አንስተዋል። ታሪክ በጎ እና መጥፎ ክፍል ስላለው አሁን ያለው ማኅበረሰብ የትናንቱን ታሪክ በዛሬ የራሱ ዓውድ ሲመለከተው ልዩነት መኖሩ አይቀርም፤ ይህን መገንዘብ ከተቻለ ከሁሉም ታሪክ ጠቃሚ ነገር ማግኘትና መማር እንደሚቻል ነው የጠቆሙት።

ዲያቆን ማለደ አክለውም፣ ትናንት ከነበሩ ታሪኮች ደግመን ልንሠራቸው የሚችሉ ተግባራት ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል። እንዲሁም ተሻሽሎ ወይም ተስፋፍቶ የሚሠራ የትናንት ታሪክ ሊኖር እንደሚችልም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይህን የሚያደርገው ግን የነቃ እና ስለታሪክ ጠቀሜታ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ነው ሲሉ ገልጸዋል። ታሪክ በሳይንሳዊ መንገድ በጥንቃቄ ተሰንዶ የሚቀመጠውም እንደዚህ አይነት ማኅበረሰብ እንዲጠቀም ለማስቻል ነው የሚል እምነታቸውን አስቀምጠዋል። እንዲህ አይነት የተሻለ ዕይታ ያለው ማኅበረሰብ ከታሪክ ውስጥ መልካም ያልሆነው እንዳይደገም የማይጠቅም ከሆነም እንዲጠፋ ያደርጋልም ብለዋል።

አሁን ላለው ፍጅት የታሪክ አረዳድና አተረጓጎማችን በቀጥታ ሚና አለው የሚሉት ዲያቆን ማለደ፣ ፖለቲካው በታሪክ ላይ ባለው ጫናም ኢትዮጵያ በታሪኳ መጠቀም ሲገባት ተጎጅ መሆኗን ሳይገልጹ አላለፉም። በዚህም ለታሪክ ንቀት ያላቸው ፖለቲከኞች ታሪክ ያልሆነን ነገር ታሪክ አስመስለው በማቅረብ በሕዝብ ላይ ያሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በታሪክ ባለሙያዎች ሳይቀር በሚያስገርም ሁኔታ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ሲተረጎም ማየታቸውን ገልጸው፣ ታሪክን አዛብተው በመተርጎም በኃይልና በጉልበት ሕዝብ ላይ ከሚጭኑት በተጨማሪ ፣ሆነ ብለው የተዛባ የታሪክ አረዳድን ባህሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የዛሬ ታሪኳን በሳይንሳዊ መንገድ በሚገባ የሚሠንድ ተቋም የሌላት በመሆኑ፣ በትናንት ታሪክ ከሚሰቃየው የአሁኑ ትውልድ የከፋ፣ የነገው ትውልድም ነገ ታሪክ በሚሆነው የዛሬ ድርጊት ይታወካል የሚል እምነትም አላቸው።
የታሪክ መምህሩ ታዬ ቦጋለ ፣‹‹መራራ እውነት›› በሚለው የታሪክ መጽሐፋቸው ታሪክን በማዛባት አባዜና ሴራ የተነሳ ፅዱ የታሪክ ገጾቻችንን የፖለቲካ ደባ እንዳስነወራቸው ገልጸዋል። በዚህም አብዛኞቹ የታሪክ ዘውጎች የታሪክን ትምህርት ዓላማና ግቦች፣ እንዲሁም ጠቀሜታ ያላገናዘቡ፣ የተጦመሩትም የታሪክ ትምህርትን ታሳቢ አድርገው እንዳልሆነ ነው የጻፉት።

ገብረ ሕይወት ባይከዳኝም እንዲሁ፣ ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› በሚለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ገልጸዋል። ‹‹ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል፣ ለቤተ መንግሥት መኮንን ግን የግድ ያስፈልጋል፤ የዱሮ ሰዎችን ስህተትንና በጎነትን አይቶ ለመንግሥቱና ላገሩ የሚበጀውን ነገር ያውቅ ዘንድ። የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅመው የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው። እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልገናል። መጀመሪያ፣ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል፣ ኹለተኛ የማያዳላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ፣ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ፣ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ። ያገራችን የታሪክ ጻፎ ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢአት ይሰራሉ። በትልቁ ነገር ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ። ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ፤ አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ላንባቢው አይገባም።››

ታሪክ በማይቋረጥ መልኩ በትውፊት፣ በቃል፣ በጽሑፍ ወይም ደግሞ በቅርጻ ቅርጽ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር የአንድ ሕዝብ መገለጫ ሀብት እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያንም ሠፊ ታሪካቸውን በሚገባ በመሠነድና በሳይንሳዊ አተያይ በመተርጎም ለበጎ ነገር ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይገባል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ በትናንት ታሪክ የምትታመሰውን ያህል፣ የነገው ትውልድም በታሪክ እንዳይጎዳ ማንም ቢሆን ታሪክን የሚሠንድበትና የሚተረጉምበት መንገድ የሚያግባባ፣ ለፍቅርና ለዕድገት በሚበጅ መልኩ መሆን አለበት።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com