የእለት ዜና

የመጀመሪያ የሆነ የመኪና መለዋወጫ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ሥራ ሊጀምር ነው

በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የመኪና መለዋወጫ ፋብሪካ በመዲናችን አዲስ አበባ መከፈቱ ተሰምቷል።
“ዜድ ዋይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው በቻይናውያን እና በኢትዮጵያውያን ሽርክና ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የተቋቋመው ፋብሪካ በአሁኑ ሰዓት ምርት ለመጀመር የማሽነሪ ሙከራ ላይ ይገኛል ተብሏል።
በመዲናችን አዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ብሔረ ጽጌ አካባቢ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ ለማንኛቸውም መኪኖች የሚሆን የአየር ማጣሪያ (ኤር ፊልትሮ) እና የዘይት ማጣሪያ (ኦይል ፊልትሮ ) በማምረት ሥራውን እንደሚጀመር ተገልጿል።
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት ማጣሪዎችን ለማምረት የሚያስፈልገውን ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑም ተጠቁሟል ።

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንጅነሪንግ ዘርፍ ዳይሪክተር ተረዳ ታደሰ፣ ተቋማቸው አዳዲስ የብረታብረት አምራች ዘርፎች ሲደግፉ እንደነበር ገልጸው፣ ለዜድ ዋይ ፋብሪካም በቴክኒክ፣ በቅድመ አዋጭነት ጥናት እና በሌሎችም መስክ ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል ።

የፋብሪካው ሥራ አስፈጻሚ ሲሳይ ነገራ፣ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ጨምሮ እስከ የቤት አውቶሞቢል ድረስ ያሉ ተሸከርካሪዎችን የአየር እና ዘየት ማጣሪያዎች የማምረት አቅም እንዳለው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ዜድ ዋይ አገሪቱ ፊልትሮ ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ የመቀነስ አቅም አለው ሲሉም ተናግረዋል። “ፋብሪካችን የየትኛውንም አየነት መኪና ብራንድም ሆነ ሞዴል የማምረት አቅም ስላለው፣ ባለንብረቶች ገበያ ውስጥ ያጡትን ምርት ከውጪ ለማስገባት ይፈጠርባቸው የነበረውን እንግልትም ያስቀራል” ሲሉ ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።

ፋብሪካው በአመት ከ 80 ሺሕ ቶን በላይ የማምረት አቅም አለው የተባለ ሲሆን፣ ምርቱንም ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡ የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት አንጻር ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተነግሯል ።
በ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት አራት ኩባንያዎች 69.54 ቢሊዮን ብር የማምረት አቅም በመያዝ የዘርፉን ኢንቨስትመንት መቀላቀላቸውን የኢንጂነሪንግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ገልጿል።
ፕሮጀክቶቹ የሚገኙበት አካባቢ አዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሃንና ኦሮሚያ (ቢሾፍቱ) ሲሆን፣ የምርት ዘርፎቹም መሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ መሆኑ ታውቋል።

የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከተሳበው ኢንቨስትመንት ቁጥር፣ ከማምረት አቅም አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለ589 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ተብሏል።
በ2017 እ.አ.አ. ወደ 817 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የብረት ምርት (ከ 10 ሚሊዮን ቶን በላይ) ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ነው የሚገለጸው። በአገር ውስጥ በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች፣ ከ 157 ሚሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን እንዳለ የተረጋገጠ ሲሆን፣ 1 ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ ብረት እንዳለ የመስክ ምልከታ ግምቶች ያሳያሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢንስቲትዩቱ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እና የሌሎች አገራትን እንደ ቻየና ፣ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ፣ ለገቢ ብረት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሬ ለማስቀረት አነስተኛ ማዕድን አውጪዎች ብረት እያወጣ ለፋብሪካ ማቅረብ እንዲችሉ የሚያደርግ የቅድመ አዋጨነት ሥራ መጀመሩን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለኢንዱስትሪ ማዕድናት ማለትም እንደ ብረት ፣ከሰል እና ሌሎች ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ፣ ለኹለት ዓመት በጀኦሎጂካል ሰረቬይ በተጠናው ጥናት መሠረት በጎጃም መርጦ ለማርያም ፣መካነ ሰላም እና በደቡብ ወሎ የብረት ክምችት መገኘቱ ተረጋግጧል ።

ይህንንም ተከትሎ የ “ሲ ኤንድ ኢ” ብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ እህት ኩባንያ የሆነው “አጎዶ ዮ” በከሰል ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ በመካነ ሰላም የብረት ማዕድን ለማውጣት ፈቃድ ወስዶ በመንቃሳቀስ ላይ የገኛል ። በተጨማሪም በቅርቡ ሰቆጣ ማይኒንግ የተሰኘ ድርጅት ፍቃድ አገኝቶ ወደ ማዕድን ፍለጋ መሰማራቱን ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!