የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የማኅበራዊ ሚዲያው ጫና

አሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ብዙ ሰው እንደሚረዳው፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በውስብስብ ችግሮች የተሞላ ነው። የጎበዝ አለቆች በየቦታው ከተነሱበት እና ሥርዓት አልበኝነቱ ወደር አይገኝለትም ከሚባለው ዘመነ መሳፍንት ወቅት ጋር የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲመዘን የአሁኑ ተመስገን ነው ሊባል የሚችል አይደለም።

በዚያን ጊዜ ሕዝቡ መንግሥት አለኝ ብሎ አይዘናጋም ነበር። ቁርጡን ስለሚያውቅ ራሱን ካልጠበቀ ነጣቂ እንዳለበት ያውቃል። በዘር ተቧድኖ መጫረስም የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ክስተት እንጂ ቀድሞ ያልነበረ ነው።
በንጹኃን ላይ ግፍ ደርሷል ከሚባልበት ከደርግ ዘመንም ጋር ቢነጻጸር እንኳን የአሁኑ በጣም ግራ የሚያጋባና የቀጣዩን ጊዜ ሁኔታ ለመተንበይ እንኳን የሚያስቸግር ነው። በደርግ ዘመን እንዳሁኑ ሥጋት እና እንግልት የሚደርስባቸው የስቃይ ሞት የሚሞቱም አልነበሩም።

የአሁኑ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የተፈጠረው በተለያዩ ጊዜያቶች በተቀበሩ ፈንጆች መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ብሔር ተኮር እንቅስቃሴዎች የተጸነሱት ገና በንጉሱ ዘመን ጀምሮ በመሆኑ፣ ኹሉም የብሔር እንቅስቃሴዎች ባለፉት ዓመታት ለነገዋ ኢትዮጵያ መጥፎ ፈንጅ እየቀበሩ ያለፉ ነበሩ።

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከኹሉም በፊት በዘር መደራጀትን ያስተማረውና የተገበረው ህወሓት ሲመሰረት፣ የያዘው ሐሳብ ኢትዮጵያን ማዘመን፣ ታላቅነቷን ዕውን ማድረግ ወይም ሌላ መልካም ነገር አልነበረም። ማንን እናጥፋ፣ ምን እንዝረፍ፣ ጥላቻና አለመተማመንን በሕዝቦች መካከል ለመፍጠር ምን እንሥራ የመሳሰሉትን ማንም ሰው የሆነ ፍጡር በአገሩ ላይ የማያስበውን ተንኮልና ሴራ ነበር ይዞ ለትግል በረሃ የገባው። በየጊዜው እየፈነዳ ኢትዮጵያን የሚያደማት ከዚህ በላይ የከፋ ፈንጅ የለም።
ከዚያ በኋላም የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጭ፣ የአማራ፣ የጋምቤላ፣ የኦጋዴን እየተባለ ኹሉም በየአካባባው የማይከሽፍ ፈንጁን ይቀብር ጀመር።

በዚህ ሁሉ ምክንያት ዛሬ ላይ በአራቱም ማዕዘናት ኢትዮጵያ ለአንድ አዳር እንኳን ሠላም ሆና ማየት ይናፍቃል። አንድ ኢትዮጵያዊ ወደፈለገበት ቦታ መሄድ ቢፈልግ አስቀድሞ ስለአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ መጠየቅ ግዴታው ነው። ማንም ከሚሄድብት ይልቅ የማይሄድበት አካባቢ ይበዛል። አንድን ክልል የራሳችን ብቻ ነው የሚሉ ሰዎች አያሌ ሆነዋል። የአንዱ ክልል ልማት ለሌላው አያስደስትም። የአንዱ መጎዳት ለሌላው መጠቀሚያ ሲሆን ይስተዋላል።
አንዱ ብሔር የሌላኛው አጥፊ እንደሆነ ይቆጠራል። እዚያም እዚህም ሞት አለ። እናም አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ኹኔታ ለብዙዎች መከራ የሚጭን፣ ለሌሎችም ግርምትን የሚያጭር ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት መንግሥት ነው ያለው ተብሎ ቢጠየቅ ለማወቅ ያዳግታል። የራሱ ወታደር እና ፍላጎት ኖሮት ትዕዛዙን የሚያስፈጽም ኃይል በየቦታው አለ።

አራት ኪሎ የከተመው መንግሥት የማያድናቸውና የማይጠብቃቸው ብዙ ዜጎች አሉ። አቅም አንሶት ይሁን የዜጎቹን ጩኸት ችላ ብሎ አይታወቅም። ቀስትም መድፍም የታጠቁ ኃይሎች ንጹኃን ሕዝቦችን በመጨረስ ላይ ናቸው። በየቀኑ ሞት አለ። በየጊዜው መፈናቀል አለ።
ሠላም እንኳን ቢሆን ሥራ አጥነት፣ ጥልቅ የሆነ ድኅነት እና ሥደት በሞላባት አገር ውስጥ ይባስ ብሎ መቋጫ ያላገኘው ጦርነት ደግሞ የአገሪቱን ሁኔታ ይበልጥ አስከፊ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም ላይ ትኩረት እንዳያደርግ ብሎም በፍቅር በመተሳሰብ ራሱን እና አገሩን እንዳያሳድግ የያዙት ማነቆዎች ብዙ ናቸው። በትናንት ታሪክና ድርጊት ኑሮውን አስከፊ ከማድረጉ ሌላ፣ ዛሬ ላይም ሌሎች አገራት የሚያድጉባቸውንና የሚታወቁባቸውን የሳይንስ ውጤቶች በመጠቀም አገሩን ለማጥፋት ሲጠቀምብት ይስተዋላል።

ለአብነትም ፌስቡክና ሌሎች ማኅብራዊ ሚዲያዎች ከብዙ አገራት የሚሰበስቡት ሀብት ቀላል የሚባል አይደለም። ብዙ ኢትዮጵያውያንም ለእነዚህ ሚዲያዎች ገንዘባቸውን በመገበር አገራቸውን እያፈረሱ የሚገነቡት የሰው አገር ነው።
በቅርቡ እንኳን አንድ የአሜሪካ ሴናተር፣ ፌስቡክ በማይናማርና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን መናገራቸው አይዘነጋም። ማይናማር ካላት ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ የሚልቀው የመረጃ ምንጩ ፌስቡክ እንደሆነ ይነገራል። ኢትዮጵያ ውስጥም በፌስቡክና ሌሎች ማኅብራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ብዙ ሰው አቅጣጫ ጠቋሚ እና እውነት አዋቂ ነው።

ብዙዎችም የጦር ባለሥልጣናት ሳይቀር ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚለውን ቀደም ያለ አነጋገር ለዚህ በመጥቀስ፣ የአሁኑ ጦርነት ሚዛኑ ወደ መንግሥት እንዳያዘነብል ማኅበራዊ ሚዲያው ትኩሳት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ። ከዚያ ይልቅ ግን መንግሥት ሕዝቡ ማውቅ የሚፈልገውንና እየሆነ ስላለው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲነገረው ከማድረግ ይልቅ ሥራዬ ብሎ ለሕዝብ መረጃ ሲያደርስ አይስተዋልም። በዚህም ኹሉም አዋጊ ኹሉም መረጃ ተንታኝ ነው።

በአሁኑ ወቅት ብዙ አገሮች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙት አገራቸውን ለማስተዋወቅ እና ለማበልጸግ ነው። የማኅብራዊ ሚዲያዎች ባለቤት ከሆኑት አገሮች በተጨማሪ ሌሎች አገሮችም በእነዚህ ሚዲያዎችን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ያውቃሉ። አንዳንድ አገሮች ልቅ የሆነ አጠቃቀም አገራቸውን ምን ያህል ወደ ኋላ እንደሚጎትተና እንደሚጎዳ ስለሚያውቁ ሕግም አበጅተዋል።

ለምሳሌ ሕንድ በማኅበራዊ ሚዲዎቿ ላይ ሕግ ካስቀመጡ አገራት አንዷ ናት። ሕንድ ውስጥ ከመንግሥት ወይም ሕጋዊ ከሆነ አካል ትዕዛዝ የደረሰው የሚዲያ ባለቤትም ሆነ ተጠቃሚ በ26 ሰዓታት ውስጥ የለጠፈውን ማጥፋት ይኖርበታል። ይቅርታ ከመጠየቅ እስከ ማስተካከል ብሎም እስከ መቀጣት ሊደርስ ይችላል።

አውስትራሊያ በበኩሏ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን የሚቆጣጠር አካል አቋቁማ ክትትል የምታደርግ አገር ናት። ለአገሪቱ መልካም ያልሆነ ሥራ በሚዲያ ላይ የለጠፈ አካል በድርጅት ግማሽ ሚሊዮን ዶላር፣ ግለሰቦች ደግሞ ከመቶ አስር ያላነሰ የዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ደቡብ ኮሪያም የሕዝብን ሞራል የሚነካ፣ የአገር ሉዓላዊነትን የሚጥስ፣ የወጣቶችን አስተሳሰብ የሚበክል ማንኛውንም ነገር በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሰተጋባ እንዳይኖር በሚል ጠበቅ ያለ ሕግ ካጸደቀች ዓመታት ተቆጥረዋል።
መሰል ሕጎችን ተግብረው በአገራቸው ሽብርተኞች እንዳይፈጠሩ፣ ሕዝባቸው ለመልካም ነገር ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያደርጉ አገራት ቀላል አይደሉም።

አገራቸውን በሚወዱ ሌሎች አገሮች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያውን የአገራቸውን ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ለአብነትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ትዊተር እንዲጠቀሙ ብዙ አገራቸውን የሚወዱ ሰዎች ጥሪ ሲያቀርቡ ተስተውሏል። ግብጽ ያን ሁሉ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ስትፈጥር የነበረው በአፍሪካ ቀዳሚዋ የትዊተር ተጠቃሚ በመሆኗ ነው። ህወሓትም ቢሆን ማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ አብላጫ ለማግኘትና ኢትዮጵያ ሌላ መልክ እንዲኖራት ለማድረግ የሚጠቀመው በዋናነት ይህንን ማኅበራዊ ሚዲያ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያው ደላላ የሚባሉት (lobbyists) በሚሊዮን ገንዘብ እየተከፈላቸው ኢትዮጵያን የሚጎዳ በርካታ ነገር የፈጸሙት ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያላት ተጠቃሚነት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። አሁን ላይ በብዙ ገንዘብ በየአገራቱ ቆንጽላ በመክፈት እና አምባሰደር በመሾም የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት ከማድረግ በላይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በማኅበራዊ ሚዲያው በሕዝብ የሚሠራ (public diplomacy) ሥራ ትልቅ ዋጋ አለው።

ሻለቃ ታመነ አባተ የኢትዮጵያ የቀድሞው መከላከያ ሠራዊት የልማትና የድጋፍ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበሩ። ማኅበራዊ ሚዲያው አሁን ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና ለአዲስ ማለዳ ሐሳቸውን አጋርተዋል። ሻለቃ እንደሚሉት ብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ዓላማቸው የአገር ጉዳይ ሳይሆን ገንዘብ ማግኘት ነው። ኹሉም የሚኖረው አገር ስትኖር ነው የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ ሚዛናዊ ባልሆነ ወሬ አገርን እያፈረሱ ገንዘብ መሰብሰብ መጥፎ ድርጊት ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

አሁን ላይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚነዙ ሐሰተኛ ወሬዎች ማኅበረሰቡን ከማወናበድ ሌላ ግንባር ላይ ባለው ሠራዊት የሚያደርሱት ተጽዕኖ እንደሌለም ገልጸዋል። በወታደር ቤት ውስጥ በአገርና በጠላት ጉዳይ ላይ በአመራሩ ሁል ጊዜ ወቅታዊ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑና ወታደሩም ቁጭ ብሎ ወሬዎችን የሚሰማበትና የሚያነብበት ጊዜ ስለሌለው ምንም አይነት ተጽዕኖ አያሳድርበትም ብለዋል። ሆኖም ግን በጠላትም ይሁን ኃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች የሚነዙ ሐሰተኛ ወሬዎችን አረጋግጦ የሚቀበል ማኅበረስብ ከሌለና ገደብ ካልተበጀላቸው፣ ጠላት ኹለት ዕርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ፣ ማኅበረሰቡም ሥራውን እንዳይሠራ፣ ሥነ-ልቦናው እንዲሰለብ እና ከጠላት ጋር እንዲወግን ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል።

የሚዲያ መምህር እና የልማት ተግባቦት አማካሪ የሆኑት አሰግደው ሽመልስ በበኩላቸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያው አሁን ላይ በኢትዮጵያ እያስከተለ የሚገኘውን አሉታዊ ተጽዕኖ አስረድተዋል። በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያ መደማመጥ የጎደለው እንደሆነ ይገልጻሉ። እንዲሁም ስለአገር ደኅንነትና ሉዓላዊነት ማኅብራዊ ሚዲያው ላይ አጀንዳ ተቀርጾ፣ የሕዝብን ፍላጎትና የአገርን ደኅንነት በማስጠበቅ የዘርፉን ጥቅምና ጉዳቱን ለይቶ የሚንቀሳቀስ የማኅብራዊ ሚዲያ ተቆጣጣሪ (ትራፊክ) አይደለም ያለው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ትልቅ ችግር ማኅብራዊ ሚዲያው የተያዘው በልሂቃን አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

በዕውቀት ማጠር፣ ዓለማዊና አገራዊ ቀጠናውን ካለመረዳት፣ የአገርን ክብርና ሉዓላዊነት ሔደው ከሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማቆራኘት፣ የሆነን ፖለቲካ ፓርቲ የጎዱ መስሏቸው አገርን በሚጎዱ፣ ወደ ነገ እንዴት መኼድ እንዳለበት በማያውቁና በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ዓለማ አቀፋዊ ጫና ባልተረዱ ሰዎች ከዕውቀትና ሙግት ይልቅ፣ በስድብና በሐሰት ተረኮች ላይ የተመሠረተ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ተፈጥሯል ነው ያሉት።

አክለውም፣ አሁን ላይ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያለው መንጋ ወታደራዊ ዝግጅቶችንና ዕቅዶችን ሳይቀር ኹሉንም የወታደርና የአገር ምስጢር ማወቅ ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ለአገር ደኅንነት አደገኛ ነው ብለዋል። ማኅበራዊ ሚዲያው በዜጋ ጋዜጠኝነት (citizen journalist) አማካይነት ኹሉም ዜጋ መረጃ ለማግኘትና ለመተንተን መብት ቢሰጠውም፣ መብት ከአገር ደኅንነት ስለማይበልጥ ስለምንለቃቸው መረጃዎች ማስተዋል ይገባል ባይ ናቸው።
ሰሞኑንም ግዴለሽ የሆኑ ሰዎች በሚነዙት ወሬ በሰሜን ወሎ፣ ድቡብ ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና ዋግኽምራ አካባቢዎች ማኅበረሱቡ ክፉኛ እንዲጨነቅ እያደረጉት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ዓለም በበይነ መረብ የተሳሰረችበት ወቅት በመሆኑ፣ ልክ እንደሌሎች የተወሰኑ አገሮች ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የተቀመጠውን የአገርንና የጦርን መረጃ ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥን መቅጣት ያስፈልጋል። ከዚያ ውጭ መረጃን አጣርቶና አገናዝቦ የሚጠቀም የሚዲያ ዕውቀት ያለው ዜጋ ለማፍራትም መሥራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

በአፍሪካ ደረጃ የመረጃን ትክክለኛነት አጣርቶ የመጠቀም ብቃታችን 12 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቁመው፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚናገረውና በሚጽፈው የሚሞቱ፣ የሚታፈኑና የሚሰቃዩ ሰዎች መኖራቸውን በማወቅ ከድርጊቱ የመቆጠብ የሞራል ግዴታ አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

ዲጅታል ሚዲያው ከሌሎች ሚዲያዎች ይበልጥ ነጻና ተደራሽ ስለሆነም፣ በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ምሁራን ማኅበረሰባቸውን ቀርበው እንደሚያስተምሩትና እንደሚሞግቱት፣ የእኛም አገር ምሁራን የማኅበራዊ ሚዲያውን አቅም ሳይንቁና ሳይሸሹ ተጽዕኖውን ለማቅለል፣ እንዲሁም ችግሮችን ለማረቅ የመሥራት ግዴታ አለባቸው ነው ያሉት።

‹‹በአንድ አገር እየኖርን የማንደማመጥ እና የጋራ ዓላማ የሌለን ሕዝብ እየሆን ስለመጣንና አገራችንን ለመገንባትም ሆነ ለማፍረስ የማኅበራዊ ሚዲያው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው የሚሉት የሚዲያ ባለሙያው፣ ኹሉም ዜጋ ለአገሩ ክብርና ለሰው ልጆች መልካም ኑሮ በኃላፊነት እንዲሠራ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!