የእለት ዜና

በአለርት ሆስፒታል የተገልጋዮች ቁጥር መብዛት ታካሚዎችን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑ ተገለጸ

በአለርት ሆስፒታል የሕክምና አግልግሎት የሚያገኙ ታካሚዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑን ተገልጋዮች እየተጉላሉ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ፣ በየሕክምና መስጫ ክፍሎች በር ላይ ወረፋ የሚጠባበቁ በርካታ ታካሚዎችን ለማየት ችላለች። የቆዳ፣ የቁስል፣ የውስጥ ሥጋ ደዌ እና የተመላላሽ ቀዶ ሕክምና፣ ብሎም የእናቶች የወሊድ ክትትል አግልግሎት ከፍተኛ ወረፋ የሚታይባቸው የሕክምና አገልግሎት መስጫዎች ናቸው። በዚህም በመድኃኒት አቅርቦት እና በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች መኖራቸውን ነው ታካሚዎች የተናገሩት።

ለዚህም አንዱ ምክንያት፣ ብዙ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎች ቶሎ ስለማይገቡና ሊቀሩም ስለሚችሉ ነው ሲሉ ታካሚዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የሕክምና ባለሙያዎች የቅርብ ዘመዳቸውን ወይም ጓደኛቸውን ቅድሚያ አግኝቶ እንዲታከም ማድረጋቸው ደግሞ በር ላይ ቁጭ ብለው የሚጠባበቁ ታካሚዎች ረዥም ጊዜ ቁጭ ብለው እንዲጠብቁ የሚያደርግ ጉዳይ መሆኑንም ጨምረው ተናገረዋል።

አዲስ ማለዳ በተለይ በርካታ የቁስል ታካሚዎች እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ምንም ዓይነት አገልገሎት ሳያገኙ ቁጭ ብለው ሲጉላሉ በማየቷ፣ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑትን ዶክተር አድማሱን ለምን ሆነ ስትል ጠይቃለች። እርሳቸውም ይህ የሚሆነው ሐኪሞች በጠዋት ገብተው ስፔሻላይዝ የሚያደርጉ ተማሪዎችን ስለሚያስተምሩና ባለፈው 24 ሰዓት ውስጥ የተሰጡ ሕክምናዎች ላይ ቁጭ ብለው ስለሚወያዩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ለድንገተኛ ታማሚዎች ካልሆነ በስተቀር ካርድ ማውጣት እንደማይቻልና በዚህም ራቅ ካለ ቦታ የትራንስፖርት ወጭ አውጥተው የሚመጡ ታካሚዎች እንደሚጉላሉ ለተነሳው ቅሬታም ዳይሬክተሩ፣ በ‹ሪፈር› ከ11 ጤና ጣቢያዎች የሚመጡ ታካሚዎችን ስለሆነ የምናገለግለው ከፍተኛ የታካሚ ቁጥር በመኖሩ ነው ብለዋል።

በሆስፒታሉ የእርግዝና ክትትልና የወሊድ አገልግሎት የሚያገኙ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑም ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው አሳውቀዋል። ልምድ ያላቸው ሐኪሞችም ለእናቶች ክትትል ከሰዓት በኋላ እንደማይገኙም በታካሚዎች ተጠቁሟል።
ብዙ ጊዜ የቀጠረን ዶክተር ሊቀር ይችላል፤ መቅረቱንም የምናውቀው እዚህ ከመጣን በኃላ ነው የሚሉት ታካሚዎች፣ ይህም የሚሆነው ሐኪሞች ውጭ ላይ የግላቸውን ሥራ ስለሚሠሩ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለጹት። በዚህ ጉዳይ ላይ ዶክተር አድማሱ፣ ማንኛውም ሐኪም ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በሥራው እንደሚገኝ ገልጸው፣ የሆስፒታሉ ሐኪሞች በክፍለ አገር ላሉ ሐኪሞች የ‹ኦንላይን› ዕገዛ ስለሚሰጡ፣ ጽኑ ሕሙማን ስለሚከታተሉና የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ስለሚሠሩ እንደሌሉ ተቆጥሮ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ዶክተር አድማሱ እናቶች ማንኛውንም ሕክምና በነጻ እንደሚያገኙ ቢገልጹም፣ የወሊድ አገልግሎት የሚያገኙ እናቶች ከሚያነሱት ቅሬታ አንዱና ዋነኛው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ነው። በዚህም በተለይ ቅዳሜና እሁድ የሆስፒታሉ ግምጃ ቤት ዝግ ስለሚሆን ጓንትና ሌሎች መድኃኒቶችን ከውጭ በውድ ዋጋ ለመግዛት እንደሚገደዱ ነው የተናገሩት።

በሆስፒታሉ በተጨማሪ የዓይን ሕክምናም የሚሰጥ ሲሆን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ ታካሚዎች በግላቸው ከፍለው ሕክምና እንደሚያገኙና ከዘጠኝ ሰዓት በፊት የሚመጡ ታካሚዎች ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገሩ አስረድተዋል። ዳይሬክተሩ ግን ከ11 ሰዓት በፊት ማንኛውም የዓይን ታካሚ መደበኛውን የሕክምና አግልግሎት እንደሚያገኝ ነው የገለጹት። ሆኖም ሐኪሞች ከዘጠኝ ሰዓት ጀምረው ቅድመ-ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።

በሆስፒታሉ ከፍተኛ የታካሚዎች ቁጥር የኖረው እና መጨናነቅ የተፈጠረው፣ ሆስፒታሉ የታካሚዎችን ቁጥር በመጨመር ተሸላሚ ለመሆን ስለሚፈልግ ነው መባሉን ተከትሎ፣ ዶክተር አድማሱ ተሸላሚ የምንሆነው በጥራት እንጂ በቁጥር አይደለም ነው ያሉት። አክለውም የመንግሥት ሆስፒታሎች ወደ መሀል ከተማ ስለሚገኙ በፊት በሪፈር እንቀብል ከነበረው ስድስት ጤና ጣቢያዎች አሁን ወደ 11 ከፍ አድርገናቸዋል ብለዋል። ከአሮሚያ፣ ከጉራጌ እንዲሁም እንደ ቆዳና የዓይን ሕክምና ላሉ አገልግሎቶች ከመላ አገሪቱ ካሉ ጤና ተቋማት በሪፈር የሚመጡትን እንቀበላለንም ሲሉ ተናግረዋል። ከሱማሌ ላንድ መጥተው መታከም የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። በቀጣይ አስራ አንዱን ጤና ተቋማት እንዲበቁ በማድረግ አላስፈላጊ የሆኑ ሪፈራሎችን በማስቀረት የታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሆስፒታሉ እየሠራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ዶክተር አድማሱ በመጨረሻም፣ አለርት ሆስፒታል ከተመሠረተ ረዥም ዕድሜ ስላለው ታካሚዎችን እያስተናገድን ያለው ድሮ በነበሩ አገልግሎት መስጫዎች ነው ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!