የእለት ዜና

በመተከል ዞን የሚገኘው ታጣቂ ቡድን በየደረሰበት ንጹኃንን እየገደለ ነው ተባለ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተሠማራው መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ በዞኑ ታጥቆ በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ የታጣቂው አባላት በየደረሱበት ንጹኃን ሰዎችን እየገደሉ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን፣ በተለይም በመተከል ዞን፣ በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ጥቃት አለመቆሙን ተከትሎ መከላከያ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን የዞኑ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። መከላከያ በሚወስደው ዕርምጃ “እየተበታተኑ ነው” የተባለው የታጣቂው ቡድን አባላት በየደረሱበት አካባቢ ንጹኃን ሰዎችን እየገደሉ ነው ተብሏል።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት እስካሁን ንጹኃን ሰዎችን ከገደሉባቸው የዞኑ አካባቢዎች መካከል ግልገል በለስ አንዱ ሲሆን፣ ከመከላከያ ጥቃት የሸሹ ታጣቂዎች ግልገል በለስ ላይ ሦስት ሰዎችን ገድለዋል ተብሏል። መንግሥት በወሰደው የማጥቃት ዕርምጃ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ለጊዜው ከማጥቃት የታቀቡ ቢሆንም፣ ከመንግሥት ጥቃት የተረፉ የታጣቂው ቡድን አባላት ከገደሏቸው በተጨማሪ ያቋሰሏቸው ሰዎች መኖራቸው ተገልጿል።

የመከላከያ ጥቃት ጥሩ ዕርምጃ መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ ነዋሪዎች፣ ዕርምጃ መውሰዱ ሲቋረጥ መልሰው ንጹኃንን የማጥቃት አድል ስለሚፈጠርላቸው ያልተቋረጠ ሕጋዊ የማጥቃት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ቦዴፓ) የመተከል ዞን ወቅታዊ ኹኔታን አስመልክቶ ባሳለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ “የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል እና የከማሺ ዞኖች አሁናዊ የጸጥታ ኹኔታ መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ቢጀምርም፣ አሁንም አልፎ አልፎ ጥቃቶች ሊቆሙ አልቻሉም” ብሏል።

“ከሰሞኑ መንግሥት በመተከል ዞን ተጨማሪ ኃይል በማሠማራት የተለያዩ ዕርምጃዎች መውሰድ ቢጀምርም፣ ይህንን ተገን በማድረግ ንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በተለይ በመተከል ዞን ድባጤ እና ቡለን ወረዳዎች ብሔርና የፖለቲካ አመለካከትን መሠርት በማድረግ በዜጎች ላይ እስራትና ግድያ እየተፈጸመ ይገኛል” ብሏል።

ፓርቲው በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ እያለ በጸጥታ አስከባሪዎችና በወረዳ አመራሮች የሚደረጉ እስራትና ወከባዎች ከአሁኑ የፓለቲካ ምህዳሩን እያጠበቡት መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠይቋል። “የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማጥበብ፣ ሥጋትና ውጥረት ለመፍጠር ማንነትንና የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት ያደረጉ እርምጃዎች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የማያሰፍኑ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታርሙ” ሲል የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

ፓርቲው አደረኩት ባለው አጭር ዳሰሳ ጥናት፣ ዜጎች ከመደበኛ ማረሚያና ማረፊያ ቤቶች ውጭ ለረጅም ጊዜ እየታሠሩ ይገኛሉ ብሏል። ይህ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት የሚያጋልጥ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ መንግሥት በፍጥነት ማስተካከያ እንዲያደርግና ያለአግባብ ታስረው የሚገኙ ዜጎቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል።

የመንግሥት ኃይል አጠቃቀምና ሕግ ማስከበር ሒደት ሕግን የተከተለ፣ እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት የጠቆመው ፓርቲው፣ ከዚህ ባሻገር የሚደረጉ ሕገ-ወጥ አካሄዶች ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ፣ መንግሥት ተገቢውን የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድ የቦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሳስቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!