የእለት ዜና

ሰቆጣ ማይኒንግ ይዞታውን ለቆ መውጣቱን አስታወቀ

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን፣ ሰቆጣ አካባቢ በሦስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ በብረት ማዕድን ሥራ ፈቃድ ወስዶ ሲነቀሳቀስ የነበረው ሰቆጣ ማይኒንግ እና የንግድ አጋሮቹ የሆኑት የሩሲያ ባለሀብቶች አካባቢውን ጥለው መውጣታቸውን አስታወቁ።
ሰቆጣ ማይኒንግ በ2012 መገባደጃ የብረት ማዕድን ለማውጣት ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜው በነበረው የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት እና የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ምርት መግባት አልቻለም ነበር። ድርጅቱ የምርት ሥራውን በ2014/15 ለመጀመር ዕቅድ የያዘ ቢሆንም፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በዕቅዱ መሠረት መቀጠል ባለመቻሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ሉቺያኖ ፊራኖሊን የሰቆጣ ማይኒንግ የአክስዮን ባለድርሻ እና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ሰዓት ዕቃዎቻቸውን እና ማሽነሪዎችን ከአካባቢው እንዳስወጡ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“በመጀመሪያ ዕቅዳችን ከውጪ የሚገባውን ብረት ከ25 እስከ 30 በመቶ መተካት የነበረ ሲሆን፣ በሙሉ አቅማችን ማምረት ስንጀምር ደግሞ ወደ 400 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ብረት ለአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ነበር” ሲሉ ለቺያኖ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሰቆጣ ማይኒንግ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት በቀድመው የማዕድን፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚነስቴር፣ በአሁኑ የማዕድን ሚኒስቴር የ20 ዓመት የፍለጋ ፈቃድ ወስዶ ወደሥራ የገባ ሲሆን፣ ድርጅቱ ‹ሲኖ ስቲል› የተባለ የቻይና በማዕድን አዋጭነት እና ምርመራ ላይ የተሠማራ ድረጅት ጥናት እንዲያካሂድለት አድርጎ በ242 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከ100 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆን የብረት ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁሟል።

ደርጅቱ ወደ ምርት ሲገባ አገር ውስጥ ያሉትን ከ150 በላይ የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን በተለይም የብረት ባር እና ፌሮ አምራቾቸን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ታስቦ ነበር። የዓለም የብረት ዋጋ እየናረ ነው፤ አገሪቱ የምታወጣውም ወጪ እንደዛው እየጨመረ ነው፤ ስለዚህም የአገሪቱ ሰላም ሲመለስ ቀናት ሳናባክን ወደ ሥራ ገብተን ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፈን ለዓለም ገበያም እናቀርናለን ሲሉ ሥራ አስፈጸሚው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአገር ውስጥ በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች፣ ከ157 ሚሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን እንዳለ የተረጋገጠ ሲሆን፣ አንድ ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ ብረት እንዳለ የመስክ ምልከታ ግምቶች ያሳያሉ። ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እና የሌሎች አገራትን ለአብነት የቻየና፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካ ተሞክሮን በመውሰድ፣ ለገቢ ብረት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሬ ለማስቀረት በአነስተኛ ማዕድን አውጪዎች ብረት እያወጡ ለፋብሪካ ማቅረብ እንዲችሉ የሚያደርግ የቅድመ አዋጨነት ሥራ መጀመሩን የብረታ ብረት ኢንዱስተሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንጅነሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር ተረዳ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት እንደ ብረት፣ ከሰል እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ ለኹለት ዓመታት በጀኦሎጂካል ሰርቬይ በተጠናው ጥናት፣ በጎጃም መርጡ-ለማርያም፣ መካነ ሰላም እና በደቡብ ወሎ የብረት ክምችት መገኘቱ ተረጋግጧል።
ይህንንም ተከትሎ የ‹ሲ ኤን ዲኢ› ብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ እህት ኩባንያ የሆነው ‹አጎዶዮ› በከሰል ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ በመካነ ሰላም የብረት ማዕድን ለማውጣት ፍቃድ ወስዶ በመንቃሳቀስ ላይ ይገኛል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!