የእለት ዜና

‹ግሪንቴክ አፍሪካ› የተሰኘ ነዳጅ ቆጣቢ መሣሪያ የኢትዮጵያን ገበያ ሊቀላቀል መሆኑ ተገለጸ

ቲቢኬ አስመጪና ላኪ ኃ/የተ/የግል ማኅበር ነዳጅ ቆጣቢ እና የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀትን የሚቀንስ ነው ያለውን ግሪንቴክ አፍሪካ የተሰኘ በመኪና ላይ የሚገጠም መሣሪያ ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ።
ነዳጅ ቆጣቢ መሣሪያው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ለሰጡ አሮጌ ተሸከርካሪዎችም ሆነ ለአዲሶቹ ተሸከርካሪዎች ሊገጠም እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ቴክኖሎጂው የመኪና ነዳጅ ፍጆታን ከ15 እስከ 30 በመቶ፣ እንዲሁም ከመኪኖች ወደ ከባቢ አየር የሚወጣውን በካይ ጋዝ በ80 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል።
የቲቢኬ አስመጪና ላኪ ኃ/የተ/የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በቀለ ማሞ፣ ድርጅቱ መሣሪያውን ወደ አገር ውስጥ ከማስግባቱ በፊት ለኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሥርዓት ተስማሚነቱን ለማረጋገጥ አስፈላጊው ፍተሻ እንደተደረገለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የግሪንቴክ አፍሪካ ምርት በአሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና እና አውሮፓ ባሉ ዕውቅ የዘርፉ ላብራቶሪዎች መፈተሹን የገለጹት በቀለ፣ ቲቢኬ አስመጪና ላኪ ከቴክኖሎጂው አምራቾች ጋር ከ2 ዓመት በላይ በጋራ ሲሠራ መቆየቱንና በአሁኑ ሰዓትም ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
ቴክኖሎጂው በተሸከርካሪ ላይ ከተገጠመ እስከ 10 ዓመታት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) እስከ ከባድ ተሸከርካሪዎች ድረስ በየመጠናቸው መዘጋጀቱንም በቀለ ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ነዳጅ የመቀጣጠል አቅምን ስለሚያፋጥን የተሽከርካሪ ሞተርን እንደሚያጸዳ የተገለጸ ሲሆን፣ የተሻሻለ የነዳጅ ኢኮኖሚ፣ ዝቅተኛ ልቀትና ተጨማሪ የፈረስ ጉልበት ያስገኛል ተብሏል።
ምርቱን በአከፋፋዮች በኩል ወደ ገበያ ለማሰራጨት እንደታሰበ እና ከ2000 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችም የሥራ ዕድል በመፍጠር በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንደሚገጠምም ተነግሯል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት ያዕቆብ ያለው በበኩላቸው፣ በመንግሥት በኩል የተሸከርካሪ በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን በመግለጽ፣ በዚህም አስፈላጊ ቴክኖሎጂ የደረጃ ማውጣት ሥራ ተሠርቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እስከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ተሸከርካሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ተሸከርካሪዎች ረጅም ዓመታትን በአገልግሎት ያሳለፉ መሆናቸውም ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!