የእለት ዜና

የግንዛቤ ሕክምና የጡት ካንሰርን ለመከላከል

‹‹አትድኚም ብለውኝ ነበር›› ስትል ንግግሯን ጀመረች። የጡት ካንሰር በዝምታ ደረጃውን አሳድጎ ሕመም አበርትቶባት ወደ ሕክምና ተቋም በሄደች ጊዜ ነው ይህን ያሏት። ካንሰሩ ከጡቷ አልፎ ወደ አንገቷ ስለተሠራጨ ከባድ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ሲነግሯትም ተስፋ ቆርጣ ነበር። ቢሆንም ሕክምናውን እንድታደርግ ተወሰነ። ሕክምናው ቀላል አልነበረም፤ በቀዶ ጥገና ጡቷን እንድትቆረጥ ግድ አላት። ይህን ትኩስ ቁስል ይዛ ታድያ ቤተሰቧን ትታ ወደመጣችበት ወደ ጎጃም ተመለሰች እንጂ አዲስ አበባ ተጠግታ የምትቆይበት ቦታ አልነበረም።
ከዛም ለክትትል ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች፤ ካንሰሩ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ‹ኬሞቴራፒ› እንድትጀምር ተባለች። ለስድስት ወር ስምንት ያህል ጊዜ ኬሞ ተከታትላ ጨረሰች። አሁን ነገሮች ደኅና የሆኑ ይመስላል። ሦስት ዓመት እንዲህ በዝግታ አለፈ።
ከሦስት ዓመት በኋላ ተመልሳ አዲስ አበባ ተገኘች። ጥሩ ዜና አልሰማችም፤ ካንሰሩ ተክቷል ተባለች። ይሄኔ ግራ መጋባትና ጭንቀት ከበባት። ናሙና ተወስዶ ተመረመረ፤ እውነት ነበር። እናም ዳግም የቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ተረዳች። በዚህ ጊዜ ተስፋ ቆርጣ፣ ‹የለም! አገሬ ገብቼ ብሞትም ከልጆቼ ጋር ልሁንና ልሙት!› ብላ ነበር። ይሄኔ ነው ከዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን ሰዎች ጋር የተዋወቀችው፤ ፋውንዴሽኑ ባለታሪካችንን ንጹህን ያገኛት በዛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆና ነው።

ንጹህ በርትታ ኹለተኛውን ቀዶ ጥገና አከናወነች። በፋውንዴሽኑ የፒንክ ሐውስ ወይም ‹ገነት› ተብሎ በሚጠራው ጊዜያዊ የካንሰር ሕሙማን መቆያ ማዕከል ቆይታ እንድታደርግ፣ የሚያስፈልጋትን በበቂ ሁኔታ እየተመገበችና እያገኘች በቅርቡ ሕክምናዋን እንድትከታተል ያስቻላትም ፋውንዴሽኑ ነው።

‹‹እንደ እናቴ ቤት ከፍቼ ነው የምገባው›› ስትል ስለ መቆያ ስፍራው አገልግሎት ትገልጻለች። ንጹህ ታድያ ትግሏ ከካንሰሩ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም እንዲህ አለች፤ ‹‹አሁንም ቢሆን ክፍለ አገር መሄድ ያስጠላኛል። ብሰማም ባልሰማም፤ ምን ኃጢአት ሠርተሸ ነው ጡትሽ የተቆረጠ ይሉኛል። እኔ ከሁሉም በላይ ኃጢአት የሠራሁ አይመስለኝም! በዘሬም የለብኝም (ካንሰር)፤ ታድሎኝ ነው’ንጂ›› አለች።

ካንሰር፣ ሕክምናውና የግንዛቤ ችግር
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በአንዲት አዳጊ አገር የካንሰር ሕመምና ሕክምናው ሊኖረው ከሚችለው ተጠባቂ ችግር በላይ ተደራራቢ የሚሆኑ ፈተናዎች አይጠፉም። የእነዚህ ኹሉ ምንጭ ደግሞ የግንዛቤ ችግር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ካንሰር አሁን ላይ በአዳጊ አገራት 26 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደሚገኝም ጥናቶች ያመላክታሉ።

ካንሰርን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳይቻል ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ቀድሞ የሚጠቀሰው ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት አርፍደው መሄዳቸው እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቀድሞ ወደ ሕክምና መምጣት ቢቻል ግን 90 በመቶ የሚሆኑ የካንሰር ሕመም ያለባቸውን ሰዎች በቶሎ ማገዝና ማዳን እንደሚቻል ነው የሚነሳው።

ፊፊ ደርሶ በዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን እንዲሁም የፒንክ ሐውስ መሥራቾች መካከል ናቸው። ፋውንዴሽኑ እንዲመሠረት ምክንያት ስለሆኑት እህታቸው ዓለምፀሐይ ጥቂት ያወሳሉ። በዛም ውስጥ የነበረውንና ያለውን የግንዛቤ ዕጥረት አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል። በዛም ዓለምፀሐይ በካንሰር ሲታመሙ ‹ያ በሽታ!› ይባል እንደነበርና ከብዙ ቤተሰብና የአካባቢ ማኅበረሰብ ተደብቆና በምስጢር ተይዞ የነበረ ጉዳይ እንደሆነ ያወሳሉ።

‹‹ጡቷ ተቆርጦም ‹ተሠራልኝ› ነበር የምትለው፤ ማኅበረሰቡ ጋር የግንዛቤ ችግር ስላለ በግልጽ አትናገርም ነበር። ለስድስት ወር ያህል የተለያየ ሕመም ነው በሚል ግምት ካንሰሩ ሳይታወቅ ቆይቷል። በዛም ምክንያት እየተሰራጨ ከባድ ደረጃ ላይ ደረሰ። እርሷም ለሰው ስለማትናገር በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስና በሥነ-ልቦና ተጽዕኖ ፈጥሮባታል›› ሲሉ የነበረውን አስታውሰው ይናገራሉ።

በጥቁር አምበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኤዶም ሰይፈ የግንዛቤ እጥረት አለ በሚለው ነጥብ ላይ በሚገባ ይስማማሉ። የጡት ካንሰርን በተመለከተ ካሉ ችግሮች መካከል የግንዛቤ ችግር ዋናውና መነሻው ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ጋር ሲባል ሴቶች እህቶችና እናቶችም ወደ ሕክምና ከመሄድ ይልቅ ዝም ብሎ መቀመጥን እንዳይመርጡ ለማስቻል ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ግን ይህ ችግር ያለው በስፋት ካለው ማኅበረሰብ ጋር ብቻ አይደለም ባይ ናቸው። የግንዛቤ ችግርን ለመፍታት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ላይ ቅንጅት አለመኖሩም ይህን ችግር ያባብሰዋል ብለዋል። ‹‹ድንበር አስምረን ሳይሆን ተባብረን በጋራ ብንሠራ ሰዎችን ማትረፍ እንችላለን። እስከአሁንም የበለጠ መሥራት እንችል ነበር›› ሲሉ አክለዋል።

በተመሳሳይ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር የሚገኝ ውስን እውቀትም እንዳለ አልሸሸጉም። ‹‹የጤና ረዳቶች፣ ሐኪሞችና ነርሶች፣ ወዘተ. ቅድሚያ በነበራቸው ሥልጠና ላይ ለካንሰር የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነበር›› ያሉት ዶክተር ኤዶም፤ በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የምርምር ውጤቶች ስለማይታወቁና በሽታውን ከሚገባው በታች ቀለል በማድረግ ‹‹ይድናል! ማስታገሻ ውሰዱ›› የሚል ትዕዛዝ የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ይህም ታማሚዎች የካንሰር ሕክምናን በጊዜ እንዳይጀምሩ ያደርጋል።

ሌላው ዶክተር ኤዶም ያነሱት የካንሰር ምርመራን ነገር ነው። የካንሰር ምርመራ ወጪ እንዲሁም ወረፋ ቀላል እንዳይደለ ጠቅሰዋል። ከተደራሽነት አንጻርም በከተማ እንጂ በገጠር በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱን አመላክተዋል። ከዛም ባለፈ ብዙ መሰናክሎችን አልፈው ወደ ሕክምና የሚያቀኑ ሰዎች ስለሕክምና አሰጣጡ፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድና የሚኖረውን ሒደት በሚመለከት የሕክምና ባለሙያዎች በቂና ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የካንሰር ሕክምና በሂደቱ ለታካሚ መንፈሳዊ፣ አካላዊ፣ የቤተሰብና አካባቢ ድጋፍ መስጠትን የሚጠይቅ ነው። ይህንና የተባሉት ግንዛቤዎች ታድያ በሰዎች ዘንድ ካልተፈጠሩ፣ ዛሬ ወደ ሕክምና የመጡ ሕሙማን በማግስቱ ተመልሰው ወደዛ የጤና ክብካቤ አገልግሎት መስጫ አያቀኑም።

ነርስና የማኀበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ ኤልሳቤት ደሳለኝ በዚህ ላይ ሐሳባቸውን አክለዋል። እርሳቸው በበኩላቸው የካንሰር ምርመራም ሆነ ሕክምና ለማድረግ አልፎም ለሕክምና እና ለመድኃኒት ክትትል ከሚያስፈልገው ወጪ በላይ የማኅበረሰብ ሥነልቦና ውቅርን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል። ‹‹ታካሚዎች ካንሰር እንዳለባቸው ሲነገራቸው፣ ካንሰሩ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ቢሆን እንኳ ከሐኪም ይልቅ ማኅበረሰቡን ያምናሉ። እናም እገሊት ጥሪቷን ጨርሳ መች ዳነች፣ ተስፋ የለውም ወደሚለው ያዘነብላሉ›› ሲሉ ይናገራሉ።

ሌላው ኤልሳቤት ባነሱት ነጥብ እንዳወሱት፣ በኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ ለካንሰር ሕከምና በሚመጡ ሴቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከገጠራማው ክፍል የሚመጡ ናቸው። እነዚህም በኢኮኖሚ ጥገኛ በመሆናቸው ለሕክምና አዲስ አበባ ማቅናት ቢፈልጉ እንኳ የትዳር አጋራቸው ውሳኔ ትልቁን ሚና ይይዛል።

ምን ይበጃል?
ዶክተር ኤዶም ሲናገሩ፤ ሁሉንም ችግር ትኩረት እንስጠው ይላሉ። በዚህም መሠረት ግንዛቤ መፍጠር፣ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሠልጠን ጨምሮ፣ ወጪና ጉልበት የሚጠይቁ ቢሆንም፣ ሊሠራባቸው ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። እገዛ ከተገኘ፤ ልክ ባለፈው አምስት እና ስድስት ዓመት የካንሰር ባለሙያዎች ሥልጠና ተጀምሮ ያንን ማስፋፋት እንደተቻለው ሁሉ፣ በዚህም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል። በተጓዳኝ ባለሙያዎችን ለማገዝ በሙያው ስር የሚዘጋጁ የሥራ መመሪያዎችን በኅትመት መልክ ለብዙ የጤና ባለሙያዎች ማዳረስ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ተቋማትን ማስፋፋትና ሕክምናውን ተደራሽ ማድረግ ሌላው ዶክተር ኤዶም ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ነው። ‹‹ለብዙ ዓመታት የካንሰር ሕክምናው ላይ ብዙ አልተሄደም ነበር። ባለፉት 20 ዓመታት ግን በዓለማችን ላይ የጡት ካንሰር ሕክምናን በተመለከተ አዳዲስ የምርመራ ውጤቶችና መድኃኒቶች ይወጣሉ። ሁሌም አዲስ ግኝት ስላለ በሦስትና ስድስት ወር መመሪያ ይታደሳል። በሕክምና የታካሚዎችን ቆይታ ማራዘም እንዲሁም ሕመምና ስቃይ መቀነስ የሚያስችሉ መድኃኒቶች ግኝቶች፣ በፍጥነትና እኛ መድረስ እስኪያቅተን ድረስ ዘርፉ እየሰፋ ነው። እኛ ገና ኬሞ ቴራፒ ማዳረስ ላይ ነን›› ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።

ዶክተር ሲና ዱጋሳ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽኑ ሕሙማን ሕክምና ትምህርት ክፍል መሪ እና የጽኑ ሕሙማን ክብካቤ ላይ የሚሠሩ ባለሙያ ናቸው። ሴቶች በተለይም የራሳቸውን ጡት በየጊዜው በቀላሉ መመርመርና አዲስ ነገር መኖር አለመኖሩን መከታተል እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ይህን ለማድረግም የሚመለከታቸው አካላት ከመገናኛ ብዙኀን ጋር በስፋት መሥራት እንዳለባቸው ያምናሉ።

‹‹ራስን መመርመር እንዴት እንደሆነ መጀመሪያ ሒደቱን ማወቅ ያስፈልጋል፤ በጣም ቀላል ነው። ይህን ማድረግ ችግር ካለ በቅድሚያና በቶሎ ማወቅ ያስችላልና፤ አንዲት ሴት ይህን መከታተልና ማወቅ አለባት›› ሲሉም መክረዋል።
አያይዘውም ልምድን የማካፈል ጥቅምን አንስተዋል። በተለይም ከካንሰር ጋር ታግለው ድል ያደረጉ ሴቶች ጉዟቸው ምን ይመስል እንደነበር በመግለጽ ለብዙዎች በተምሳሌትነት ሊቀመጡ ይችላሉ ብለዋል። ከዛም በላይ በየዓመቱ አንድ ሰሞን፣ ሳምንት ወይም ወር ጠብቆ ሳይሆን በየጊዜው ማኅበረሰቡን ማንቃት፣ ሴቶች ራሳቸውን እንደሚመረምሩና እንዲከታተሉ ማድረግ፣ መጠቆምና መምከር እንደሚያሻ ሐሳባቸውን ሲሰጡ ያስተላለፉት መልዕክት ነው።

ከዛም በተጓዳኝ አሁን ላይ ብዙ ወጣት ሴቶች ላይ ነውና የጡት ካንሰር ሕመም እየታየ ያለው፣ በዚህ ዙሪያ ጥናት የማድረግ አስፈላጊነትን ሳያነሱ አላለፉም። ማንኛውም አገር ላይ ተመሳሳይ መልክ ላይኖር ይችላል ያሉት ዶክተር ሲና፣ እንዴት ነው መቀየርና ማሸነፍ የሚቻለው፣ አኗኗራችን የቱ ተቀይሮ ነው ካንሰር እንዲህ ሊስፋፋ የቻለው፣ ወዘተ. የሚሉ ነጥቦች ላይ የተጠናከረ የምርምር ሥራ መሥራት፣ ቢቻል የምርምር ማዕከል መክፈትም ያስፈልጋል ብለዋል።

ኤልሳቤትም በበኩላቸው ከላይ ከተነሱት መካከል የሚጋሯቸው ሐሳቦች አሉ። ይልቁንም ዓርአያ የሚሆኑና ካንሰር የነበረባቸው ግን የዳኑ ሰዎች በቅርባቸው ላለ ማኅበረሰብ ግንዛቤ ሊሰጡ ይገባል። ይህም የበለጠ ተዓማኒና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆን ነው ነርስና የማኅበረሰብ ጉዳዮች ባለሙያዋ ያስረዱት።

አያይዘውም በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ታካሚዎች ጥቂት ጭብጥ ቆሎና ዳቦ ይዘው ሕክምናውን ለመከታተል ከባድና ፈታኝ፣ የማይቻልም እንደሚሆንባቸው ያስረዳሉ። ለዚህም የዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ማዕከልን ያመሰገኑ ሲሆን፣ ቢያንስ ሕክምና የሚከታተሉ ሴቶች በሚገባ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲመገቡ ማድረጉ ትልቅ ሥራ እንደሆነ መስክረዋል።

በዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን፣ ፒንክ ሐውስ የተባለው ጊዜያዊ የካንሰር ሕሙማን ማቆያ ከተመሠረተ ዐስር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ገና ኹለተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል። ከአዲስ አበባ ውጪም ጎንደር ላይ ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን፣ ይህም የአምስት ወር ዕድሜ ያስቆጠረ ነው።

ፋውንዴሽኑ ሴቶች ይልቁንም የካንሰር ምርመር፣ ሕክምና እና ክትትል ለማድረግ የአቅም እና የገንዘብ ውስንነት የገጠማቸውን ማገዝን ሥራዬ ብሎ የያዘ ድርጅት ነው። ርዕዬ ብሎ የያዘውም ግንዛቤ መፍጠር እና ቅድመ ልየታን በመጠቀም ከካንሰር ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ይላል። ተቋሙ ዘንድሮ 2014 ለኹለተኛ ጊዜ የጡት ካንሰር ወርን ምክንያት በማድረግ የእግር ጉዞ አካሂዷል። ይህም የማቆያ ማዕከሉን ከማስተዋወቅ ባሻገር ገቢ ለማሰባሰብ እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚገናኙበትን ዓውድ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com