የእለት ዜና

ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር እንዴት ትውጣ?

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከአንድ ዓመት በፊት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ቀጥሏል።
መነሻውን ትግራይ ክልል ያደረገው ጦርነት ከሐመሌ መጀመሪያ ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልል የተወሰነ ሲሆን፣ በተለይም በአማራ ክልል ጦርነቱ በአንደኛ ዓመት ዋዜማው ላይ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ተስፋፍቷል። ጦርነቱ ለኢትዮጵያ ሕልውና አስጊ መሆኑን መገንዘቡን የጠቆመው መንግሥት፣ በመላው አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውጇል።
የተስፋፋውን ጦርነት መንግሥት ብቻውን ሊቀለብሰው እንደማይችል የገለጸ ሲሆን፣ ኹሉም ዜጋ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት ችግር ለመታደግ እና ጦርነቱን ለማሸነፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። ህወሓት በወረራቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ላይ ንጹኃን ዜጎችን እየገደለ፣ እያፈናቀለ እና የመንግሥትና የዜጎችን ንብርት እየዘረፍ እና እያውደመ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን ይህን ችግር እንድትሻገር እና ጦርነቱን እንድታሸንፍ እንደ ሕዝብ የተደራጀ እና የተቀናጀ የጋራ ትግል አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር እንዴት መውጣት እንዳለባት እና አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እንዴት መመራት እንዳለበት የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ባለሙዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድጎታል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እንደ “አገር የመቀጠል ወይም ያለ መቀጠል” መንታ መንገድ ላይ እንደሆነች ብዙዎች ሲገልጹ ይሰማል። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚያነሱት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከዓመት በፊት የተጀመረው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ እና እልባት አለማግኘቱ መሆኑን ይገልጻሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት አሁን ላይ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ኢትዮጵያ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንድትገባ እንዳደረጋት የፖለቲካ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። አንደኛ ዓመቱን ባሳለፍነው ረቡዕ የደፈነው ጦርነት የተጫረው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በሚገኙ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ነበር።

መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው ጦርነት ለስምንት ወራት በክልሉ ተገድቦ የቆየ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር አሰማርቶት የነበረውን የመከላከያ ኃይል ሰኔ 21/2013 የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ማስወጣቱ ህወሓት ኃይሉን እንዲያደራጅ ዕድል አግኝቷል። በዚህም ህወሓት የአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን ከሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ እንዲወርና ጦርነቱ እንዲባባስ አድርጓል።

የህወሓት ታጣቂዎች በደረሱባቸው በአማራ እና በአፋር ክልል የሚገኙ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ታጣቂዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና የንብረት ዘረፋ መፈጸማቸውን መንግሥት ከዚህ በፊት ባወጣቸው መረጃዎች ገልጿል።
ህወሓት ጦርነቱን በአማራ እና አፋር ክልል ላይ ከጀመረ ከሦስት ወራት በላይ የሆነው ሲሆን፣ ቡድኑ በየጊዜው ጦርነቱን እያስፋፋ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ተከትሎ፣ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሕዝቡ ጦርነቱን ለመመከት እንዲቀላቀል ጥሪ አድርገዋል።
በዋናነት ጦርነቱ እየተካሄደበት የሚገኘው አማራ ክልል መንግሥት፣ ህወሓት “በሕዝባዊ ማዕበል” ጦርነት እያካሄደ በመሆኑ፣ ጦርነቱን ለመመከት ማንኛውም ለጦርነት ብቁ የሆነ ሰው ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት የክተት ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥት በበኩሉ፣ ህወሓት እያካሄደ ያለውን ጥቃት ለማስቆም እና ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ የመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር እና አንድነት እንደሚያስፈልግ ገልጿል። በዚህም ኹሉም ክልሎች በጦርነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ብሎም ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና በመከላከያ ኃይል ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ ወጣቱ ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት ጥሪ አቅርቧል።

በአንደኛ ዓመቱ ዋዜማ የተባባሰው ጦርነት ህወሓት ከያዘው ዓላማ አንጻር ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ እንደተጋረጠባት የገለጸው የፌደራል መንግሥት፣ ችግሩን ለመቀልበስ ለስድስት ወር የሚዘልቅ አስቸኳይ ጊዜ አውጇል። አስቸኳይ ገዜ ዐዋጁ ከወጣትበት ጥቅምት 23/214 ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ ተፈጻሚነቱ በብሔራዊ ደረጃ ነው።

አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ፣ “የአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ ዐዋጅ ቁጥር 5/2014” ሲሆን፣ “መንግሥት የአገርን ሕልውና፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፣ የሽብርተኛው ሕውሓት እና የሽብር ግብረ አበሮቹ እንቅስቃሴ በአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ የደቀነ በመሆኑ፣ ሽብርተኛው ህውሓት እና የሽብር ግብረ አበሮቹ ለዕኩይ ዓላማቸው መሳካት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በንጹኀን ዜጎች ላይ እየፈፀሙ ያሉት ግድያ፣ ዝርፊያ እና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢሰብዓዊ ጥቃቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከግምት በማስገባት፣ ከቀጥተኛ እና መደበኛ የውጊያ አውድ በተጨማሪም፣ የሽብርተኛው ሕውሓት እና የሽብር ግብረ አበሮቹን ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች ከሰላማዊ ዜጎች ጋር በመመሳሰል በሕዝብ እና በአገር ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ እና ተጨባጭ የደኅንነት ሥጋት በመረዳት፣ ሽብርተኛው ህውሓት ኢትዮጵያን የማዳከም እና ብሎም የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሠራ እንደሆ በመገንዘብ፣ ከላይ የተገለጹት የአገር ሕልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ እና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል” በማለት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ዓላማ አስረድቷል።

በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆነው ይህ ዐዋጅ፣ መንግሥት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የጸጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ጸጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ መስጠት፣ ዕድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ እና የጦር መሣርያ የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ፣ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ፣ የስዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን እንደሚችል እና ማናቸውም ሕዝብ የመገናኛ እና የሕዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል ተብሏል።

እንዲሁም፣ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ ዐዋጅ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል። ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ሕንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሣሪያዎችን ለመውረስ፣ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት፣ ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ማዘዝ እና ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እና ሥጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ያለ የአካባቢ አመራር መዋቅር በከፊልም ሆነ በሙሉ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካች ይቻላል ተብሏል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በዚህ ወቅት አስፈላጊ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር አስቸኳይ ጊዜ መታወጁ ለችግሩ መንግሥት ትኩረት እንደሰጠው እና የችግሩን አሳሳቢነት ደረጃ ሕዝብ እንዲረዳ እና የበኩሉን እንዲወጣ ዕድል እንደሚከፍት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ታደሰ አክሎግ(ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ህወሓት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ፣ በብሔር አስተዳደር ተደብቆ ሕዝብ ሳይረዳው በድብቅ ዓላማውን ሲያስፈጽም ነበር የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ የፌደራል ሥርዓቱን በጎሳ በማደራጀት ኢትዮጵያን በስልት የማፈራረስ ሥራ መሥራቱን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተጠቀመው ድብቅ አካሄድ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ማስቀጠል ባለመቻሉ፣ ዓላማውን ለማሰፈጸም የትግራይን ሕዝብ ከሕፃን እስከ አዛውንት በጦርነት በማሰለፍ የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን በኃይል ኢትዮጵያን የማፍረስ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

“የህወሓትን ሴራ እና ተንኮል ኢትዮጵያዊያን በልኩ የተረዳነው አይመስልም” የሚሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ በተነሳበት ዓላማ “የሕዝብ ማዕበል” ጦርነት ሲጠቀም፣ በኢትዮጵያዊያን በኩል ነገሩን ለመከላከያ ብቻ በመተው የመዘናጋት ዝንባሌ እንደነበር ጠቁመዋል። የህወሓት ዓላማ ኢትዮጵያን አፍርሶ ታላቋን ትግራይን መመስረት ነው የሚሉት መምህሩ፣ ለ27 ዓመታት ሕጋዊ መምሰልን በስልት የተጠቀመው አካሄድ ሲከሽፍበት መከላከያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

ህወሓት የተጠቀመው የጦርነት ስልት የትግራይን ሕዝብ ከሕፃን እስከ አዛውንት በኃይል የማሰለፍ መሆኑን የጠቆሙት መምህሩ፣ በኢትዮጵያ በኩል በህወሓት ልክ የመደራጀት እና እንደ ሕዝብ ተደራጅቶ ችግሩን የመቀልበስ ችግር እንደነበር ጠቁመዋል። ህወሓት ጥቃት የከፈተባቸው አማራ እና አፋር ክልል በቂ የሚባል ዝግጅት ስላልነበራቸው እና ቡድኑ በተለያየ መንገድ የውጭ ድጋፍ የሚያገኝ በመሆኑ፣ “በሕዝባዊ ማዕበል” የመጣውን የህወሓት ኃይል ለመከላከል መቸገራቸውን አስታውሰዋል።

“አሁን ኢትዮጵያዊያን የነቁ ይመስላል፤ ችግሩ አገራዊ አውድ ይዟል” የሚሉት መምህሩ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በነበረው ጦርነት በሕዝቡ በኩል የሚታየው የመዘናጋት እና ትኩረት ያለመስጠት ችግር አሁን ላይ ተለውጧል ብለዋል። በዚህም የጦርነቱ እየተስፋፋ መምጣት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕዝቡ በኩል ችግሩን በአትኩሮት እንዲመለከተው ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። ህወሓት ጦርነት እያካሄደ ያለበት ዓላማ ንብረት በመዝረፍና በማውደም የሕዝቡን ኢኮኖሚ ለማድቀቅ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ እና ችግሩን እንደ ቀላል ማየት ተገቢ አለመሆኑን አሳስበዋል።

“ወቅቱ የሞት ሽረት ትግል የሚደረግበት ነው” የሚሉት መምህሩ፣ መንግሥት አሁን ላይ ለችግሩ ከሰጠው ትኩረት አንጻር፣ ህወሓት “በአንድ ወቅት የነበረ” ተብሎ የሚጠራ ታሪክ እንጅ ኢትዮጵያ ላይ ሊኖር የማይችል ጅርጅት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ፣ ህወሓት በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልስ በሕዝቡ በኩል የሚታየው ጦርነቱ የሆነ ቦታ እየተካሄደ እንደሆነ እና መከላከያ ብቻውን እንደሚያስቆመው አድርጎ መሳል እና በግዴለሽነት መቀመጥ የተሳሳተ አረዳድ መሆኑን የጠቆሙት መምህሩ፣ ጦርነቱን ለመከላከያ ብቻ ከመተው እያንዳንዱ ኢትየጵጵዊ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

እስካሁን በነበረው ሁኔታ ህወሓት በሚያሰራጨው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ዜጎች አካባቢያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውን የጠቆሙት መምህሩ፣ “እስካሁን በህወሓት የተገፋው ሕዝብ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና በውስጥ አጥፊዎች የተበተነ ሕዝብ ነው” ብለዋል። “መንግሥት ይወጣዋል በሚል ሰበብ እስካሁን የተፈጠረው መዘናጋት መደገም የለበትም” ያሉት መምህሩ፣ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እስካሁን ሕዝቡን በሐሰት ወሬ ሲበትኑ የነበሩ ሠርጎ ገቦችን ለመከታትል እና ለማጥራት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
በዐዋጁ መሠረት አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚያገኙበት ኹኔታ እንደሚኖር የጠቆሙት መምህሩ፣ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በመደበኛ ጊዜ ያሉ መብቶችን የሚገድብ በመሆኑ በሰብዓዊ መብት ሠበብ የሚፈጠሩ ችግሮችን ያስቀራል ብለዋል። ይሁን እንጅ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ውስጥም ቢሆን መዘናጋት እንዳይፈጠር መሥራት እና ዐዋጁን በጠንካራ አመራር መሬት ላይ ማውረድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

“አሁን መቀለድ አይቻልም” ያሉት መምህሩ፣ በማንኛውም ሁኔታ አጠራጣሪ ኹኔታዎችን ኹሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት መከታተል እንዳለበት አመላክተዋል። ከዚህ ቀደም በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የተፈጠረውን የመረጃ ከፍተት እና በሕዝብ ውስጥ ተደብቀው ለህወሓት የሚተባበሩ አካላተን ከመንግሥት መሥሪያ ቤት እስከ ግለሰብ ድረስ መጠበቅ፣ መከታተል እና ጊዜው እስኪያልፍ በልዩ ኹኔታ ማየት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

“ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጠላትን አሳንሶ ማየት አይገባም” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ የጦርነት ሥልቱንና አመራሩን ለፖለቲከኞች መተው ተገቢ አለመሆኑን እና የጦር ሜዳ ሥልቱን ለወታደራዊ ባለሙያዎች መተው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጦርነቱን ለማሸነፍ “ሕዝባዊ ማዕበል” እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን፣ የጦርነት አደረጃጀቱን ማጠናከር እና ወደ ጦር ግንባር የሚዘምተውን ሕዝብ በተቀናጀ አደረጃጀት ማስተሳሰር ይገባል ተብሏል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንፃር በሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች ነገሮች የማበላሸት ዕድል ስለሚኖራቸው፣ ሚዲያዎች የሚያሰራጯቸው መረጃዎች የተመጠኑ፣ ለጠላት የማይጠቅሙ እና ችግሩን ለመቀልበስ አጋዥ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚባ መምህሩ ጠቁመዋል። ዐዋጁ ማንኛውም መገናኛ ብዙኀን እና ጋዜጠኛ ላይ ያስቀመጠው ገደብ “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራልም ሆነ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙኀን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፈቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል” ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com