የእለት ዜና

የክተት ጥሪው ለምን ክልላዊ ሆነ?

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በተከፈተው ጦርነት፣ እስካሁን ድረስ ቡድኑ መጠነ ሠፊ የሆነ ጥፋት እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ጦርነት በህወሓት ከፍተኛ ግፍና በደል ከደረባቸው ሕዝቦች ውስጥ የአማራ እና አፋር ክልል ሕዝቦች ዋነኞቹ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ቡድኑ ሕፃናትና አዛውንቶችን ጨምሮ ዕጽዋትና እንስሳትንም ሳይቀር መግደሉና ማውደሙ የሚዘነጋ አይደለም። አሁንም ቢሆን በየቀኑ የከፋ ጥፋት እየፈጸመ ይገኛል።

በዚህ ወራሪ ኃይል በየጊዜው የሚደርሰውን ግፍና መከራ ለመዋጋት፣ በተለይ መቀሌን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መስፋፋት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ፣ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ በመሆን ከኦሮሚያ፣ ሱማሌ፣ ሲዳማ፣ እና ሌሎችም ክልሎች የተወጣጡ የልዩ ኃይል አባላት፣ እንዲሁም ወጣቶች ወደ ግንባር ዘምተው እየተዋጉ እንደሆነ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ መገለጹም የሚታወስ ነው።

ቢሆንም ግን፣ ይህ ኹሉ ኃይል ተሠልፎ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ የሚደርስው ጥቃት ሊቆም አልቻለም። በአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ እንዲሁም በወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ህወሓት ዘልቆ ገብቶ ንጹኀንን ሲጨፈጭፍ፣ በአፋርም ቀደም ብሎ በጋሊኮማ አካባቢ ንጹኀንን በአሰቃቂ ሁኔታ በከባድ መሣሪያ ሲያጠፋ ቆይቷል። ይህ ኹሉ የሆነው ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ሲሆን፣ ወቅቱም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ እየተዋጉ ነው በሚባልበት ጊዜ ነው።

ህወሓት ያደረሰው ጥፋት የከፋ የሆነው ጦርነቱን ሕዛባዊ ስላደረገው ነው የሚሉ ቢኖሩም፣ የቱንም ያህል ሕዝባዊ ቢያደርገው በቂ አገራዊ ኃይል እያለ፣ ሰሜን ዕዝን መውጋቱ ሳያንስ ጭራሽ ሌላ ጥፋት እንዲሠራ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህ ኹሉ ጥፋት በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ እንዲደርስ ያደረገው በየደረጃው ያሉ የመሪዎች ቸልተኝነት ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ይህም ሕዝቡን በአሉባልታ እንዲሸበር ያደረገና ለጠላትም በር የከፈተ ጉዳይ ሆኖ ታይቷል።

በቅርቡ ደግሞ ወራሪው ኃይል ደሴና ኮምቦልቻ መግባቱን ተከትሎ በነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። ይህን ተከትሎም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥቃቱ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚቆም አይደለም በማለት ጥቅምት 21/2014 አስቸኳይ የክተት ጥሪ ማውጣቱ አይዘነጋም።

ሆኖም ህወሓት የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት ሆኖ ሳለ፣ ጦርነት የከፈተውም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ፣ ይህ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአስቸኳይ ጥሪ ለምን ለአማራ ሕዝብ ብቻ ቀረበ የሚለው ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ነው።

በክልሉ አሁን ላይ የሥራ ቅጥር፣ ዝውውርና የደረጀ ዕድገት ቁሞ በጀቱ ለጦርነት እንደሚውል ነው የተገለጸው። ሌሎች ክልሎችም ይህን ሊፈጽሙና ወራሪውን ኃይል ሊመክቱ እንደሚገባቸው ነው አስተያየት ሲሰነዘር የነበረው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ከውጭ የሚወጋትን ጠላት ያህል የውስጥ ጠላትም ሲጎዳት እንደኖረ የሚታወቅ ነው። ሆኖም እስካሁን ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥሪ አውጀው የጋራ ጠላትን በጋራ ሲፋለሙ እንጂ አንዱ ተዋጊ አንዱ ተመልካች ሲሆኑ የታየበት ጊዜ የለም። በጣሊያን ወረራ ጊዜም በንጉሱ የታወጀው የክተት ዐዋጅ ለመላ ኢትዮጵያውያን የቀረበ ነበር። በሶማሌ ወረራ ጊዜም እንዲሁ አገራቸውን እንዲታደጉ የቀረበው ጥሪ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንደነበር ይነገራል።

የአሁኑ ወራሪ ኃይልም የውጭ ተልዕኮ ተሸክሞ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የውጭ አገር ዜጎችን ሳይቀር ግንባር ላይ አሰልፎ በሚዋጋበት ጊዜ፣ ክልሎች በተናጠል የጠሩት የክተት ጥሪ በብዙዎች ዘንድ በቂ ነው የሚያሰኝ አልሆነም።
አማራ ክልል ሕዝባዊ ማዕበል መነሳት አለበት በሚል የክትት ዐዋጅ ባወጣ በማግስቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የሲዳማና የደቡብ ክልሎችም እንዲሁ ኢትዮጵያን ከወራሪ ቡድኑ ጥቃት ለማዳን ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ባህር ዳር ላይ የነበረው ውይይት ኹሉም ክልሎች ለዘመቻው እንዲዘጋጁ ለማስቻል ነው ሲሉ ተናግረው ነበር። በዚህም ሌሎች ክልሎችም ሥራ መጀመራቸውን ገልጸው፣ በየቀኑ እየተሰናሰለ ሲሄድ፣ የተባለው አገራዊ ጥሪ መስመር እንደሚይዝ ለመንግሥት አመራሮች አብራርተዋል።

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ በብሔራዊ ደረጃ እንዲሆን ለምን አልተደረገም የሚለው ነበር። በክልሎች በኩል ተፈጻሚ እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ የአማራ ክልል ጥሪውን አቅርቦ በፍጥነት ሕዝቡን ማንቀሳቀስ እንደቻለው ሁሉ፣ በሌሎች ክልሎችስ ለምን በአፋጣኝ ማድረግ አልተቻለም በማለት የሚጠይቁም አሉ። ጥሪ ስለማድረጋቸው ያልተሰማ ክልሎች ከመኖራቸው በተጨማሪ፣ ህወሓት በደሴና ኮምቦልቻ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝርፊያና የንጹኀን ጭፍጨፋ እያደረገ ባለበት ሰዓት ጥሪ ከማወጅ በስተቀር፣ እንደ አማራ ክልል ኃይላቸውን ግንባር ያስገቡ ወይም ለማስገባት ጉዞ የጀመሩ ክልሎች ስለመኖራቸው እስካሁን የተሰማ ነገር የለም።

በዋናነት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙዎች ቤት ንብረታቸውን በቀማኛው የህወሓት ቡድን እየተዘረፉ፣ ወጣቶችም ተሰልፈው በግፍ በአደባባይ ተረሽነው ሳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን የምናሸንፍበት የኢትዮጵያ አቅም ገና አልተነካም ሲሉ ለአመራሮች ተናግረዋል። መንግሥት ትልቅ አቅም እንዳለው ከታወቀ፣ አለኝ ከማለት ይልቅ ጥሪውን ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ በማቅርብ እና በተለያዩ አደረጃጀት ወስጥ ያሉ አካላትንም በልዩ ሁኔታ አስተባብሮ ጦርነቱ ሳይጓተት እንዲሁም ብዙ ጥፋት እና እልቂት ሳያስከትል በቀላሉ ማስቆም ይችል ነበር የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የእናት ፓርቲ ሊቀመንበር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) አሁን ላይ ያለው ጦርነት የአማራና የአፋር ብቻ ባለመሆኑ የአማራ ክልልም አስፈላጊ በጀቶችን ሳይቀር ለጦርነት ማዞሩ ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል። እንደእሳቸው ገለጻ፣ ክልሉ ጦርነቱን በበላይነት ቢያጠናቅቅ እንኳን ሙሉ በጀቱን ለጦርነት አውሎና መቆም የሌለባቸውን ተግባራት እንዲቆሙ አድርጎ ኢኮኖሚው ከተናጋ በኋላም ችግር መፈጠሩ አይቀርም የሚል ዕምነት አላቸው። ሆኖም በአፋርና አማራ ክልል ህወሓት የከፈተውን ጦርነት በድል የማጠናቀቅ ኃላፊነት የፌደራል መንግሥቱ ነው፤ የጦርነቱን በጀት ሙሉ በሙሉ መቻል ያለበትም የፌደራል መንግሥቱ መሆኑ አለበት ሲሉ ነው የጠቆሙት። ሌሎች ክልሎች የሚያደርጉት የክተት ጥሪም ለአማራና ለአፋር ክልሎች ዕገዛ ለማድረግ በሚል አይነት መሆን እንደሌለበት ነው ያመላከቱት። አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውጭ ሌሎች ተግባሮቻቸውን ለጊዜው ያዝ አድርገው ከኹለቱ ክልሎች እኩል መፋለም አለባቸው ብለዋል።

ሊቀ መንበሩ የክተት ጥሪው ለምን ክልላዊ ሆነ የሚለው ጥያቄ በፓርቲያቸው ውስጥም ቀደም ብሎ መነሳቱን ጠቅሰው፣ አሁንም ቢሆን የፌደራል መንግሥቱ በበጀትም ሆነ በኃይል የበላይነት ወስዶ ጦርንቱን ማስቆም እንዳለበት አሳስበዋል። የፌደራል መንግሥቱ ጥቅምት 23/2014 የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁን ተከትሎ የክተት ጥሪው አገራዊ ሆኗል ብለው የሚናገሩ መኖራቸውን ተከትሎ፣ ሰይፈ ሥላሴ የክተት ጥሪና የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የተለያዩ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አገሪቱ በጊዜያዊነት የምትመራበትን ሁኔታ የሚገልጽ እንጂ ለጦርነቱ ጥሪ ማቅረብ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።

በአማራና አፋር ክልል እየተደረገ ያለውን ውጊያ ኹለቱ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ዐዋጅ አውጀው እንዲዋጉ በማድረግ ጦርነቱን በክልሎች ብቻ የሚደረግ አድርጎና አሳንሶ ማየት እንደማይገባም አክለው ገልጸዋል።

ለብዙ ጊዜ ሲዘጋጅ የነበረን፣ መድፍና ታንክ የታጠቀን ወራሪ ኃይል የአማራ ክልል ኋላ ቀር መሣሪያ የታጠቁ ገበሬዎች እንዲዋጉት ማድረጉን ቆም ብሎ በማሰብ፣ ጉዳዩም የክልሉ ብቻ ባለመሆኑ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መነጋገር አለበት ይላሉ ሊቀ መንበሩ።
በሌላ በኩል፣ የጋዜጠኝነት ምሩቅ የሆነው ወጣት ታመነ መንግስቴ እንዲሁ ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን ሲገልጽ፣ የአማራና አፋር ሕዝብ በቀጥታ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ በመሆኑ ቀድሞ ወደ ግንባር መግባቱ ተገቢ እንደሆነ አንስቷል። ለተደቀነውን አገራዊ አደጋ የክተት ጥሪው ክልላዊ መሆኑን ባይደግፍም፣ የአማራና የአፋር ሕዝብ ቆራጥ ሆኖ በመፋለምና ድል በማድረግ ራሱን መሸለም፣ ብሎም በአሸናፊነት፣ ጠንካራ ሥነ ልቦናና አንድነት ሕዝቡ ራሱን መገንባት እንደሚያስችለው ታመነ ገልጿል። ለዚህም ከሌላ ዕርዳታ እስኪመጣ በመጠበቅ መዘናጋት እንደማይገባው፣ የራሱን ጠንካራ አደረጃጀት ፈጥሮ በመዋጋት ሠላሙንና ክብሩን ማስጠበቅ እንዳለበት ገልጾ፣ ይህን ማድረጉም ወደፊት ለሚፈጠረው ጠንካራ ሕዝባዊ ሥነ ልቦና እጅግ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ያነሳው።

የሕግ ባለሙያ የሆኑት ካፒታል ክብሬ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ ክልሎች በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52 መሠረት የራሳቸውን የጸጥታ ኃይል የማዋቅርና ደኅንነታቸውን የማስጠበቅ ሥልጣን እንዳላቸው ገልጸዋል። በዚህም የተከፈተባቸውን ወረራ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ከጸጥታ ኃይላቸው በተጨማሪ የሕዝብ እንቅስቃሴም አድርገው መመከት እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈ ኹኔታው በክልሎች የማይፈታ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውጆ የአገርን ደኅንነት ያስጠብቃል። ህወሓት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ለመጣል ጦርነት እንደከፈተ በአመራሮቹ አማካይነት በወሬም በድርጊትም ሲገልጽ አይተናል፤ በዚህም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ጉዳዩ የአንድ ክልል መሆኑ ያበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

የሕግ ባለሙያው አያይዘውም፣ አሁን ላይ የፌደራል መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ያወጀው ጉዳዩ ከክልል አልፎ አገራዊ ፈተና በመሆኑ ነው ይላሉ። በቀጣይም ዐዋጁ የሚመራው በዕዝ ስለሆነ የፌደራል መንግሥቱ ኹሉንም የአገሪቱን ሕዝብ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር በአንድ ሰንሠለት አድርጎ አገራዊ አደጋውን ለመቀልበስ እንደሚሠራና አሁን ላይም በክልሎች ሲደረግ የነበረው የክተት ጥሪ አገራዊ ይሆናል የሚል ዕምነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ሆኖም፣ ወራሪውን ኃይል በጋራም ይሁን በተናጠል በመታገል እስከወዲያኛው እንዳይነሳ አድርጎ መቅበር ይገባል። ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ በአድዋ በዘመናዊ ጦር ተደራጅቶ የመጣውን የጣሊያን ፋሽስት ድል አድርጋ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች አገር ናት። ከጥንት ዘመን ጀምሮም ቢሆን በየዘመኑ ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ የውስጥና የውጭ አካላትን በማንበርከክ ዛሬ የደረሰች አገር መሆኗ በታሪክ ምስክርነት የሚታወቅ ነው።

ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜም ህወሓት ሱዳን ውስጥ ባሰለጠናቸው ወታደሮቹ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ጋር ተደርቦ እንደወጋ ታሪክ ይናገራል። አሁንም ይህ ኃይል ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የተናቀች፣ በውስጥም የተፈረካከስች የሰቆቃ ምድር እንድትሆን እየሠራ በመሆኑ፣ ኹሉም ሕዝቦች አደጋው በተወሰኑ ክልሎች ላይ ብቻ የተጋረጠ እንዳልሆነ በመረዳት በተባበረ ክንድና በቁርጠኝነት የኢትዮጵያን ዘላለማዊ ክብር እና ነጻነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com