የእለት ዜና

በንባብ ባልዳበረ አእምሮ አገርን ማበልጸግ ይቻል ይሆን?

ማርከስ ቱሊስ ሲሴሪዮ የተባለው ጣሊያናዊ ጸሐፊ እና ፈላስፋ፣ “መጻሕፍት የሌለዉ ቤት እና ነፍስ የሌለዉ የሰዉ ፍጥረት አንድ ናቸዉ” ብሏል። ጸሐፊው፣ መጽሐፍ ለሰው ልጅ ከኦክስጅን የማይተናነስ ግልጋሎት እንደሚሰጥ የገለጸበት አባባል ነው።
ማንበብ የተሻለ አስተሳሰበብ ባለቤት ያደርጋል፤ ጠያቂ ያደርጋል፤ ተመራማሪ ያደርጋል፤ የአስተሳሰብን አድማስ ያሰፋል፤ በሥነ ምግባር መታነጽን ያድላል፤ የሌሎችን ስሜት የመጋራትን እና አዛኝ የመሆን ሰብዕና ባለቤት ያደርጋል፤ለችግሮች መፍትሔ ሰጪ ያደርጋል፤ የፈጠራ አቅምን ያሳድጋል፤ የተግባቦት ክህሎትን ያዳብራል፤ በራስ መተማመንን ያሳድጋል፣ ሐሳቦች ኹሉ ትክክል ናቸዉ ከማለት ያድናል፤ ማንም ሐሳቡን እንደ ጥቅምት አህያ ሊጭን ቢፈልግ “እምቢ” የማለት ድፍረትን ይሰጣል።

ማንበብ ለሰዉ ልጅ ከሚሰጣቸዉ ጥቅሞች በጣም ጥቂቶቹ ከላይ የተገለጹት እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜ በምሁራን አንደበት ተነግሯል። ኢትዮጵያ ከደሀ አገራት ዉስጥ የምትመደብ እንደመሆኗ መጠን ፣ ዕድገቷ እውን እንዲሆን ዜጎቿ ከላይ የተገለጹት፣ በንባብ የሚመጣ የሰብዕና ባለቤት ሊሆኑ ግድ ይላል።

ታዲያ በአገራችን ለንባብ የሚሰጠዉ ትኩረት ምን ያክል ነዉ የሚለዉን መጠየቅ ያሻል። በከተማችን አዲስ አበባ ወጣቱ ንባብን ባህሉ እንዲያደርግ የሚገፋፋ ዓውድ አለ ለማለት እንደሚያስቸግር በአደባባይ የሚታየው ሐቅ ምስክር ነው። ባለሀብቱ የመጻሕፍት ቤቶችን ከመገንባት ይልቅ መጠጥ ቤቶችን፣ የማንበቢያ መናፈሻ ከመሥራት ይልቅ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶችን፣ የመጻሕፍት ማንበቢያ ሻይ ቤቶችን ከመክፈት ይልቅ ጭፈራ እና ሺሻ ቤቶችን መክፈት አዋጪ የሥራ መስክ አድርጎት ይስተዋላል።

በከተማችን ከትምህርት ቤቶች እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዉጪ 20 የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ይገኛሉ። እንደ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ የአዲስ አበባ ነዋሪ በ 2008 የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከ 3 ሚሊዮን በላይ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ወደ 5 ሚሊዮን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል። ናይሮቢ ለ 4 ሚሊዮን የከተማዉ ነዋሪ ወደ 60 የሚጠጋ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት እንዳሏት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእኛ ጋር ሲነጻጸር በ3 ዕጥፍ ይበልጣል።

በአዉሮፓ፣ ለምሳሌ ለንደን ውስጥ ለ9 ሚሊዮን የከተማዉ ሕዝብ ወደ 400 ገደማ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ተገንብተዋል። በአሜሪካ ኒዉዮርክ ለ 8 ሚሊዮን ሕዝብ 92 የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አሉ። ከላይ ከተገለጹት ከተሞች በድህነት የመጨረሻዋ አዲስ አበባ ናት። በቤተ መጻሕፍት ቁጥርም የመጨረሻዋ ይህችዉ ከተማ ነች።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል ይገባል፣ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል፣ የተለያዩ ባለድረሻ አካላት፣ መንግሥት፣የዚችን አገር ዕድገት ማየት የሚሹ ከሆነ፣ ቤተ-መጻሕፍትን በገፍ እንዲከፈት ማድረግ አማራጭ የሌለዉ መፍትሔ እንደሆነ ማወቅ ግድ ይላቸዋል።
መንግሥት በመስከረም 24/2014 በዓለ ሲመት ላይ ለሕዝብ ከገባው ቃል አንዱ፣ በመጪዎቹ ተከታታይ ዓመታት፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕዉን ማድረግ ነዉ። በዚህ ሒደት መንግሥት የትዉልድን አእምሮ በንባብ ማበልጸግን እንደዋና የግብ መዳረሻ መሰላል ካላደረገ ከንቱ ልፋት ይሆንበታል። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፣ ቤተ-መጻሕፍት በገፍ ቢከፈት አንባቢ ከሌለ መከፈቱ ብቻ ፋይዳ የለዉም።

በከተማችን ያለ የማንበብ ዝንባሌ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ በርካታ ምሁራን ይናገራሉ። አዲስ ማለዳ በከተማዋ ባሉት የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ተዘዋውራ ለመመልከት ሞክራለች።በጣም ጥቂት፣ በዕድሜ ገፋ ካሉ ስዎች ውጪ አንባቢ አልባ እንደሆኑ ለመታዘብ ችላለች። ወጣቶች በከተማችን ባሉት ዉስን የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት መግባት እና ማንበብ ከማዘዉተር ይልቅ መጠጥ ቤቶች እና ጫት ቤቶች ቀልባቸዉን ይስባቸዋል። በየሻይ ቤቶች የሚታዩ ወጣቶች በእጃቸዉ የሚነበብ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ከመያዝ ይልቅ፣ ሞባይላቸዉ ላይ ማተኮር እንደሚቀላቸው ተስተውሏል።

በተቃራኒው፣ በኢትዮጵያ 1970 ዎቹ ሥነ ፅሁፍ እጅግ ከፍ ያለበት ወርቃማ የኪነ ጥበብ ዘመን ነበር። እንደምሳሌ፣ በሥነ ስዕል የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣በሙዚቃዉ እነ ነዋይ፣ ፀሐዬ፣ አረጋሃኝ እና ሌሎች አርቲስቶች ዘመን የማይሽራቸዉ ሥራዎች ያበረከቱበት፣ በሥነ ጽሑፉ በአሉ ግርማ፣ ብርሀኑ ዘሪሁንን የመሳሰሉ ደራሲዎች ምርጥ ሥራዎቻቸዉን ያቀረቡበት ዘመን ነበር። ከትርጉም ሥራዎችም ፣የነ አርቪንግ ዋላስ፣ ሲድኒ ሼልደን፣ አጋታ ክርስቲ እና ሌሎችም በብዛት ተተርጉመዉ ለገበያ የቀረቡበት ዘመን ነበር 1970 ዎቹ መጨረሻ። በዚህ ወርቃማ የሥነ ጽሁፍ ዘመን ወጣቱ ትዉልድ በርካታ መጻሕፍትን እያነበበ የመወያየት ልምድ አዳብሯል። በቀን 25 ሳንቲም መጻሕፍትን በመከራየት እያነበበ፣ በተቻለ መጠን ሳንቲሙ እንዳይበዛበት ቶሎ ጨርሶ ይመልሳል። በዚህ ምክንያት በሳምንት በርካታ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድ እንዲያዳብሩ አግዟቸዋል።

በየትምህርት ቤቱ የንባብ ክበቦች ጠንካራ መሠረት የነበራቸዉ በመሆኑ፣ ተማሪዎች ማንበብ የዕለት ተዕለት ሥራቸዉ ነበር። ሌላዉ፣ በደርግ ወቅት ከነበረዉ የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም አንጻር የተፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አሸናፊና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ አባላቱን በንባብ ያበለጽጉ እንደነበረ በበርካታ የታሪክ መጻሕፍት ተቀምጧል።

አሁንስ ? እንደ 1970 ዎቹ አይነት አንባቢ ትዉልድ አለ? በዚህ ሐሳብ ዙሪያ በርካታ ጥናቶች ያደረጉትን በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ፣ ሥነ ልሳን እና ተግባቦት መምህር ሩቂያ ሐሰን (ዶ/ር) አዲስ ማለዳ አነጋግራለች።
የስታሊንን የብሔር ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ መጻሕፍት የማንበብ ልምድ እንደነበረ፣ ሌሎችም የማርክሲዝም እና ሌኒኒዝም መጽሐፍ በማንበብ የፊውዳል ሥርዓቱን ለመጣል ትልቅ የንበብ አብዮት እንደነበረ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በእርግጥ ፣ ማንበብን ለፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ መንገድ የመውሰድ አዝማሚያ ይታይ እንደነበረ አልሸሸጉም።

ሩቂያ የመምህራን የማንበብ ልማድን ለማወቅ፣ በዩኒቨርሲቲ እና በሁለተኛ ደረጃ የሚስተምሩትን በናሙናነት በመውሰድ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 ባጠኑት ጥናት መሠረት፣ አብዛኛው መምህራን ከሚያስተምሩት ትምህርት ውጪ የሚያነቧቸው ተጨማሪ መጻሕፍት እንደሌለ ተረድተዋል።አክለውም መምህራን፣ ለተማሪውም ለማኅበረሰቡም እንደምሳሌ እንደመታየታቸው መጠን፣ እጅግ በጣም የማይጠበቅ የጥናት ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር አያይዘውም፣መምህራን ዕውቀታቸው በሚያስተምሩት ትምህርት ላይ ብቻ ስለሚወሰን፣ ለተማሪዎቻቸው ቁንጽል ዕውቀት እንዲያስተላልፉ ሆኗል። ስለዚህ የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ ይገባል በማለት ትውልድ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የዚህ ጥናት ተጨማሪ ውጤት አንደሚያሳየው፣ ከሴት መምህራን በተሻለ ወንዶች፣ፖለቲካ እና ስፖርት ነክ መጽሔትና ጋዜጦችን የማንበብ ዝንባሌ አሳይተዋል።

በቀጣይ፣ በ 2020 የዩኒቨርስቲ መምህራንና ተማሪዎች የማንበብ ልማድ ምን ይመስላል የሚለውን ለማጥናት ሞክረዋል። አሁንም በሚያሳፍር ሁኔታ አስተማሪዎች የሚያስተምሩትን ፣ተማሪዎቹም የሚማሩት ትምህርት ብቻ እንደሚያነቡ የጥናት ውጤቱ እንደሚያሳይ የዩኒቨርስቲ መምህሯ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከሚነበቡት መጻሕፍት ይዘት ውስጥ፣ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦና፣ ታሪክ፣ መዝናኛ፣ ስፖርት፣ ፖለቲካ ፣እና ሌሎችም ጉዳዮች በጥናቱ ውስጥ ተካትተው፣ የመጨረሻ የማይነበቡት ፖለቲካ እና ታሪክ ነክ ጉዳዮች መሆናቸውን የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጣም የሚነበቡት ደግሞ፣ የመዝናኛ እና የስፖርት ጽሑፎች እንደሆኑ ጥናቱ እንደሚያመለክት ጠቁመዋል።

ሥጋታቸውን ሲገልጹም፣ የአገር ብልጽግና እውን የሚሆነው ሳይንሳዊ ፣ጥናታዊ ፣ቴክኖሎጂ እና አገራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጽሑፎችን በማንበብ እንደሆነ ነው። አገራችን በዕድገት ከፍ እንድትል ልጆቿ በንባብ አእምሯቸውን በማስፋት፣ በምክንያት እና በአመክኒዮ አዲስ ሐሳቦችን እንዲቀበሉ ማንበብ ትልቅ አስተዋጸዖ እንዳለው አስረድተዋል።

መንግሥትም ለንባብ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት “አብርሆት” የተባለ ግዙፍ ቤተ-መጻሕፍት በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከመገንባቱ ጎን ለጎን ትውልዱ አንባቢ እንዲሆን ሳቢ እና ምቹ ማድረግ፣ መጻሕፍቱ ዲጂታል እንዲሆኑም ማስቻል፣ ኤሌክትሮኒክ መጻሕፍትን በብዛት ማቅረብ ፣ የመጻሕፍት ዓውደ-ርዕዮችን እና ዳሰሳዎችን በብዛት ማዘጋጀት፣ መንግሥት የመጻሕፍት ሻጮች ለአንባቢው በቅናሽ እንዲሸጡ ልዩ ድጎማ ማድረግ ቢችል ትውልድ የማንበብ ልምድን እንዲያዳብር ያግዘዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ ፣ሔነሪ ዋርድ ቢቸር የተባለዉ ጸሐፊ መጻሕፍት ለቤት ዕቃ ሟሟያነት አልተፈጠሩም፤ ይሁን እንጂ ከሳሎን ቤት ዕቃ በተሻለ ቤትን ዉብ የማድረግ ልዩ ኃይል አላቸዉ እንዳለው፣ ከተማን በንባብ ማበርታት ከመንግሥት የሚጠበቅ ትልቁ ጉዳይ እንደሆነ ሩቅያ ሐሰን (ዶ/ር)በአጽንዖት ገልጸዋል። አክለውም፣ በዕድገት ቁንጮ የሆኑ አገራት ከማንበብ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው ገልጸው፣ ኢትዮጵያም ካደጉት አገራት ተርታ ባትሰለፍ እንኳን ዜጎቿ ከድህነት ማጥ ውስጥ እንዲወጡ የማንበብ ልማድን ማዳበር ዋነኛው መፍትሔ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

አዲስ ማለዳ ፣ በሕዝቡ የንባብ ባህል ዙሪያ የመጻሕፍት ሻጩን ሰይፈዲን ሙሳ አስተያየት ጠይቃለች። እንደ ሰይፈዲን አስተያየት ፣ከ 5 ዓመት በፊት እና በኋላ የነበረው የአንባቢ ቁጥር ሲገልጽ፣ ከ 5 ዓመት ወዲህ የመጻሕፍት ሽያጭ እያደገ መምጣቱን ታዝቧል። በፊት አንድ መጽሐፍ 2000 ቅጂ ታትሞ እንደገና ለመታተም ኹለት እና ሦስት ዓመት መቆየት ግድ ይለው እንደነበር ተናግሯል። አሁን ላይ ግን በኹለት እና ሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ድጋሚ 2000 ይታተማል በማለት የመጽሐፍ ሽያጭ ልምድ ከበፊቱ አንጻር እየተሻሻለ እንደመጣ ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል። ይሁን እንጂ እንደ ሰይፈዲን አባባል ከመቶ ሚሊየን የሕዝብ ቁጥር አንጻር፣ እጅግ አነስተኛ የማንበብ ባህል እንዳለ አልሸሽገም። አክሎም፣ከሚሸጡት መጻሕፍት ውስጥ፣ ከትምህርት አጋዥ ቀጥሎ፣ የልቦለድና ሥነ ልቦና መጻሕፍት ብዛቱን እንደሚወስዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

መጻሕፍትን ማንበብ የሰው ልጆችን አእምሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ከማሳደጉም ባሻገር፣ በማንበብ የበለጸገ አእምሮ አገርን የማሳደግ ትልቅ አቅም እንዳለው በርካቶች ይስማማሉ። የተለያዩ ሕንጻዎች፣ ሻይ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የንባብን ልማድ የሚያነሳሳ ዓውድ ሊኖራቸው ግድ ይላቸዋል። አንዳንድ ፑል ቤቶች ግድግዳቸው ላይ “ማንበብ ክልክል ነው” ብለው መለጠፋቸውን አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በቃኘችው ታዝባለች። በተቃራኒው፣ ያደጉት አገራት በኹሉም የአገልግሎት ተቋማት ትራንስፖርትን ጨምሮ፣ “የማንበቢያ ቦታ” ብለው በመጻፍ ሕዝቡ ባለማንበብ የሚያጠፉው ሽርፍራፊ ሰዓት እንዳይኖር በተዘዋዋሪ ያስገድዱታል። ኢትየጵያም፣በዕድገት ጎዳና እንድትራመድ፣ያደጉ አገራትን የማንበብ ተሞክሮ በመውሰድ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ይኖርባታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com