የእለት ዜና

የጨቅላ ሕፃናት ወተት እና ማሟያ ምግቦች ንግድን የሚቆጣጠር መመሪያ ተግባራዊ ሆነ

የኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን አስገዳጅ የሆነ የጨቅላ ሕፃናት ወተት እና አልሚ ወይም ማሟያ ምግቦች ንግድ የሚቆጣጠር እና ሥርዓት የሚያሲዝ መመሪያ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ተፈጻሚ ማደረግ መጀመሩን አስታውቋል።
የሕፃናት ምግብ ቁጥጥር የሚል ሥያሜ የተሰጠው መመሪያው፣ አግባብ ባልሆነ መንገድ ጨቅላ ሕፃናትን በመመገብ ሒደት ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለመገደብ፣ እንዲሁም ለከባድ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ ብሎም የእናት ጡት ወተት ማጥባትን ለማበረታታት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

መመሪያው ማንኛውም አምራች ወይም አስመጪ ምርቱን ወደ ገበያ ከማስገባቱ በፊት ለባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት፣ የምርቱን መልካም የአመራረት ሒደት እና ምርቱ በተመረተበት አገር በነጻነት የሚሸጥ መሆኑን የሚገልጽ እና ሌሎችም አስፈላጊ የጥራት ምስክር ወረቀቶችን ሊያቀርብ እንደሚገባ ይደነግጋል።

በተጨማሪም፣ መመሪያው የእናት ጡት ማጥባት ተቀዳሚ እና ለሕፃናት ጤና ጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍ ጠቃሚ ምክር በሚል ርዕስ ሥር በጉልህ በምርቱ ማሸጊያ ላይ ጽፎ ማስቀመጥን ግዴታ አድርጎ ያስቀምጣል።
መመሪያው በዋናነት በማንኛውንም ዓይነት ማስታወቂያ የሕፃናትን ምግብንና የመመገቢያ ምርትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማስተዋወቅ፣ ፕሮሞሽን መሥራትና ስፖንሰር ሥራዎችን ማከናወን ክልክል መሆኑን ይደነግጋል።

መመሪያው፤ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔት ወይም በማንኛውም መንገድ የጨቅላ ሕፃናት ምግብ ንግድ ላይ የተሠማራ በድምጽ፣ በምስል ወይም በፊልሞች፣ በኅትመት ውጤቶች ስለ ጨቅላ ሕፃናት ምግብ (ፎርሙላ) በጽሑፍ፣ በገለጻ፣ ወይም የጨቅላ ሕፃናት ምግብን (ፎርሙላ) በማሳየት መልዕክት ማስተላለፍ፣ ወይም ልዩ ገጽታ በችርቻሮ መሸጫ መደብር ወይም በሥራ ቦታ ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ ማሳየት፣ በጨቅላ ሕፃናት ምግብ ምርት ላይ የዋጋ ቅናሽ መኖሩን ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም በነጻ ሕፃናት ምግብን መስጠት እና ሌሎችንም ጨምሮ እንደማስተዋወቂያነት ነጋዴው ሊገለገልበት ይችላል ተብሎ የታመነ ተግባርን በሙሉ ይከለክላል።

በተጨማሪም መመሪያው፣ ማንኛውም የጨቅላ ሕፃናት ወተት አምራች፣ አስመጪ፣ አከፋፋይ፣ ወይም ወኪል የጨቅላ ሕፃናት ወተትን በዕርዳታ መልክ ለማንኛውም ሰው መስጠት አይችልም ሲል የሚደነግግ ቢሆንም፣ እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ካገኘ እና ጨቅላው ሕፃን የተጎዳ ከሆነ መስጠትን ይፈቅዳል። ሆኖም ልገሳውን ይፋ ማድረግ መመሪያው ይከለክላል።

መመሪያው የተዘጋጀበት ዓላማ የልጆችን ጤንነት እና በሽታ የመከላከል አቅም ለማዳበር የሚያስችል እና የእናት ጡት ወተትን መተካት የሚችል አቅም እንዳላቸው በሚመስል መልኩ የሚሠሩ ማስታወቂያዎችን ለማስቆም ታስቦ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከባለሥልጠኑ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ቅዱስ ሳሙኤል በጀምላ ንግድ ጥናት እና ማማከር መስክ ከስምንት ዓመት በላይ የቆዩ የገበያ (ማርኬቲንግ) ባለሙያ ሲሆኑ፣ መመሪያው ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነ እንደሚሰማቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“ማስታወቂያ መከልከል ባህል እየሆነ የመጣ ይመስላል” የሚሉት ቅዱስ፣ ለሕፃናት ምግብ እና ወተት እጅግ ጥንቃቄ መደረግ ቢኖርበትም፣ የማስታወቂያ ዋናው ዓላማ ሕብረተሰቡን ዕውቀት ማስጨበጥ ቢሆንም፣ መመሪያው የተለያዩ አስገዳጀ ነጥቦችን ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
ለምሳሌ፣ ያለው ንጥረ ነገር በባለሥልጣኑ ከተረጋገጠ በዝርዝር ማስቀመጥ፣ የጎንዮሽ ጉዳት ካለውም በተመሳሳይ መልኩ እንዲቀመጥ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ይህ መመሪያ በተለያዩ ሁኔታዎች ምክንያት ማጥባት የማይችሉ እናቶችን መረጃ የማግኘት መብት የሚከለክል ሆኖ አግንቼዋለሁ ሲሉ ቅዱስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ንጹህ ወርቅአፈስ የማኅበረብ ጤና ባለሙያ እና ከአስር ዓመት በላይ በማኅበረሰብ ጤና ላይ በተለይም በእናቶች እና በሕፃናት ጤና ጥበቃ ላይ የሠሩ ሲሆን፣ “ጥሩ ጀማሮ ነው፣ ነገር ግን ማስታወቂያዎችን ከመከልከል በተለየ ሊሠራባቸው እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ነበሩ፤ ለምሳሌ በኮንትሮባንድ ገብተው ገበያ ላይ የዋሉ ምርቶቸን ማጽዳት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነበር” ብለዋል።

ለእናት ጡት ወተት የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን የሚገልጹት ንጹህ፣ እስከ አራት ዓመት ከግማሽ ድረስ ሕፃናትን ጡት ማጥባት ይመከራል ብለዋል። አያይዘውም፣ ይህ መመሪያ ማስታወቂያ ሲከለክል በምትኩ ጡት ማጥባትን የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎች እንዲሠሩ ጤና ሚኒስቴር በስፋት መሥራት መቻል አለበት ሲሉ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!