የእለት ዜና

ሪፖርቶች ላልሠሟቸው ድምጾችም ድምጽ እንሁን!

ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመት ሞልተው ሳምንት ለተሻገሩ ቀናት፣ በየዕለቱ አዲስ ሞቶችን፣ ሰቆቃና ጥቃቶችን፣ ኪሳራና ዕልቂቶችን ስታስተናግድ ቆይታለች። በ‹ሕግ ማስከበር ዘመቻ› የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደለየለት ጦርነት ከተሻገረ ወዲህ፣ ንጹኃን ዜጎች ኹሉንም ዓይነት መከራና ስቃይ እንዲሸከሙ ሆኗል። ሕፃናትና ሴቶችም ለረሃብ፣ ስደትና ጾታዊ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ በዐይን ምስክርነት ተገኝተናል።

ኅዳር 1/2014 በርካታ መገናኛ ብዙኀን ማልደው ሲቀባበሉት ከነበረው ጉዳይ መካከል ቀዳሚው ‹አምነስቲ ኢንተርናሽናል› ያወጣው ዘገባ ነበር። ይህም የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ነፋስ መውጫ ከተማ ላይ ከፈጸሙት ጥቃት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር መፈጸማቸውን ዘገባው ይጠቅሳል። አምነስቲ ‹‹ካነጋገርኳቸው መካከል 16 ሴቶች በህወሓት አማጽያን የአስገድዶ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ ከእነዚህም 14ቱ በቡድን የተደፈሩ ናቸው›› ብሏል።

እንደ ዘገባው ይህ ድርጊት የተፈጸመው ከነሐሴ 6 እስከ 15/2013 ባሉ ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ነው። በአንጻሩ በተመሳሳይ ጊዜ በተመሳሳይ አካባቢ ከ70 በላይ ሴቶች ጥቃት ተፈጽሞብናል ብለው ማመልከታቸውን የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች አስታውቀዋል።
እርግጥ ነው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጦርነትና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃቶች መድረሳቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ዓለምም ይህን አስቀያሚ እውነት እውቅና ሰጥታ ከ‹ጦርነት አቁሙ› ጥሪ በተጓዳኝ ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሣሪያ ውሏል ወይም አልዋለም የሚለው ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጋለች።

በተለያዩ አገራት የተፈጠሩ የጦርነትና የግጭት ክስተቶችን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2002 ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጾታዊ ጥቃት የጦርነት፣ እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው ብሎ አወጆ ነበር። ይህም የሆነው ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች ጾታዊ ጥቃቶች በተለይ አስገድዶ መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገሉ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው። የተባበሩት መንግሥታትም በ2008 መደበኛ በሆነ መንገድ አስገድዶ መድፈር እንደ ‹ጦር መሣሪያ› እየዋለ እንደሆነ አስታወቀ።

የተለያዩ ምሁራንና ተመራማሪዎች ይህ ለምን ሆነ ብለው ጠይቀዋል። የጠላት ጦር ከተባለ ሠራዊት መካከል ምርኮኛ እንኳ በክብር እንዲያዝ በሚታመንበት ዓውድ ላይ ስለምን ንጹኃን የሆኑ ዜጎች ላይ ይልቁንም ‹ታግለው የሚጥሉበት አቅም የላቸውም› ተብለው በሚታሰቡ ሴቶች ላይ ለምን እንዲህ ያለ ጥቃት ይፈጸማል ብለው አሰላስለዋል።

ለዚህ ጥያቄ የተደረሰበት አንድ ‹ምሁራዊ› መልስ፣ ‹‹አስገድዶ መድፈር የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ አንድን ተጠቂ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብና ማኅበረሰብን ሊከፋፍል የሚችል ኃይል ይሰጣልና ነው›› የሚል ነው። ተዋጊዎች ጠላታችን ባሉት ወገን ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃትን የሚፈጽሙት እንደተባለው የጥቃቱ ተጽዕኖ አንዲት ሴት ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ እንዲሁም አገር ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በሚገባ የተረዱ በመሆናቸው ነው።

እንዲህ ያለ ጥቃት ጦርነት ካበቃም በኋላ አብሮ ዘልቆ የሚቀጥል ነው። ያልተፈለገ እርግዝና፣ በግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና የመሳሰሉት ከጦርነት በኋላ በሚኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ ብዙ ቀውሶችን ይፈጥራሉ።

አዎን! እንደ ቀላል 16 ወይም 70 ተብለው የተቀመጡ ቁጥሮች ቤተሰብንና ማኅበረሰብን የመከፋፈል አቅም አላቸው። ይህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ ከሚደርስ መሸማቀቅና ማኅበራዊ መገለል የሚነሳ ነው። ከጥቃት አድራሽ በላይ ተጠቂዎች ተወቃሽ በሚሆኑበት (Victim Blaming) ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያለ ጥቃትን የተከተለ ማኅበረሰባዊ ግብረ መልስ ደግሞ እንግዳ አይደለም። ያም ብቻ አይደለም፣ እነዚህ ሴቶች በደረሰባቸው የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ጽንስ ሊፈጠር ይችላል። ቀጥሎስ?

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ጦርነት የተቀሰቀሰ ሰሞን በተመሳሳይ የሴቶች ጥቃት ጉዳይ በስፋት ሲነሳ ነበር። በሴቶች ሥም የተመሠረቱ ማኅበራትም በተወሰነ መጠን ጩኸቱን ተከትለው ‹ይመለከተናል!› ሲሉ ስንሰማ ነበር። ከዛ በኋላም ጥቃቶች አልቆሙም፣ ማኅበራት ግን የነበረ ድምጻቸው እያደር ቀንሷል። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ‹ሴቶች ይሳተፉ! ሴቶች ይመረጡ! ሴቶች ይምረጡ!› ከሚለው ድምጽ ሩቡ እንኳ አሁን ላይ አይሰማም።

በጦርነት መካከል ‹አክቲቪስት› መሆን ትርጉም የሌለው የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም። አክቲቪስት ሆነው እሳቱ ላይ ቤንዚን የሚያፈሱ ግን እንደዛ ብለው አያስቡም። ልክ እንደዛው ኹሉ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ገብቶ ሴቶችን ማዳንና ማትረፍ፣ ጥፋት አድራሾችን ለይቶ ለዚህ ጥፋታቸው ተገቢውን ቅጣት መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ድርጊቱን ማውገዝ፣ (አለን የሚሉት በሚፈልጉት ጊዜና ኹኔታ ብቻ ቢሆንም) ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነቱን ማሳየት፣ በጥቃት ውስጥ ያለፉ ሴቶችን ማጽናናትና የተሸከሙትን ተደራራቢ መከራ ለአፍታ ተሸክሞ፣ በ‹አይዞኝ!› ቃል መደገፍ ያሻል።

ድምጹ ጆሮ የተሰጠው፣ የደረሰበትን በደል ሲናገር ጩኸቱ ሰሚ ያገኘለት ደግሞ የታደለ ነው! አምነሲቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ከገለጻቸው፣ ከወራት በፊት የወጡ ዘገባዎች ከጠቀሷቸው፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ካሳወቃቸው በላይ ብዙ ሴቶች በጦርነትና ችግር፣ መፈናቀልና ረሃብ ላይ ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ይህ ከቶውንም ‹ከዛ ወገን ያሉ ሴቶች፣ ከዚህ ወገን የሚገኙ ሴቶች› በሚል ሚዛን የሚሰላ፣ ‹የእነ እገሌ፣ የእነ እገሌን ሴቶች ደፈሩ› በሚል መስፈሪያ የሚሰፈር አይደለም። ንጹኃን ዜጎች የትም ሆነ የት የሚደርስባቸው ጥቃትና መከራ ኹሉንም ያሳስባል፤ የኹሉም ጉዳይም ነው።
ጭንቀት በሞላው ጓዳ ታፍነው የቀሩ፣ አቤት ባይ ያጡ፣ ‹ምን ለውጥ ይመጣል!› ብለው ድምጻቸውን ላጠፉና ሪፖርቱ ላልተመለከታቸው እህቶቻችንም ድምጽ እንሁን። በአዲስ ማለዳ እምነት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በቁጥር የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም፤ ወይም አምነስቲ በዘጠኝ ቀናት ውስጥ ደርሰዋል ካላቸው ጥቃቶች አንጻር በጦርነቱ የቆይታ ጊዜ የተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥር አስደንጋጭ ሊሆኝ መቻሉ አያጠራጥርም።

የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ነገሩን እንዲያወግዙና ማገዝ በሚቻልበት ኹሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ አዲስ ማለዳ አደራ ትላለች። በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ላሉ፣ በጦርነቱ ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸውና የመድኃኒት ዕጥረት በገጠማቸው አካባቢዎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ድጋፎች እንዲደርሱ ማድረግ የግድ ይላል።

መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም በተለይ የጥቃት ሰለባ የሆኑ እንዲሁም ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ሴቶች ትኩረት ይስጡ! ኹሉንም መንግሥት ይሥራው ማለት ስለማይቻል፣ ቢያንስ ከእነዚህ ሴቶች መካከል በመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ለሚገኙት የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንዲሰጥ ማኅበራት የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ።

ሴቶችን በዋናነት አነሳን እንጂ ተከራካሪና ተሟጋች የሌላቸው ሕፃናት ጉዳይም በእጅጉ አሳሳቢ ነው። በጦርነት አካባቢ ያሉ ብቻ ሳይሆን በርቀት ሆነው የጦርነቱን ነገር የሚከታተሉትም የሚደርስባቸው የአእምሮና የልቦና መታወክ ቀላል አይሆንም። እናም እንዲህ ላሉ፣ በሪፖርቶች ጎልተው ላልተጠቀሱ፣ ድምጻቸው ላልተሰማ ኹሉ ድምጽ እንሁን። የተሻለ መልካም ቀን እስኪመጣ ተያይዞና ተደጋግፎ፣ ተረዳድቶና ተግባብቶ ማለፍ ያሻል። በእርግጥ ይህ አልፎ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ አዲስ ማለዳ ተስፋ ታደርጋለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com