የእለት ዜና

በምሥራቅ ወለጋ ኦነግ ሸኔ የጦር ካምፕ መሥርቶ ወጣቶችን እያሠለጠነ ነው ተባለ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን የጦር ካምፕ መስርቶ ወጣቶችን እያሠለጠነ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቡድኑ የጦር ሰፈር መስርቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳ መካከል “ቆቆፌ” ተብሎ በሚጠራ አነስተኛ የገጠር ከተማ ውስጥ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገረዋል። ሠልጣኞቹ በዘጠኝ ባጃጅ እና በአምስት ‹ሲኖ ትራክ› መኪኖች ተጭነው ሲጓጓዙ የአካባቢው ነዋሪዎች መመልከታቸውን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ቆቆፌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎችን እና ትምህርት ቤቶችን ለስልጠና ቦታ እየተጠቀሙበት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አንስተው፣ በጦር ማሰልጠኛዎቹ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ወጣቶች እየሰለጠኑ መታየታቸውን ጠቁመዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ጥቅምት 25/2014 አንድ የአማርኛ ተናጋሪ ግለሰብ በነዚሁ ታጣቂዎች ተገድሎ አስከሬኑ መንገድ ላይ ሲጎተት ማየታቸውን ተናግረዋል። በተለይ ጥቃቱ በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ የገለጹ ሲሆን፣ አክለውም ታጣቂ ቡድኑን የሚደግፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰንጋ እያረዱ ሲቀልቧቸው መመልከታቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የወረዳው እና የቀበሌው አመራሮች፣ “እኛም ጥቃት ይፈጸምብናል” በሚል ሥጋት ከታጣቂው ቡድን ጋር ስምምነት በመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። የመንግሥት ታጣቂዎች ኦነግ ሸኔ በአካባቢው በስፋት እንደሚንቀሳቀስ መረጃው ቢኖራቸውም፤ ከወረዳው ወደ ቀበሌ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የጸጥታ ኃይሎች መግባት እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም፣ በነዚሁ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ነቀምት እና ከነቀምት አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የሕክምና እና ሌሎች የመንግሥት አገልግሎቶች ማግኘት አለመቻላቸውን ተናገረዋል። በተጨማሪም ከነቀምት እስከ ቡሬ ያለው መንገድ ከተዘጋ ሰባት ወር ስላለፈው፣ ከተደቀነባቸው የሞት አደጋ ሥጋት ማምለጥ እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በኪረሙ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚኖሩ ነፍሰ ጡር እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑንም ገልጸዋል። እስካሁን በኪረሙ ወረዳ ዘጠኝ ነፍሰጡር እናቶች በሕክምና ዕጦት ደም ፈሷቸው ሕይወታቸው ማለፉን የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ታጣቂው ቡድን እየፈጸመ ያለውን ጥቃት በመሸሽ በሐሮ አዲስ ዓለም ከተማ የተጠለሉ ከ40 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በችግር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት እነዚህ ተፈናቃዮች፣ እስከአሁን ከመንግስት ድጋፍ እያገኙ አለመሆናቸውን እና ለከፍተኛ እንግልት፣ ረሀብ እና የሥነልቦና ውድቀት መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ የነዋሪዎቹን ጥያቄ ይዛ ለምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ አስተዳዳሪ በላይ ደሳለኝ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም፣ስልካቸውን በመዝጋታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።
የኪረሙ ወረዳ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሁንድሬ በየነን ስለ ነዋሪዎቹ ቅሬታ ለማነጋገር አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ብትደውልላቸውም፣ እሳቸውም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።

በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በስፋት እተንቀሳቀሰ ያለው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚቆጣጠራቸውን አካበቢዎች እያሰፋ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከክልሉ ለማጽዳት ጥረት እያደረገ መሆኑን መገለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!