የእለት ዜና

የጦርነቱ ፍፃሜ ወደ ድርድር ያመራ ይሆን?

በኢትዮጵያ አሁን እየተከካሄደ ባለው ጦርነት ህወሓት እያደረሰ ያለው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ ፍጻሜውን ለመተንበይ አዳጋች ሆኗል። ህወሓት በትግራይ ክልል መቀመጫውን ባደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24/2013 ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ የተጀመረው ጦርነት እስካሁን በርካቶችን ለሞት፣ መፈናቀል፣ ለንብርት ውድመትና ዘረፋ እንዲሁም ለሥነ-ልቦና ቀውስ ዳርጓል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከገጠማት ችግር መውጣት የምትችልለው በምን መንግድ መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ አንዳንዶች ዘረፈ ብዙ ችግር እያከተለ የሚገኘውን ጦርነት ለማስቆም ፖለቲካዊ መፍተሔ እና ድርደር ያሻል ይላሉ።
አንዳንዶች ደግሞ አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ከሚንቀሳቀሰው እና በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ደርጅት ጋር መደራደር እንደማይቻል በመግለጽ ጦርነቱን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከሰሞኑ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ህወሓትና ፌዴራል መንግሥቱ በመካከላቸው ያለው ችግር በውይይት ሊፈታ የሚችል እንደሆነና ኹለቱ ኃይሎች ፖለቲካዊ መፍትሔን እንደሚፈልጉ በግለሰብ ደረጃ መስማማታቸውንም መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት ኃይሎች ለድርድር ፍላጎት ያላቸው የሚያስመስል ፍንጭ መስጠታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የሰሞኑን አጀንዳ ሆኗል። የጦርነቱ ፍፃሜ ወደ ድርድር ያመራ ይሆን? የሚለውን ጉዳይ የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ በጉዳዩ ላይ የወጡ መረጃዎች በማጣቀስ እና የፖለቲካ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ በ2010 ከተደረገው ለውጥ ማግስት ጀምሮ በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የነበረው በቃላት መወራወር ወደ ግልጽ ጦርነት አምርቶ፣ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አሁንም ድረስ የጦርነት ቀጠና ሆኖ መቀጠሉ ይታወቃል። ህወሓት በትግራይ ክልል መቀመጫውን ባደረገው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24/2013 በወሰደው ጥቃት የተነሳ “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሚል ጦርነቱ በአጭር እንዲቋጭ እና ከህወሓት አመራሮችም የተወሰኑት እጅ እንዲሰጡ፣ የቀሩትም እንዲገደሉና እና ሌሎች ደግሞ እንዲታደኑ ተደርጓል። በሂደቱም በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ክልሉን የማረጋጋትና የማስተዳደር ሥራ እየሠራ ስለነበር፣ ብዙዎች ጦርነቱ በፍጥነት የሚጠናቀቅ እና ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ወደ ነበረበት ሠላም የሚመለስ መስሏቸው ነበር።

ሆኖም ግን ለስምንት ወር ገደማ ክልሉ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሥር ሆኖ የህወሓት ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ የነበረ ቢሆንም፣ ነገሮች እንደታሰቡት ሳይሆኑ ቀርተው ፌደራል መንግሥቱ ሰኔ 21/2013 የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ሲወጣ ህወሓት እንደገና ክልሉን ለመቆጣጠር ችሏል።

ማዕከላዊ መንግሥቱ የተናጥል ተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገው ለክልሉ አርሶ አደሮች የዘር ወቅት በመሆኑ ነው ቢልም፣ ዳግም ክልሉን የተቆጣጠረው ህወሓት ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደማይቀበለው በመግለጽ፣ ከተቆጣጠረው የትግራይ ክልል ውጭ ጦርነት መክፈት ጀምሯል። በዚህም አስቀድሞ በበረሃ እያለ በአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ ሲል ስለነበር፣ ይህን እሳቤውን ለማስፈጸም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ማድረሱን ቀጠለ። በተመሳሳይ መልኩ በአፋር ክልልም እንዲሁ ጥቃት መሰንዘርና ንጹኃንን መግደል፣ ማፈናቀል ብሎም ሥጋት መፍጠሩ ይታወቃል።

ህወሓት ጥቅምት 24/2013 በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ወንጀለኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከታትሎ እንደሚይዛቸውና ለሕግ እንደሚያቀርባቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል በመግባቱና የሕግ ማስከበር ዘመቻውም በብዙዎች ዘንድ የተሳካ የሚመስል ስለነበር፣ ቡድኑ ከጫካ ተመልሶ ክልሉን ሲቆጣጠር እንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ የጠየቀ በርካታ ሰው ነበር።

እየቆየ ግን ህወሓት በንጹኃን ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት እጅግ አሰቃቂና ታይቶ የማይታውቅ እየሆነ ይሄድ ጀመር። በወረራ የሚይዛቸው ቦታዎችንም እያሰፋ ዘረፋና ግድያውንም አጠናክሮ እንደቀጠለበት ይነገር ነበር። ይህን ተከትሎም መንግሥት በዚያን ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ነኝ እያለ፣ የመከላከል ሥራ ብቻ እየሠራ ህወሓትን እንዲጠናከር አድርጎታል የሚል ወቀሳ ብዙዎች ሰንዝረውበታል።

በመቀጠልም፣ በአጭር ቀን ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበው ጦርነት ከዓመት በላይ ማስቆጠሩና በዚህም ሳቢያ ከሞቱት ውጭ ብዙዎች ለከፋ ስቃይና እንግልት መዳረጋቸው አልቀረም።
ከሰሞኑ ደግሞ ህወሓት ወረራውን እያስፋፋ ባለበት ወቅት፣ ‹‹መንግሥት ከህወሓት ጋር ሊደራደር ይችል ይሆን?›› የሚል እሳቤ የሰሞኑ ትኩረት የሳበ አጀንዳ ሆኖ በብዙዎች ዘንድ ሲንሸራሸር ተስተውሏል።

ቀድሞውንም በብዙ አገሮች ተኩስ አቁም እንዲደረግና ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ሲጠየቅ መክረሙ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት በሠጠው ማብራሪያ ላይ፣ “ከህወሓት ጋር ለመደራደር ቢያንስ ንጹኃንን ከሚያሰቃይበት የአፋርና አማራ ክልል መውጣት አለበት” ማለቱን ተከትሎ በበርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚነሳው መሠረታዊ ሐሳብ፣ “አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ከሚንቀሳቀስ ቡድን ጋር በዕውነቱ ቁጭ ብሎ መደራደር ይቻላል ወይ?” የሚለው ነው።

በዚሁ ሰሞን ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ ማምራታቸውና ከህወሓት ሊቀመንበር ጋር ተገናኝተው ውጤታማ ያሉትን ውይይት ማካሄዳቸውን መናገራቸው ደግሞ፣ መንግሥት ድርደር ሊያደርግ ይችላል የሚል ሐሳባቸውን እንደማጠናከሪያ አድርገው የተጠቀሙበት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አሉ።

ኦባሳንጆ ከመቀሌ ከተመለሱ በኋላ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የፌዴራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማደራደር የሚያደርጉትን ጥረት በአወንታዊ መልኩ ቡድኑ እንደተቀበለው መግለጻቸው ይታወሳል። አያይዘውም፣ ህወሓትና ፌደራል መንግሥቱ በመካከላቸው ያለው ችግር ፖለቲካዊ እንደሆነ እና በውይይት ሊፈታ የሚችል ፖለቲካዊ መፍትሔን እንደሚፈልጉ በግለሰብ ደረጃ መስማማታቸውንም አሳወቀዋል።

ህወሓትም ኦባሳንጆ ከመቀሌ ከተመለሱ በኋላ፣ ፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ላይ የጣለውን ዕቀባ ካነሳ እና የተቋረጡ አገልግሎቶች ከተመለሱ፣ የተኩስ አቁም ለማድረግ እና ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን በቃል አቃባዩ በኩል አስታወቋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለሽምግልና ወደ መቀሌ የተላኩ እናቶችን፣ ታዋቂ ሰዎችን እና የአገር ሽማግሌዎች ምልጃ አሽቀንጥሮ የጣለው የህወሓት ቡድን፣ ውጊያው ከተጀመረ ዓመት በኋላ ‹‹ውጊያው ተፈልጎ ሳይሆን በሠላም ይፈታ ብለን በተደጋጋሚ ጠይቀን የኃይል አምላኪዎች ግን ወጊያውን ለማስቀጠል ስለወሰኑ፣ ያለን አማራጭ ጠላቶቻችንን በኃይል መደምሰስ ስለሆነ ነው ወደ ውጊያው የገባነው›› ሲል ተደምጧል። ቡድኑ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥሪያለሁ ካለበት ሰሞን ትንሽ ቀድም ብሎም፣ “ፌዴራል መንግሥቱ የወንጀለኞች ስብስብ ነው፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፣ ከዚህ በኋላ በኃይል እንጂ በድርድር የሚፈታ ነገር የለም” ሲል ነበር።

አሁን ላይ ፍላጎቱ እንዳሰበው አልሆንለት ሲልና የኃይል ብልጫ የሚወሰድበት መስሎ ሲሰማው፣ ማዕቀቡ ከተነሳልኝ ለድርድር እቀመጣለሁ ማለቱ የተወሰነ አግራሞት ያሳደረባቸው ሰዎች ቢኖሩም፣ “ከዚህ ቡድን ጋር ድርድር አያስፈልግም፤ ኃይል ሰብስቦ መመለሱ ስለማይቀር ይህን እንዲያደርግ ጊዜ መስጠት ነው” ብለው የሚሞግቱ አሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከኦባሳንጆ የመቀሌ ጉዞ በኋላ የሰጠው መልስ ቀደም ብሎ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ከሰጠው ማብራሪያ ጋር ተመሳሳይ አንድምታ ያለው የሚመስል ሆኖ ታይቷል። በአፍሪቃ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እያደረጉ ያሉት ዕውነትን ማፈላለግ እንጂ፣ የድርድር ሒደት እንዳልሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ነበር በፌደራል መንግሥቱ በኩል እንደገና የተሰጠው። ይህም ኦባሳንጆ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከኹሉም አካላት መረጃ እንዲያገኙ መፍቀድ የአፍሪካ ኅብረትን የማክበርና የመቀበል ማሳያ መሆኑን እንጂ የድርድር አካል አለመሆኑን ነው መንግሥት ያመላከተው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሥልጠናና አቅም ግንባታ ኮሚቴ መሪ እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ የነበሩት ሀብታሙ ኪተባ እንደሚሉት፣ የፌዴራል መንግሥቱ አጣብቂኝ ውስጥ ነው፤ ከዚህ አጣብቂኝ መውጫ መንገዱ የሚፈልገው እደራደራለሁ እያለ ነው መሆን ያለበት ሲሉ ሐሳባቸውን ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ህወሓትም አንዲት ነጥብ ቢያገኝ ስለሚጠቅመው ኹለቱም ኃይሎች ድርደሩን ይፈልጉታል ነው የሚሉት።

እንዲሁም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ እየቀረበ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠም ቢሆን የምክር ቤቱን ሐሳብ እንደማይገፋ ማሳየት አለበት ባይ ናቸው። ለኢትዮጵያ ወዳጅ ሆነው የሚታዩት ቻይናና ሩስያም አፍሪካዊ መፍትሔን እንደሚያበረታቱ ስለሚገልጹ፣ ለዚህ አረንጓዴ መብራት በማሳየት ግን ደግሞ፣ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ፌዴራል መንግሥቱ በወታደራዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የተዛነፉበትን ነገሮች ለማስተካከል ሒደቱን ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ዕምነታቸውን አንስተዋል።

የኦባሳንጆ የማደራደር ሐሳብ የመጣው መንግሥት የመደራደር ፍላጎት አሳይቶ እንደሚሆን የጠቆሙት ሀብታሙ፣ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ብልህ ይሆናል የሚል ዕምነት አለኝ ሲሉም ነው የተናገሩት። አሁን ላይ ተደራደሩ የሚለው ጫና የምዕራባውያን ብቻ ሳይሆን፣ የሚደግፉን የምስራቅ አግሮችም ሐሳብ ጭምር በመሆኑ፣ መንግሥት የመደራደር ፍላጎቱን ዝግ ቢያደርግ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ስለሚገባ በጥንቃቄ ቅድመ ኹኔታዎችን በማስቀመጥ እንደሚሠራ ይገምታሉ። በዚህም ህወሓት መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን ቅድመ ኹኔታዎች ሊቀበል ስለማይችል የድርድሩ መሳካት አናሳ መሆኑን አመላክተዋል። አሁንም ቢሆን ያሉት ድርድር የማድረግ ፍላጎት ማሳያ ምዕራፍ ላይ እንጂ ድርድር ለማድረግ አልተስማሙም ብለዋል።

ሀብታሙ ኪታባ፣ የህወሓት የፖለቲካ ባህል ሰጥቶ በመቀበል የሚያምን ስላልሆነ፣ ጦርነቱ በድርድር ያልቃል የሚል ዕምነት የለኝም ሲሉ ነው የገለጹት። የፈጸማቸውን ግፎች ይቅር ብለን እንደራደር ቢባል እንኳን ዘመናዊ ፖለቲካ የሚከተል ድርጅት አይደለም ይላሉ።
ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ መሄዳቸውን አስመልክቶ ሀብታሙ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ወዳጅና አጋር እንዲኖራት ከተፈለገ ይህን ድርድር ሳትዘጋ ቅድመ ኹኔታዎችን አስቀምጣ በጥንቃቄ መጓዝ እንዳለባት ነው ያሰመሩበት።

ኦባሳንጆ ከፌዴራል መንግሥቱና ከትግራይ ኃይሎች በተጨማሪ፣ ከአማራና አፋር እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል መሪዎች ጋር መወያየታቸው፣ ፌዴራል መንግስቱ ብቻውን መወሰን መብቱ እንኳን ቢሆን፣ ይህ ውሳኔ የሕዝብ ቁጣን ስለሚቀሰቅስ ለሕዝቡ ስሜትም ከፌዴራል መንግሥቱ ይልቅ ክልሎች ቅርብ ስለሆኑ የሕዝቡን ውሳኔ ለማካተት ተፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ዕምነት አንጸባርቀዋል። የድርድር ውሳኔ ከተላለፈም ክልሎችን መሠረት አድርጎ ነው፤ ይህ ሳይሆን የሚደረግ ድርድር በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል የግንኙነት ክፍተት ሊፈጥር ይችላል ነው ያሉት። እንዲሁም፣ ይህ ኹሉ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ ለህወሓት ተጨማሪ የፖለቲካ አቅም ሊፈጥር የሚችል ማንኛውም ነገር ቢወሰድ፣ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደ ጎን በመተው በራሳቸው መንገድ ሊሄዱ ይችላሉ። ከዚህ በፊት ባሉ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ጎድቶናል የሚሉ ክልሎች በመኖራቸው አሁንም እንዳይደገም መሥራት እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጭው ያሳሰቡት ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፖለቲካ ፓርቲ የእነብሴ ሳርምድር ወረዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት ሲያምር ጌቱ እንዲሁ፣ ህወሓት በታሪኩ በድርድር የፈታው ችግር ስለመኖሩ አናውቅም ብለዋል። ጫካ ትግል ውስጥ በነበረበት ጊዜም አዘናግቶ እጁ የገቡትን ሲረሽን ነው የሚታወቀው። ስለዚህም ወደ ድርድር ይገባል፣ ውጤትም ይመጣል የሚል ዕምነት የለኝም ነው የሚሉት።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ወደ መቀሌ ማምራታቸውም፣ ኢትዮጵያ በኅብረቱ ተጠቅማ ሕዳሴ ግድቡን በሚመለከት ግብጽና ሱዳን ላይ ጫና ስታደርግ ስለነበር አሁን ጦርነት ሲሆን አልቀበልም ባለማለት ኅብረቱን ለማክበር ነው ብለዋል።
ድርድር በጦርነት ውስጥ ኹሌም ይኖራል የሚሉት ሲያምር፣ ነገር ግን አገር ማፍረስን ለሚፈልጉ ዕድል በሚሰጥ መልኩ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል። ድርድር ካለም በህወሓት መቃብር ላይ ሆነን ነው የሚደረገው። ስለሆነም አማራጭ የሌለው ድርድር መሆን ያለበት ህወሓትን ከነሰንኮፉ መቅበር ነው ባይ ናቸው። ነፍጥ አንስቶ ደጃችን ድረስ ከመጣና ለማሰብ የሚከብድ ግፍ በሕዝባችን ላይ ከሚፈጽም ቡድን ጋር በድርድር የሚፈታ ምንም ነገር አይኖርም። መፍትሔው ነፍጥ አንስቶ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ብቻ ነው። አመራሮቻችንም ግንባር ድረስ ዘምተው ሕዝብ እያበረታቱ ያሉት የድርድር ሐሳብ ጨርሶ ስለሌለን ነው ብለዋል።

ድርድር ቢደረግ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ እንደሚያስነሳና ፌዴራል መንግሥቱም በክልሎች ሕልውና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ የአንድን ክልል ስብራት ወደ ጎን ትቶ ድርድር ያደርጋል ብለው እንደማያስቡ ጠቁመዋል። አክለውም ኦባሳንጆ ከአፋርና ከአማራ ክልል በፊት ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር መወያየታቸው ግራ የሚያጋባ ነገር ቢኖረውም፣ በጥቅሉ ከክልሎች ጋር መወያየታቸው ብዙም ትርጉም ያለው ነገር አይደለም የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጫና ወጥታ አታውቅም፤ በታሪኳ ከብቸኛ ጠላት ጋር የተዋጋችው ጦርነትም የለም። ከድሮ ጀምሮ የእነሱ ተሳትፎ የሌለበት ጦርነት አልተደረገም። አሁንም ህወሓትን ስናሸንፍ እነሱንም ድል እናደርጋቸዋለን በማለት፣ በኢትዮጵያ ላይ በድርድር ስም የሚደርሰውን የውጭ ተጽዕኖ ገልጸውታል።

በአጠቃላይ ህወሓት የከፈተው ጦርነት ማብቂያ እንዲያገኝ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሚያደርጉት የማደራደር ጉትጎታ እንዳለ ሆኖ፣ ያን ኹሉ ግፍ ከፈጸመ ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን መንግሥት ራሱ አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ቡድን ጋር ሊደራደር ይችላል ብሎ ማሰብ ለብዙዎች የሚዋጥ ሐሳብ አይመስልም።

በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሥራቸውንና አካባቢያቸውን ጥለው አሸባሪውን ለመደምስስ እየተመሙ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ መንግሥት ከአሸባሪው ጋር ይደራደራል ብሎ መገመትም ለበርካቶች ያዳግታል። እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ አስቸኳይ የክተት ጥሪ ማወጁ ለምን አስፈለገ የሚሉና እና ይህ ከተደረገ ህወሓት የፈጸመው ድርጊት የጽድቅ መስሎ እንዲሰማው በማድረግ ወደፊትም ለጉልበተኞችና ለዘራፊዎች መንገድ የሚጠቁም ነው ይሉታል። ከዚህ ኃይል ጋር ድርድር ከተደረገ የአገሪቱን መፈራረስ ለሚጠባበቁ ቡድኖች የልብ ልብ የሚሰጥና ለአገራቸው ክብርና ሕልውና የተሰውትን ጀግኖች መስዋዕትነት ደመ ከልብ የሚያደርግ የወረደ ተግባር ነው ብለው የሚቃወሙትም አሉ።

ሽብርተኛ ለመሆን ለሚያስቡ አካላት መቀጣጫ እንዲሆንና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ሲባል የፈጀውን ጊዜና ገንዘብ ፈጅቶ፣ የተከፈለውን መስዋዕትነትም ቢሆን ከፍሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገዱ ማድረግ እንጂ፣ የምን መለሳለስ ነው ሲሉም አንዳንዶች ሐሳባቸውን ይገልጻሉ። ይህ ተራ ነገር ሳይሆን አገርን የማዳን ጉዳይ በመሆኑ፣ “ኢትዮጵያን ለማፈረስ ሲዖል ድረስም ቢሆን እሄዳለሁ” ከሚል ቡድን ጋር ምቹ ኹኔታን ለመፍጠር እንደራደር ስላለ ማመንና መደራደር አገርን ለበለጠ ስቃይ መዳረግ ስለሚሆን፣ መንግሥት የቡድኑን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ራሱ ደጋግሞ ሲገልጽ እንዳልነበር መልሶ የዘነጋው እንዳይመስልበት የሚሉም አሉ።

አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ቡድን የማያዳግም ቅጣት መቅጣት፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህወሓትን ጋልበው ለሚዋጉ ኃይሎችም ዘላለማዊ ማስተማሪያ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

መንግሥት ከህወሓት ጋር ቢደራደር ኢትዮጵያን ለሠላም ሳይሆን ለባርነት አሳልፎ ይሰጣል በማለት ብዙዎች ይሰጋሉ። ህወሓት ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ የላኩትን ኃይሎች ዓላማ ለማሳካት ቆርጦ የተነሳ ቡድን መሆኑ በመንግሥትም ስለተነገረ፣ ይህን ተልዕኮውን ትቶ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ግፍም በማመንና በመጸጸት ለሠላምና ለአገር ፍቅር ተገዥ ይሆናል ብሎ ለማመን እንደሚከብድ ብዙዎች ስማማሉ። ይልቁንም ድርድሩን ተጠቅሞ አስነዋሪና እኩይ ድርጊቱን ገፍቶበት፣ አገራችንንም ለወራሪ ኃይሎች አሳልፎ ሊሰጥና ማብቂያ ለሌለው ባርነት ይዳርገናል ነው የበርካቶች ሥጋት። እስካሁን ካደረገው፣ እያደረገ ካለው እና ከአመሠራረቱ ጀምሮ ካለው ታሪኩም በመነሳት ህወሓት ይህን አያደርግም ብሎ ማመን ለአብዛኛው ሰው የሚያዳግት ነው።

አሜሪካ ከህወሓት ጋር ድርድር እንዲደረግ በተደጋጋሚ ብትገልጽም፣ ራሷ ግን አሸባሪ ብላ የፈረጀቻቸውን ቡድኖች ስትመታና ለማጥፋት ሌት ተቀን ስትሠራ እንጂ፣ አሸባሪ ነው ካለችው ከአንድም ቡድን ጋር ስትደራደር ታይቶ አያውቅም። በአሜሪካ አገር የተፈጠረ አሸባሪ የተባለን ቡድን ቢሆን ኖሮ፣ እስትፋሱን የምትዘጋው ገና በለጋ እድሜው እንደነበር መገመት አያቅትም።

አሜሪካ የኢትዮጵያን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ የህወሓትን ሕልውና ለማስቀጠል የምትሻው ብዙዎች እንደሚሉት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ልዩ ፍላጎት የሚያስጠብቅላት፣ እንዲሁም የቻይናን የአፍሪካ ተጠቃሚነት የሚገታላት ሞግዚት ፍለጋ ነው ተብሎ ይታሰባል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን የጀግንነት ተምሳሌት በመሆኗም፣ መላው አፍሪካን ዝቅ ለማድረግ ከፍ ያለውን የኢትዮጵያውያንን ሥነ-ልቦና ማውረድ ያለባት በመሆኑ ጭምር ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ አጀንዳ የሆነው ይህ ጉዳይ ሲጠቃለል፣ መላው ኢትዮጵያውያን በየቦታው ህወሓትን እንደማይፈልጉት እየገለጹ ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜ፣ መንግሥት የብዙዎችን መስዋዕትነት መና አስቀርቶ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚፈለጉ ኃይሎች ጋር በቁርጠኝነት ከሚሠራው የህወሓት ቡድን ጋር ለወደፊት ይደራደር ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com