የእለት ዜና

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሚይዙት ጦር መሣሪያ ከኪስማዮ እየተጓጓዘ ይሆን?

የምሥራቅ አፍሪካ ወቅታዊ ሁኔታ ለብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት በር እየከፈተ እንደሚገኝ ይነገራል። በሶማሊያ ለዘመናት የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት ለአሸባሪዎችም ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ይሰማል። ይህን ለመግታት የኢትዮጵያና ኬንያ መንግሥታት የየራሳቸውን መፍትሔ ሲሞክሩ ቆይተዋል። ለቀጠናው አለመረጋጋት ጎሳዊ አስተሳሰብ በር መክፈቱ ቢነገርም፣ ሁኔታውን ያባባሰ የሕገ-ወጦች ድርጊት መኖሩም አይካድም። የምዕራባውያን ተፅዕኖ ያስከተለው መዘዝና አሁን አፍሪካ ማድረግ ያለባትን ጥንቃቄ ደሳለኝ ማናዬ እንደሚከተለው ተመልክቶታል።

በዓለም ዐቀፉ የደኅንነት ተቋም መረጃ መሠረት ምሥራቅ አፍሪካ አንድ የሕገ-ወጥ ሰንሠለት አለ። ይህ ሰንሠለት ከኪስማዮ ተነስቶ የኬንያ ሰሜናዊ ግዛት እስከሆነችው ጋሪሳ ከተማ ድረስ የተዘረጋ ነው። በዚህ መስመር ሦስት የኮንትሮባንድ ንግዶች ሲኖሩ የስኳር፣ የከሰልና የኤሌክትሮኒክ እንዲሁም የመድኃኒት ንግዶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ አደገኛ የኮንትሮባንድ ንግድ የተዘረጋበትና የሚካሄድበትን ቀጠና ስፋት ላጤነ ሰው ለጊዜው ማስታገሻ የማይገኝለት በሚመስል ራስ ምታት የሚያዝ ይሆናል።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ብዙዎቻችንን ‘ኪስማዮን እና ፓኪስታንን ምን አገናኛቸው?’ ሊያስብል ይችላል፤ ግን ሆኗል። የኮንትሮባንድ የንግድ ዕቃዎቹ ስኳር፣ ኤሌክትሮኒክ፣ አደገኛ ዕጽ ዝውውር ናቸው። ይህም ከአፍጋኒስታን ዕጽ፤ ከፓኪስታን ጦር መሣርያ፤ ከምሥራቅ አፍሪቃ ስኳር የሚመላለስበት ነው፤ የንግድ ሒደቱ። ኪስማዮ በሕገ-ወጥ የስኳር ንግድ በ2018 ብቻ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ልውውጥ ተካሂዶባታል።

አሁን አንድ ከባድ ሥጋት አለ። የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትና ራስ ገዝ አስተዳደሮች እርስ በእርስ የሚዋጉ ከሆነ፣ አሸባሪው አልሸባብና ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖች በሶማሊያ እንዳይፈለፈሉ የሚል። የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት (Federal Government of Somalia -FGS) አሁን ላይ የተለያዩ አማራጮችን እየሞከረ ይገኛል። የሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት መመሥርትም አለመመሥርትም ለኢትዮጵያ በርካታ ተጽዕኖዎች አሉት። ቀዳሚው የካራማራ ድል የቀለበሰውን የሶማሊያ ብሔርተኞች ቅዠት ለመመለስ የሚደረግ መውተርተር ነው። ሌላኛው ግን የሽብር ድርጅቶች መፈልፈያና የእጅ አዙር ጦርነት ማካሄጃ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ማስፋፊያ እንዳትሆን የሚል ስጋት ነው።

የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ በብዛት ጎሳና ነገድ ዘመም በመሆኑ አገራት ቋሚና ዘላቂ ድንበር እንዳይኖራቸው እያደረገ ነው (Christopher Calpham. The Horn Of Africa, State Formation And Decay.2017)። ከሦስት ዐስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የቀይ ባህር እመቤት ነበረች። በዚያው ልክ የሚያዋስኗት ድንበር ተጋሪ አገሮች ቁጥርም አሁን ካለው የተለየ ነበር። ኤርትራ ነፃ አገር ሆናለች፤ እናት አገር አትዮጵያም ወደብ አልባ ሆና የታሪክ ጠባሳ አርፎባታል።

የኢትዮጵያ ዕጣ ለሱዳንም ገጥሞ፣ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን በአውሮፓዊያኑ 2011 ተገንጥላ ነጻ አገር ሆናለች። እነዚህ የአፍሪቃ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካል ውጠቶች የእኔ ትውልድ በዐይኑ ያያቸው ናቸው። ግን በዚህ ብቻ የሚገደብ አይመስልም። አሁንም የተጠቀለለው የጎሳና ነገድ ፖለቲካ አፍሪቃ ቀንድ ላይ ተተርትሮ አላለቀም። ከፍተኛ ሥጋት ካለባቸው የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ሶማሊያና ሱዳን የፊተኞች ናቸው። በዓባይ ፖለቲካም እነዚህ አገራት ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ቀውስ የካይሮን ጆሮ ጠቢዎች የሚጠራ ነው። ቅድሚያ ሶማሊያና የሶማሊያ ፈርጣማ ራስ ገዝ አስተዳደሮች ያሉበትን የጂኦ ፖለቲካ ውግንና እንመልከት።

መጋቢት 2/ 2020 በደቡባዊ ሶማሊያ ጁባ ላንድ ባልዳሃዎ ግዛት፣ በማዕከላዊ መንግሥት ወታደሮችና በጁባ ላንድ የጸጥታ ኃይላት መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ጁባ ላንድ ከአምስቱ የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር አንዷ ነች። የራስ ገዝ አስታደደሯ ከኬንያ ጋር ትዋሰናለች። የኬንያ መንግሥትም የሞቃዲሾ ወታደሮች በማንዴራ ከተማ የኬንያን ንብረት አውድመዋል የሚል መግለጫ ሰጥታለች።

ኬንያ በየጊዜው የግዛት አንድነቴን አትፈታተነኝ የሚል ማስጠንቀቂያ ትሰጣለች። ከዚህ አኳያ ኬንያ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ይልቅ የጁባ ላንድ ወዳጅነቷ ይበልጥባታል። ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነው የጁባ ላንድ ገዥው ሼህ አሕመድ ኢዝላም ማዶቤ የምርጫ ሒደትና ያስከተለው ውዝግብ ነው። ማዶቤ ወደ እዚህ በትረ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በኬንያ ወታደሮች ደጋፍ እንደሚደረግለት የሚታመነው የራስ ካምቦኒ ታጣቂ ቡድን የጦር መሪ ነበሩ።

የኬንያ ጦር በ2011 በአፍሪቃ ኅብረት ጥያቄ መሠረት ወደ ሶማሊያ ከገባ ጊዜ ጀምሮም ከማዶቤ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። ማዶቤ በቅርቡ ዳግም የመመረጥ ሁኔታ ግን ለሶማሊያው ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ሰላም የሚሰጥ አልሆነም። ፋርማጆ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት መመሥረት ይፈልጋሉ። ይህ አካሄዳቸው ግን በማዶቤና ሌሎች የራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዝዳንቶች ፈተና ውስጥ ገብቶባቸዋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ማዶቤን በአንድ ነገር ይከሷቸዋል፤ የኬንያን እንጂ የሶማሊያን ጥቅም እያስከበሩ አይደለም በሚል። በእርግጥ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚደገፉ ሰው ናቸው። መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ የማስተባበያ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የማዶቤን አካሄድ ለመቀልበስ በስውር ተንቀሳቅሳለች በሚል ትወነጅላለች።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በ2011 ፑንትላንድ እና ጋልሙዱንግ ጎብኝተው ነበር። ግን በፑንትላድ ያደረጉት ጉብኝት ያለ ስምምነት የተጠናቀቀ ነበር። ጁባ ላንድ ከአምስቱ ራስ ገዝ የሶማሊያ ፌዴራል ግዛቶች የትብብር ሥምምነት ያልፈረመች ብቸኛዋ ግዛት ሆናለች። ሼህ ማዶቤ ግን በአስተዳደሯ ትልቅ ተሰሚነት እያገኙ የመጡ መሪ ናቸው። ከ74 የጁባ ላንድ የሕዝብ እንደራሴ መቀመጫዎች ውስጥ 56 በማግኘት ነው ያሸነፉት። ማዶቤ ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አከርካሪው የተመታውና የተደመሰሰው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት ወታደራዊ አባል ነበር።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል። በሌላ በኩል፣ የጁባላንዱ ሰው ደግሞ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ከጆሞ ኬንያታ ልጅ ኡሁሩ ጋር የሞቀ ግንኙነት አላቸው። አንድ ኬንያዊ ጋዜጠኛ አዲስ አበባ ውስጥ ለአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ዘገባ መጥቶ እንዳጫወተኝ፤ የኡሁሩና ማዶቤ ግንኙነት መነሻው የደኅንነት ጉዳይ ነው። ማዶቤ የአሸባሪው አል ሽባብን ሰዎች ስትራቴጂና የነውጥ መርሃ ግብር በሚገባ የሚያውቅ ሰው ነው። ስለዚህ ኬንያ ፑንትላንድ ሰዎች ጋር በመሆን ራስ ገዝ አስተዳደሯን የአልሽባብ መከለያ ቀጣና እያደረገቻት ነው።

ከዚህ አኳያ በመጪው የ2021 የኬንያ ምርጫ ላይ የሶማሊያ መረጋጋት ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እየቀረበ ነው። የናይሮቢና ሞቃዲሾ ግንኙነት በባህር ዳርቻ ይዞታ ይገባኛል ጥያቄም ብዙ ጊዜ እየተፈተነ ይገኛል። በሌላ በኩል፣ የጁባ ላንድ መዲና ኪስማዮም የሚገኘው የኪስማዮ ወደብ ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው። በተለይ ለአሸባሪው አልሽባብ የገንዝብ ምንጭ ከዚሁ ወደብ የሚገኝ ነው ይባላል። በዚህም የተነሳ ኬንያ፣ ማዶቤ አልሽባብን ከስፍራው እንዲያስወጣ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋለታለች።

የኪስማዩ ወደብ ጥልቅ ውኃ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት የሶማሊያ ወደቦች መካከል አንዱ ነው። የኪስማዮ ሰሜናዊ ጫፍ ለኬንያና ኢትዮጵያ ካለው ቅርበት አኳያ በምሥራቅ አፍሪቃ ከሚካሄዱ የስኳርና ከሰል የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሁም የአደገኛ ዕጽ ዝውውር ማካሄጃ ቦታዎች ወይም ቀጣናዎች አንዱ ነው። ከዚህ ቀጠና በቅርብ ርቅት ላይ አሜሪካ ነበረች። አሁን ግን እርሷም ከዚያ ቀጠና ለአዲሱ ፍትጊያ ሌላ ቀጣና እያማተረች ነው።

ምሥራቅ አውሮፓ እና ባልካን ቀጠና
አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየወጣች መሆኗ በቀጠናው በሚኖራት ተሰሚነት ዙሪያ ጥያቄ አጭሯል። በተቃራኒው ሩስያ እና ቻይና ወደዚያ የነዳጅ ቋት የሚያደርጉት ግስጋሴ ተጠናክሯል። አሁን ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመርህ ደረጃ የኦባማ እሳቤ በሚል ይጠራል። የማስፈጸሚያ ስልቱ ግን እንደየመጡት ፕሬዝዳንቶች የተለያየ ሆኗል። የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በቅርበት የመረመሩት እና ሦስት መጽሐፍ የፃፉት ኢያን ቤርሜር እንደሚሉት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባለፉት ሦስት ዐስርት ዓመታት ሦስት ያህል እጥፋቶችን አድርጎ ዛሬ ላይ ደርሷል።

የእነ ሬገን ኒዮሊበራሊዝም ቀኖና፣ የአባት እና ልጅ የቡሽ ዘመን የሳይቀድምህ ቅደም ‹ፕሪ ኤምቲቭ ኢምፓየር› ከመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃት ማግስት በተለይ ተጠናክሮ ነበር። እነዚህን ምዕራፎችን አጠናቆ ኦባማ ዘመን ላይ ገባ። ከግጭት ቀጠናዎች የመውጣት ‹ዊዝድሮዋል ፖሊሲ›፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስትራቴጂ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የሚያስገርመው ነገር ይላሉ ኢያን ቤርሜር፣ የኦባማን ዘመን ዕሳቤ ሲደመስሱ አራት ዓመታት በነጩ ቤተ መንግሥት ያሳለፉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የኦባማን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሠረቱ መናድ አልፈለጉም ነበር። ከሶሪያ፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከኢራቅ ወታደሮቻቸውን እንዲወጡ አድርገዋል። ከጃፓን ከኮሪያም እንዲሁ በማስጠንቀቂያ አልፈዋቸዋል። የተወሰኑትን አስወጥተዋል። ኦባማ ሔደው ትራምፕ ተተክተው፣ ትራምፕ ተሸኝተው የመጡት ባይደንም በዚያው በቀድሞው አለቃቸው ኦባማ መንገድ እያዘገሙ ለመሆናቸው መረጃዎች እየወጡ ነው።

ላለፉት 50 ዓመታት ያህል የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመዳፋቸውን ያህል አብጠርጥረው የሚያውቁት፣ የቀየሱት ቢባል የሚቀለው አንጋፋው ዲፕሎማት ሔነሪ ኪሲንጀር እንደሚሉት፤ አሜሪካ አዲስ ዓለም ፈጥራ አዲሱ ሥርዓት እርጅና ሲጫነው ሌላ ሥርዓት በዚያ ፍርስራሽ ላይ ለማንበር አዲስ ሽርጉድ ላይ ነች። ይህ ሽር ጉድ ግን እንደ ካሁን ቀደሙ ቀላል አይሆንም ባይ ናቸው። ምክንያቱም የትናንት የዋሽንግተን ተቀናቃኞች የራሳቸው የቤት ውስጥ ሳንካዎች ነበሯቸው። የዛሬዎቹ ግን ያን ያህል በጓዳ ፖለቲካ የሚታመሱ አይደሉም። ከዚያ በተቃራኒው አሜሪካ በውስጥ ፖለቲካ እየታመሰች ነው ይላሉ።

በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት የሚሠራው ስትራትፎር ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆርጅ ፍሬድማን እንደሚሉት፣ አሜሪካ እና አሜሪካውያን እውነታውን መጋፈጥ አለባቸው። የዓለም ሥርዓት ፍፁማዊ ለውጥ እየተካሄደበት ነው ይላሉ። አሜሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ ገሸሽ እያለች ወይም እያፈገፈገች መጓዝ መጀመሯ፣ በዚያ የነዳጅ ቋት የሚገኙ አጋሮቿን ሥጋት ላይ ጥሏል ባይ ናቸው።

ሰሞኑን የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች እና ዘመናዊ ሚሳኤሎች፣ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች፣ ባህር ሰርጓጅ የጦር መርከቦች የሰፈሩባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ እና ባህረ ሰላጤው አገራት፣ ዋሽንግተን እነዚህን ጦር መሣሪያዎች እንደምታስወጣ በዲፕሎማሲው መንገድ በወታደራዊ አታሼዎች በኩል ተነግሯቸዋል ይላሉ። ይህ መሆኑ በዚያ የሚገኙ ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ አጋሮች አዲስ የደኅንነት ሥጋት እንደተደቀነባቸው እየተናገሩ ነው።

በተለይ ሱኒዎቹ ከሺያዋ ኢራን በኩል ከባድ ሥጋት እንደተጋረጠባቸው አቤት እያሉ ነው። ይህ የሥጋት ውሽንፍር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዴት እንደሚከላከሉት ግን እስካሁን ይፋ ያደረጉት ስትራቴጂ የለም። በዚህም አሜሪካ ነባር ወዳጆቿን ያውም የነዳጅ ፖለቲካ ያስተሳሰረው የዘመናት ዲፕሎማሲው ላይ ትልቅ መሰናክል እንዳይደረድርበት አስግቷል። የባይደን ሰዎች ግን አማራጭ ብለው ያስቀመጡት ኢራንን ወደ ቬናው የኒዩክሌር ስምምነት መመለስ እና የኒዩክለርን ቦንብ እንዳትታጠቅ በግልፅ መሥራት የሚል ነው።

የዲፕሎማሲ ፈታሽ ጽሞናዊ ሒሳዊ ጸሐፍት እንደሚሉት ግን፣ የዋሽንግተን ሰዎች የዚያን ቀጣና ፖለቲካ ለኹለቱ አዲስ ሙሽሮች ለመተው ያሰቡ ይመስላል ባይ ናቸው። በእነርሱ የዲፕሎማሲ ሥልት ለመደነስም እያቀዱ እንደሆነ በመተንተን ላይ ናቸው። በእስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች። እነዚህ አብርሃማዊ ስምምነት የፈጸሙት አገራት በባህረ ሰላጤው ጂኦ ፖለቲካ የአሜሪካ እና ምዕራብ ዘመን ርዕዮትን አስቀጣይ ሆነው ለመሥራት ትጥቅ እና ስንቅ እየታጠቁ መሆናቸው ይዘረዝር ጀምሯል።

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ግን የአሜሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ የማፈግፈግ ጅማሮ በፍላጎት ሳይሆን የአንተ ትብስ ፖለቲካ ጅማሮ ነው ይላል። ደግሞ የአንተ ትብስ ፖለቲካ እንዴት ያለ ይሆን? ነገርዮው እንዲህ ነው። አሁን አሁን ምሥራቅ አውሮፓ እና የባልካን ቀጠና በከፍተኛ ደረጃ በሩስያ ወታደራዊ ክንድ ሥጋት ውስጥ እንደገቡ ለአሜሪካ አቤት እያሉ ነው። ዘ ኦኮኖሚስት ‹ዘ ስሞል በት ስትራቴጂክ ኔሽንስ› ይላቸዋል። ሞስኮ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት ሌት ከቀንም መሥራቷ ለአሁናዊ ተፈሪነቷ አድርሷታል።

አሜሪካ የነዳጅ ነገር በታዳሽ ኃይል እየተተካ የመምጣቱን ዝማሜ እያጤነች፣ አሁን እንደ ቀደመው ማዝገም አልፈለገችም። ከመካከለኛው ምሥራቅ እየወጣች ምሥራቅ አውሮፓ ላይ ራሽያን የመግታት ስትራቴጂ ጥድፊያ ላይ ነች። ይህ ምን አልባትም ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ አዲስ የኃይል አሰላለፍ፣ አዲስ ካርታ ብወዛ ሊፈጥር ይችል ይሆናል? አፍሪካን መሰል አኅጉራት ይህን አይነቱ ስትራቴጂካዌ ልውጠት ቆም ብለው ማጤን የግድ ይላቸዋል።

ደሳለኝ ማናዬን፤ በኢሜል አድራሻቸው dessalegnmanaye@gmail.com ላይ ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com