የእለት ዜና

የ12 ክፍል ፈተና ያልተፈተኑ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ጉዳትና መፍትሔው

ተማሪ ብሩክ ኃይሉ ይባላል። ከሐምሌ 27/2013 ጀምሮ ሲኖርበት ከነበረው የሰሜን ወሎ አካባቢ በጦርነቱ ምክንያት በመፈናቀል እህቶቹን ይዞ ወደ አዲስ አበባ እንዳቀና ይናገራል።
ተማሪ ብሩክ እንደሚለው ከሆነ፣ ካሳለፍነው ጥቅምት 29/2014 እስከ ኅዳር 2/2014 በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቂያ ፈታና አልተሳተፈም።

ሆኖም ግን በአካባቢው በሚገኝ የትምህርት ተቋም ፈተናውን እንዳይወስድ፣ በአገራችን ከተከሰተ ሰንበትበት ባለው ጦርነት ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እንኳን ፈተና መፈተን በአካቢበው በሠላም መኖር እንዳልቻለ ያወሳል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ትምህርት መቀጠል እንዳልቻሉ አመላክቶ፣ ሠላም በሰፈነባቸው አካባቢ ያሉ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቹን ተቀብለው እንዲያስተናግዷቸው ባደረገው የድጋፍ ጥሪ መሠረት፣ ብሩክ ኃይሉ በአዲስ አበባ ከተማ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ለመሳተፍ ሙከራ አድርጎ ነበር።

ብሩክ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፈተናውን ለመፈተን ብዙ ሙከራ ቢያደርግም፤ የመፈተን ዕድል እንዳላገኘና በዚህም ቀላል የማይባል የሥነ ልቦና ተፅዕኖ እንደደረሰበት አብራርቷል።
በፈተናው ለመሳተፍ ከነበረው ፍላጎት አንጻር በፈተናው መቀመጥ የሚችልበትን መሥፈርት ለመጠየቅ ወደ አገር አቀፍ የፈተናዎች ምዘናና ኤጀንሲ ያቀናው ብሩክ፣ ኤጀንሲው በከተማው ስር ለሚገኘው “በሻሌ” ትምህርት ቤት ደብዳቤ ጽፎለት ነበር።
ብሩክ ለየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ቢሮ ደብዳቤውን ቢያቀርብም፣ ቢሮው “ወታደር ነው እንጅ በየሄደበት የሚፈተነው እናንተ መፈተን አትችሉም” ብሎ እንደመለሰው ይናገራል።
በሌላ በኩል፣ በለሚ ኩራ ትምህርት ቢሮም ተመሳሳይ ተጨማሪ ሙከራ ያደረገ ሲሆን፣ ትምህርት ቢሮው እርሱም ሆነ ጓደኞቹ የያዙትን ደብዳቤ ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆነ ነው የጠቆመው።

ሙከራው ያልተሳካለት ተማሪው በዚህም ተስፋ እንደቆረጠና ፈተና አለመፈተኑ ቀላል የማይባል የሥነ ልቦና ጉዳት እንደተሰማው ያወሳል። ተማሪ ብሩክ እንደሚናገረው ከሆነ፣ እርሱ ብቻ ሳይሆን አብረውት ወደ መዲናዋ ያቀኑ ሦስት እህቶቹ፣ የተቋረጠ የትምህርት ገበታቸውን እንዲጀምሩ ያደረገው ጥረትም እንዳልተሳከለት አመላክቷል።

ብሩክ ሦስቱ እህቶቹ የአምስት፣ የስድስትና የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች በመሆናቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተቀላቅለው ትምህርታቸውን እንዲማሩ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።
በዚህም እርሱ ብቻ ሳይሆን ሦስቱ እህቶቹም በጦርነቱ ካደረባቸው የሥነ ልቦና አሉታዊ ተጽዕኖ በተጨማሪ የትምህርታቸው መቋረጥም፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሆነባቸው ነው የሚናገረው።

ተማሪ ብሩክ እኩዮቹ በዕቅዳቸው መሠረት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በሚፈተኑበት ወቅት፣ እርሱና ሌሎች በተመሳሳይ ችግር ምክንያት በፈተናው መሳተፍ ያልቻሉ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
አያይዞም፣ ሠላም ባለበት አካባቢ ፈተናውን ለተፈተኑ ተማሪዎች ኹሉ መልካም ውጤትን ተመኝቶ፣ ትምህርት ቢሮ በአሁኑ ፈተና ያልተሳተፉ ተማሪዎች በኹለተኛ ዙር እንዲሚሳተፉ ያመላከተውን ማስታወቂያ በተስፋ እንደሚጠብቅ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።
ወቅቱን ጠብቆ ፈታናዎችን የመፈተኑ ጉዳይ ሰንሠለቱ ከተዛባ ሰንበትበት ስለማለቱ የኮሮና ወረርሽ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ተማሪዎች የሚያሳልፉት ነባራዊ ሁኔታ ሕያው ምስክር ነው።
በአገራችን መጋቢት 4/2012 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘው ወረርሽኝ በየዕለቱ አያሌ ሰዎችን እያሳጣን መሆኑ አይዘነጋም።

ይህም ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙ በርካታ ውስብስብ ችግሮችንም እንዳስከተለ ብዙዎች ሲያወሱ ይደመጣል። በርካታ ከተባሉት ችግሮች መካከልም አንዱና ዋነኛው በወረርሽኙ ሳቢያ የትምህርት ተቋማት መዘጋት ሲሆን፣ በዚህም ወቅቱን ጠብቆ የትምህርት ገበታን ተከታትሎ ወደ ቀጣዩ ደረጃ የማለፍ ጉዳይ፣ ‹‹እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እየተጓዘ›› መምጣቱ ነው።

ይህን በተመለከተም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 7/2012 ባስተላለፉት መመሪያ መሠረት፣ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ተደርገው መቆየታቸውና ከወራቶች ቆይታ በኋላ በ2013 የተጓተተው ትምህርት እንደገና መጀመሩ የሚታወስ ነው።
በዚህም ቀላል የማይባል የትምህርት ጊዜ መሸራረፍ እንደተከሰተ፣ በ2013 መፈተን የነበረባቸው ተማሪዎች የፈተና የሚፈተኑበት ጊዜ ወደ 2014 መሸጋገሩ የሚታወቅ ነው።

ይህም አገራዊ ክስተት ከመዋዕለ-ሕፃናት ት/ቤቶች ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማረዎች ላይ ቀላል የማይባል የሥነ-ልቦና ቀውስ አስከትሎ እንደነበር የገፈቱ ቀማሾች ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በጊዜው ደጋግመው ሲያወሱ ይሰሙ ነበር።
አንዱ ችግር ሥር ነቀል መፍትሔ ሳይበጅለት፣ ሌላኛው ችግር በር በማንኳኳቱ፣ የትምህርት ጉዳይ አሁንም ቢሆን በተማሪዎች ላይ የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።
በኮሮና ምክንያት ሲቆራረጥ የቆየው የትምህርትን ጉዳይ አሁንም ቢሆን፣ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በመጀመሪያና በኹለተኛ ዙር እንዲከፋፈሉ ምክንያት መሆኑ አልቀረም።

ለአሁናዊ የተማሪዎች የሥነ ልቦና ተጽዕኖ ደግሞ ግንባር ቀደም መንስኤው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ጥቅምት 24/2013 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተስፋፋ የመጣው ጦርነት ነው።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም አካባቢ ባይልም፣ በብዙዎቹ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች ተማሪዎች የትምህርት ገበታቸውን መከታተል እንዳልቻሉና የትምህርት ዕቅዳቸው እንደተዛባባቸው ይታወቃል።
ለአብነት ያህል እንኳን ጦርነቱ ሲጀመር በትግራይ ክልል በአራቱም (በራያ፤ በመቀሌ፤ በአዲግራትና በአክሱም) ዩኒቨርስቲዎች የነበሩ ጠቅላላ 10 ሺሕ 164 ተማሪዎች በጸጥታ ችግር ከሐምሌ አንድ 2013 እስከ ነሐሴ 6/2013 በሰመራ ዩኒቨርስቲ አድርገው እንዲመጡ ማድረጉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያመላክታል።

በዚህም ተማሪዎቹ የሥነ ልቦና ተጽዕኖ እንዳደረባቸው ሲያወሱ መቆየታቸውና በመጨረሻ ሰሞኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሠላም ወደ ሰፈነባቸው የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች እንዲመደቡ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ምንም እንኳን በ2014 የትምህርት ዘመን ሠላም በሰፈነባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ተማሪዎች በተቻለ መጠን ወቅቱን ጠብቀው የትምህርት ገበታቸውን የመከታተል ዕድል ቢያገኙም፣ በጦርቱ ቀጠና አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች “እንኳን ትምርታችንን ልንከታተል ትምህርት ቤታችንም ፍርስርስ ብሏል” በማለት ይናገራሉ።

ይህን በተመለከትም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በርካታ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ እንደወደሙ አመላክቶ፣ ሠላም ባለበት በአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ሁሉም የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቹን ተቀብለው እንዲያስተናግዱ ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።
በጦርነቱ ትምህርታቸውን መከታተል ካልቻሉትና ቅሬታ ከሚያነሱት ተማሪዎች መካከል ካሳለፍነው ጥቅምት 29/2014 እስከ ህዳር 2/2014 በተሰጠው፣ በ2013 መከናወን የነበረበት የ12ኛ ክፍል ፈተና የመሳተፍ ዕድሉን ያላገኙ ተማሪዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።
በዚህም በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና ለመፈተን ከ600ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንደተመዘገቡ የተነገረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሥር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች 36ሺሕ 401 ተማሪዎች ፈተና ተቀምጠዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ 36ሺሕ 340 ተማሪዎች ደግሞ ለቀጣይ ዙር ፈተና ቀጠሮ እንደተሰጡ ተመላክቷል።

በዚህም፣ በተለይም ከተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ የተፈናቀሉ በርካታ ተማሪዎች ተደራራቢ የሥነ ልቦና ድቀት እየተሰማቸው ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በጉዳዩ አዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ካደረጉት መካከል ጠረፍ አሰፋ የተባለችው ተማሪ፣ ‘‘ሲጀመር ተማሪዎች ለመፈተን እየገቡ ባየሁበት ሰዓት በጣም ነው የተሰማኝ” ስትል ነው የተሰማትን ስሜት የገለጸችው።
እንደተማሪዋ ንግግር ከሆነ፣ የነበረችበት አካባቢ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በመሆኑ የ12ኛ ክፍል ፈተናን መፈተን ብትፈልግም ሳይሳካላት እንደቀረ ነው መረዳት የተቻለው።

ጠረፍ አሰፋ እንደተናገረችው ከሆነ፣ ለፈተናው ዝግጀት ብታደርግም ፈተናው ለመፈተን እንዳልቻለች አመላክታ፣ የኹለተኛው ዙር ፈተና በቶሎ እንዲሰጥ ነው ለሚመለከተው አካል ያሳሰበችው።
ሌላኛው ሻምበል ተስፋዬ የተባለው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ተማሪ፣ ፈተናውን ባለመፈተኑ 50 ፐርሰንት እንደከፋውና በግማሽ ደግሞ አለመፈተኑ መልካም እንደሆነ አብራርቷል።
አለመፈተኑን በመልካምነት የወሰደው ሻምበል እንደሚናገረው ከሆነ፣ ሙሉ ትኩረቱና ጭንቀቱ ወደ ጦርነቱ በመሆኑ ለፈተና አልተዘጋጀም ነበር።

እንደ ሻምበል ገለጻ ከሆነ፣ ፈተናውን አለመፈተኑ አሉታዊ የሥነ ልቦና ጫና እንዳሳደረበት ባይደብቅም፣ ሳይዘጋጁ ፈተና መፈተን ውጤቱ ያማረ ስለማይሆን በቅድሚያ አገር ሠላም መሆን እንዳለባት ያምናል።
ጉዳዩን በተመለከተ ሌላኛዋ ሜላት ፈንታው የተባለችው ተማሪ፣ ፈተናውን አለመፈተኗ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን በፈተናው ላልተሳተፉት ሁሉ ጉዳት እንዳለው ጠቁማለች።
ሜላት አያይዛም፣ “ቀድሞ በኮሮና ምክንያት ትምህርት ሲቆራረጥ ነበር፤ አሁንም በጦርነቱ ምክንያት መማር አልቻልንም፤ ሳንማር መፈተኑ ተገቢ አይመስለኝም። ቢሆንም ግን ችግሮች ተፈትተው በቅርቡ ለመፈተን ተስፋ አደርጋለሁ” ስትል ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸችው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት በአማኑኤል ሆስፒታል ከሚያገለግሉት የሥነ አእምሮ ስፔሻሊስት ኢሳያስ ክብሮም ጋር ቆይታ ያረገች ሲሆን፣ ለችግሩ ያላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ በሚከተለው መልኩ ተናግረዋል።
የሥነ አእምሮ ስፔሻሊስቱ፣ ተማሪዎች የሚያነሱት ችግር ከሕይወት ውጣ ውረዶች መካከል አንዱ ስለሆነ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገርም ሊከሰት የሚችል ነው በማለት ጀምረው፣ በተማሪዎቹ ላይ የሚያመጣው ችግር ከባድ ቢሆንም መቋቋም እንደሚቻል አመላክተዋል።

ችግር ሊፈጠር ይችላል፤ ለምን ተፈጠረ? ከማለት ይልቅ መፍትሔ ማፈላለጉ የተሻለ መሆኑ ላይ አትኩሮት ከተሰጠ፣ በችግር ወስጥ ማለፍ የበለጠ ጥንካሬ እንደሚለግስ ነው የገለጹት።
“ወጣቶች ላይ አርቆ የማየት ትልቅ ችግር አለ” የሚሉት ኢሳያስ ክብሮም፣ ቤተሰቦቻቸው ወደፊት የሚመጣውን የመልካም ነገር አድማስ አሻግረው ሊያሳዩዋቸው ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

ይበልጥ ጉዳት የሚያደርሰው የችግር መከሰት ሳይሆን፣ ክፉው ነገር እንደማያልፍ ለአእምሮው በማወጅ ተስፋ በቆረጠ ጭፍን አስተሳሰብ መዋኘት ነው የሚሉት የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ባለሙያው፣ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር ድብርት ለተሰማቸው ተማሪዎች ችግሩ የተፈጠረው በእነርሱ ብቻ እንዳልሆነ እያሳሰቡ ምክር መስጠቱ ትልቅ መፍትሔ ነው ብለዋል።

አክለውም፣ ችግር ሊያጠነክር እንጅ ሊያደክም አይመጣምና ተማሪም ማጥናት ያለበት ለመፈተን ብቻ ሳይሆን ዕውቀት ለማግኘትም በመሆኑ፣ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ በተለይም እንደ ኢትዮጵያዊነት ወደ እግዚአብሔር በጸሎት በመቅረብ ተስፋ ማድረግ ዋነኛው መፍትሔ ነው ሲሉ ነው ምክራቸውን የለገሱን።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!